Breaking News
Home / Amharic / ኢትዮጵያ ከአማጺው ሕወሃት ጋር ለማደራደር ከሁለቱ ወገኖች ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል!

ኢትዮጵያ ከአማጺው ሕወሃት ጋር ለማደራደር ከሁለቱ ወገኖች ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል!

1፤ የሕወሃት ኃይሎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘውን ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማ ዛሬ እንደተቆጣጠሩ ከዓይን እማኞች መስማቱን ሮይተርስ ማምሻውን ዘግቧል። የከተማዋ ነዋሪዎች ከማለዳ ጀምሮ ትግሬኛ ተናጋሪ ተዋጊዎችን በከተማዋ ጎዳናዎች መመልከታቸውንና በርካታ ነዋሪዎች ከተማዋን ጥለው መሸሻቸውን ዓይን እማኞች ተናግረዋል። የዓይን እማኞችን ምስክርነት ከገለልተኛ ወገን አለማረጋገጡን ዜና ወኪሉ ገልጧል።
2፤ ሕገወጥ ገንዘቦች እና ቁሳቁሶች እንደሆኑ ተገልጦ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በተሰራጨው ፎቶ ላይ የሚታዩት ጥሬ ገንዘቦችና የሕክምና ቁሳቁሶች የዓለማቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች መሆናቸውን ድርጅቱ ዛሬ በድረገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ፎቶው የሚያሳየው በመንግሥት ሕጋዊ ፍቃድ ያገኙና ከሁለት ሳምንት በፊት በ5 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ሲጓጓዙ አፋር ክልል ፍተሻ ጣቢያ ላይ ፎቶ የተነሱ መድሃኒቶችንና ገንዘብን እንጅ ሕገወጥ ቁሳቁሶች አይደሉም- ብሏል ድርጅቱ። ቁሳቁሶቹ መቀሌ እንደደረሱ የገለጠው ድርጅቱ፣ ጥሬ ገንዘብ ለማጓጓዝ የተገደድኩት በትግራይ የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ ነው ብሏል።
3፤ ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የሚነገሩ አንዳንድ ስብዕናን የሚያዋርዱ ቃላት እንዳሳሰቧቸው የአሜሪካው ዓለማቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት ዩኤስአይዲ ሃላፊ ሳማንታ ፓዎር ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ይህንኑ ስጋቴን ለኢትዮጵያዋ ሰላም ሚንስትር ሙፈሪያት ከሚል አጋርቻቸዋለሁ ያሉት ሃላፊዋ፣ አዋራጅ ቃላትን መጠቀም ውጥረቱን እንደሚያባብሰው እና ማንነት ላይ ላነጣጠሩ ጭፍጨፋዎች መንገድ ጠራጊ ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጠዋል። ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይገባ ሁሉም ወገኖች መሰናክል እየሆኑ እንደሆነ ሳማንታ ጠቁመዋል። አሁን ለክልሉ እየገባ ያለው ዕትዳታ ከሚፈለገው 10 በመቶ ብቻ እንደሆነ ገልጠዋል።
4፤ የሕወሃት ኃይሎች በአማራ ክልል ውስጥ በከፈቱት ጦርነት ከ200 ሺህ በላይ የክልሉ ነዋሪዎች ከቀያቸው እንደተፈናቀሉ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ ለሮይተርስ ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ሕዝብ በሕወሃት ምክንያት ሲፈናቀል ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ግን ዝምታን መርጧል በማለት ፋንታ ወቅሰዋል። ተመድ በግጭቱ ለተፈናቀሉ የአማራ እና አፋር ክልሎች ተረጅዎች ጭምር ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን የድርጅቱ ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ትናንት ለውጭ ዜና ወኪሎች ተናግረዋል።
5፤ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የኢትዮጵያ መንግሥትን ከአማጺው ሕወሃት ጋር ለማደራደር ከሁለቱ ወገኖች ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሐምዶክ የአደራዳሪነት ፍላጎታቸውን ለኢጋድ፣ ለኤርትራ እና አሜሪካ እና ፈረንሳይን ጨምሮ ለአንዳንድ ምዕራባዊያን ወዳጅ ሀገራት አሳውቀዋል። የሱዳን ባለሥልጣናት የትግራዩ ግጭት ወደ ሌላኛው የሱዳን አጎራባች ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሊጋባ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። አሜሪካ ሱዳን ያቀረበችውን የማሸማገል ሃሳብ አሜሪካ እንደምትደግፈው የአሜሪካው ዓለማቀፍ ልማት ተራድዖ ድርጅት ዩኤስአይዲ ሃላፊ ሳማንታ ፓዎር በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
6፤ ሱዳን ከኢትዮጵያ 1 ሺህ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል ለመግዛት ፍላጎት እንዳሳየች ኢዜአ አንድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሃላፊን በመጥቀስ ዘግቧል። በሱዳን ጥያቄ ላይ ለመወያየት የኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ባለፈው ወር ወደ ካርቱም አቅንተው እንደነበርና የሱዳን ባለሙያዎችም ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ሃላፊው ተናግረዋል። ደቡብ ሱዳንም ተመሳሳይ ጥያቄ እንዳቀረበች የገለጹት ሃላፊው፣ ስለ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ዝርጋታ ለመነጋገር የባለሙያዎች ቡድን በቅርቡ ወደ ጁባ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
7፤ ኢትዮጵያ እንደ ቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ልትፈራርስ ትችላለች የሚሉ ወገኖች የያዙት አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን አምባሳደር ቲቦር ናዥ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ከ2 ሺህ ዓመታት በላይ ታሪክ እና በርካታ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈችውን ኢትዮጵያን በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ማግስት ሀገር ሆና ከተፈጠረችውና ከሩብ ክፍለ ዘመን በፊት በርስበርስ ጦርነት ከፈራረሰችው ዩጎዝላቪያ ጋር ማወዳደር አያስኬድም- ብለዋል ናዥ። ኢትዮጵያ ወደፊት ሰላሟ ሲመለስላት እንደገና እንደምታንሰራራ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ የነበሩት ናዥ እምነታቸውን ገልጠዋል።
8፤ አፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ለእስራዓል የታዛቢነት መቀመጫ መስጠቱን በመቃወም 7 ዐረብ የአፍሪካ ሀገራት ለኅብረቱ ደብዳቤ እንዳስገቡ የዐረብ ሀገራት ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የኅብረቱን ውሳኔ ተቃውመው ደብዳቤ ያስገቡት የኅብረቱ አባል ሀገራት፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ቱኒዚያ፣ አልጀሪያ፣ ኮሞሮስ፣ ሞሪታኒያ እና ሊቢያ እንደሆኑ ተሰምቷል። ሀገራቱ ተቃውሟቸውን የገለጹት፣ አፍሪካ ኅብረት ለፍልስጤማዊያን ካለው ነባር የአጋርነት መርህ ጋር ይጋጫል በማለት ነው። ደቡብ አፍሪካ ኅብረቱ ለእስራኤል የታዛቢነት መቀመጫ የሰጣት አባል ሀገራትን ሳያማክር ነው በማለት ባለፈው ሳምንት ያወገዘች ሲሆን፣ የኅብረቱ መሪዎች በጉዳዩ ላይ ሊወያዩበት እንደሚገባ አሳስባለች።
9፤ የተቃዋሚው የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ሬክ ማቻርን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት እና ከንቅናቄው ጦር ሠራዊት አዛዥነት አንስተናል በማለት ትናንት ያወጡትን መግለጫ የፓርቲው ፖሊት ቢሮ እንዳጣጣለው ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘግቧል። መግለጫውን ያወጡት ጥቂት ጀኔራሎች የንቅናቄውን ሠራዊት የማይወክሉ ሰላም አደፍራሾች ናቸው- ብሏቸዋል የፓርቲው ከፍተኛ ውሳኔ ሰጭ አካል ዛሬ ባወጣው መግለጫ። ጀኔራሎቹ በማቻር ምትክ የአማጺያኑ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ሲሞን ዱዋል የፓርቲው ጊዜያዊ ሊቀመንበርና የሠራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ እንዲሆኑ ሰይመናል ብለው ነበር። ማቻር በአንድነት ሽግግር መንግሥቱ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ የአማጺያኑ ሠራዊትና የመንግሥት ሠራዊት ግን እስካሁን አልተቀላቀሉም።

[ዋዜማ ራዲዮ]
 
 
 

Check Also

የኮሎኔል አብይ አህመድ አስገራሚ የትምህርት መረጃዎች ! የትኛው ነው ትክክል?

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

One comment

  1. ኢትዮጵያ ከአማጺው ሕወሃት ጋር ለማደራደር ከሁለቱ ወገኖች ጋር ግንኙነት እንደጀመሩ የሱዳን ዜና ምንጮች ዘግበዋል! የሚለው ዚና ከእውነት የራቀ ነው በትናንትናው እለት ማለት በ5/8/2021 የሱዳኑ ጠቅላኡ ሚኒስተር ሃምዶክ ሁለቱን ወገን ላደርደር ብሎ መጠየቁን ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሰክረታሪ ብለኒ ተገቢው መልስ መሰጠቱንና ሱዳን በምንም አይነት ተአማኒነት እንደሊላትና ለምንም ነገር ብቁ እንዳልሆነች ተነግሮታል ስለዚህ የሱዳን የዚና ምንጮች የሚያራግቡትን የጁንታውን ምኞት ባታስተጋቡ እና ሰዉን ውጅንብር ውስጥ ባትከቱት ጥሩ ነው አንዳንዲም ዝምታ ጥሩ ነው ፤

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.