Breaking News
Home / News / የአዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ በአዲስ አበባ ከተማና በነዋሪዎቿ ላይ በኦሮሞ ሃይሎች እየተፈፀሙ ያሉትን በደሎችና ሴራዎች በተመለከተ መፍትሔ እንዲሰጡ ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል።

ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚ አብይ አህመድ
Posted on February 9, 2019 by Addis Ababa

ጥር 2011 ዓ.ም.

ግልባጭ – ለኢፌድሪ ጠ/ሚ ጽሕፈት ቤት

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ጉዳዩ : የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪዎች ሁለንተናዊ መብቶችና የተጋረጡባቸው መሰናክሎችን ይመለከታል፡፡

ይድረስ ለክቡር ጠ/ሚ አብይ አህመድ (ዶ/ር),

እንደሚታወቀው ባለፉት 27 አመታት በኢትዮጵያችን ከዘውግ ማንነት በቀር ሌላ የማያውቅ መዋቅርና ህገመንግስት አለህዝብ ፈቃድና ህገመንግስታዊ ሂደት በመጫኑ ህዝባችንን በጋራ ያኖሩ የአንድነትና ውህደት እሴቶቹ ለአደጋ ከመጋለጣቸውም በላይ፣ በህወሀት መራሹ አምባገነናዊ ስርአት አፈና ምክንያት ማናቸውም ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ታግደውና ተገድበው ቆይተዋል፡፡ ህይወትና ደም በተገበረበት የህዝብ ትግልም አሁን ብዙዎች ወደተሻለ ነገ እንዲያሻግራቸው ተስፋ የጣሉበትና በጎ ጅምሮችን ያሳየ ለውጥ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርስዎም ለአመታት ከመንግስት ልሳን ተፍቆ የነበረውን ኢትዮጵያዊ ማንነትና ትርክት በልዩ ልዩ መድረኮች በማንሳትዎና ሰሚ አጥተው የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያንን በማነቃቃትዎ ከፍ ያለ ምስጋናችን ይድረስዎ፡፡

ይህ ተስፋችንና በጎ ተምኔታችን እንዳለ ሆኖ የአዲስ አበባ እና የነዋሪዎችዋ ሁለንተናዊ መብቶች ጉዳይ ቸል መባሉና የተሳሳቱ የህግና የፖለቲካ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸው ግን ቅሬታ ፈጥሮብናል፡፡ ስጋትም አሳድሮብናል፡፡ ስለሆነም፣ ዝንጋኤውና ስህተቱ አብቅቶ በአዲስአበባና አዲስአበቤዎች ጉዳይ ላይ ዜጎችን እኩል የሚያደርግና ወደፊት ተመልካች የሆነ አቋምና ርዕዮት ይይዙ ዘንድ በዚህ ግልጽ ደብዳቤ ጥያቄዎቻችንን ልናቀርብልዎ፣ ሃሳቦቻችንንም ልናጋራዎ ፈልገናል፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እንደሚያውቁት አዲስ አበባና ነዋሪዎችዋ የኢፌድሪ ሕገ-መንግስት ከጸደቀ ጀምሮ በህገመንግስት፣ በሌሎች ዝርዝር ህግጋት፣ በጠቅላላው መዋቅርና የእነርሱ መብት ጠባቂና ፍላጎት ፈጻሚ ሊሆን ይገባው በነበረ የከተማው አስተዳደር አካላት ሳይቀር ድርብርብ ህገመንግስታዊ፣ መዋቅራዊና ፖለቲካዊ በደሎችን ሲያስተናግዱ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በማስተናገድ ላይ ናቸው፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገመንግስት ብቸኛ መሰረት ባደረገው የብሄር ማንነት የማይገለጹ፣ የኢትዮጵያውያንን ሁሉን አይነት ስብጥርና ቅንብር በውበት አዋህደውና አበልጽገው የያዙ አዲስ አበባን የመሰሉ ፤ በአንድ የብሄር ሳጥን ውስጥ የማይገቡ ከተሞችና አካባቢዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ድርሻ እንዳይኖራቸው የህግ፣ የፖለቲካና የመዋቅር ሻጥር ከመሰራቱም በላይ፣ በራሳቸው ህልውናና እጣ ላይ ምንም የወሳኝነት ሚና እንዳይኖራቸው ተገልለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም የዚህ አፈና ሰለባ ሆነው ድምጻቸውን የማሰማት ዕድል ሳይሰጣቸው፤ ጠብመንጃ በያዙ አምባገነኖችና ተባባሪዎቻቸው ቀንበር ስር እንዲውሉ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሀገረ/መንግስት መናገሻና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ እጣ ፈንታዋ ሆን ተብሎ እንዲዋልልም ተደርጓል፡፡

ሆኖም፣ ይህ ህገመንግስታዊና መዋቅራዊ ችግር ቢኖርም፣ በጊዜ ሂደት ህገመንግስታዊና መዋቅራዊ ማሻሻያ እስኪደረግ ድረስ የዚህን ህገመንግስት ማእቀፍ ተከትሎ መረጋገጥ ባለባቸው የአዲስአበባ ነዋሪዎች መብቶች ዙርያም በርካታ ችግሮች ተደቅነዋል፡፡ በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር (በአዋጅ ቁጥር 361/95፣ ከተማዋን የሚያስተዳድር ምክር ቤት እና አስፈጻሚ አካላት እንደሚሰየሙ፤ በአዋጁ (አንቀጽ 12(1)) መሰረት የምክር ቤቱ አባላት በየአምስት አመቱ በከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚመረጡ፤ የተመረጡት ተወካዮችም ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ የከተማው አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ የሚሆነውን ከንቲባ እንዲሁም ምክትል ከንቲባ እንደሚመርጡ የሚደነግግ ሆኖ ሳለ፣ ይህ የህጉ አንቀጽ ጨርሶ ግልጽነት በሌለው፣ ህዝብን ባላሳተፈና በተድበሰበሰ ሁናቴ ተቀይሮ አቶ ታከለ ኡማ ምክትል ከንቲባ ሆነው አለአግባብ ተሹመዋል፡፡

በአ.ሁ.ን እምነት ይህ ተግባር ጸረዲሞክራሲያዊና የአዲስአበባ ነዋሪን ፈቃድ የረገጠ ከመሆኑም በላይ የህግን የበላይነት የጣሰ አንድን ግለሰብ ወደስልጣን ለማምጣት ሲባል የተከናወነ የፖለቲካና የህግ ስህተት ነው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ ድንጋጌ መሰረት የአዲስአበባና ድሬዳዋ ከተሞች ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ መከናወን የነበረበት ቢሆንም በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም. በሃገሪቱ ውስጥ በነበረው የጸጥታ እና ያለመረጋጋት ችግር ምክንያት የተራዘመው ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ የሚጠቁም ምንጭ ከከተማው አስተዳደርም ሆነ ከጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ማግኘት አለመቻሉ አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህም በላይ የከንቲባውን ቦታ ክፍት በመተው ምክትል ከንቲባው በተዘዋዋሪ የዋና ከንቲባ ቦታ እንዲይዙ በመደረጉ ምክትል ከንቲባው ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ ያገኙትን ስልጣን ተጠቅመው በከተማችን ላይ ነዋሪው ያልተስማማባቸውን ዘላቂና አሉታዊ ለውጦችን እውን ለማድረግ እየሰሩ ስለመሆኑ የሚጠቁሙ በርካታ መረጃዎች አሉ።

ስለሆነም፣ ካለፈው ዓመት መገባደጃ ጀምሮ የአ.አ. ነዋሪዎች ሲያነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች ደግመን ለእርሶ ጠ/ሚ አብይ አህመድ እናቀርባለን ክቡር ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪዎችን እራስን በራስ የማስተዳደርና የከተማዋን ነዋሪዎች ሰብአዊ ዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶች አስመልክቶ ግልጽና እርግጠኛ አቋምዎ ምንድነው; እርስዎ ወደስልጣን ሲመጡ ያልተቆጠበ ድጋፍ የሰጠውን የአዲስአበባ ነዋሪ ፈቃድ ገፍቶ፣ ለ27 አመታት የተንገላታበትን አፈና በሚያስቀጥል ሁኔታ እንደተወካዩ የማያያቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ነዋሪው ፍላጎቱንና መብቱን የሚጻረር አጀንዳ ይዘው እንደመጡ የሚቆጥራቸውን ምክትል ከንቲባ በህዝቡ ላይ መሾምዎ ስለምንድነው; በአሁን ወቅት በአዲስአበባ ከተማ መዋቅር ውስጥ የሚከናወኑት ህገወጥና ድብቅ ተግባራት አላማስ ምን ይሆን; የፖለቲካ ትርፍ በማግኘት ስሌት ነዋሪ ላልሆኑ ሰዎች መታወቂያ በገፍ ማደልን ጨምሮ የህዝቡን አሰፋፈርና የከተማዋን ማህበረፖለቲካዊ መሰረት ለማዛባት የሚካሄዱ ማናቸውንም ይፋና ህቡእ እርምጃዎችን አምርረን እንቃወማለን፡፡

የአ.አ. ነዋሪዎች ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብትና ነፃነት ተነፍገን ፣ እንደዜጋ ሳንታወቅና ሳንከበር፣ ይልቁንስ ከአገራችን ኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ተገልለን ባለንበት ሁኔታ ለውጥ መጣ ብሎ ማመን ያስቸግራል። እርሶም ወደ ጠ/ሚ ቦታ ከመጡ በኋላ የከተማችን ወጣት መብቱን ስለጠየቀ ብቻ ታፍሶ አለተገቢ የህግ ሂደት Due Process of law ለህግ ክብር የሌላቸውየጸጥታ አካላት እንዲያንገላቱት መፍቀድዎ እጅጉን ያሳዝናል፡፡ የአዲስአበባ ነዋሪ ስለነጻነቱና መብቶቹ ውድ ዋጋ የከፈለ ህዝብ ነው፡፡ አላማውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሃገሩ በእኩልነት የሚኖርባትን አገር ለመገንባት እንጂ እርሱ እንደሁለተኛ ዜጋ የሚቆጠርበትን ስርአት ለማስቀጠል አይደለም፡፡ አንዱ ልጅ ሌላው የእንጀራ ልጅ ሆኖ የሚኖርባት አገር መንግስት አይጸናም። የእርሶ መንግስት አ.አ. እና ድሬዳዋን በሚመለከት የሚወስደው እርምጃ በታሪክ ያስጠይቆታልና የተፈጸሙ ስህተቶችን ከወዲሁ በማረም በህግ መብታችንን መጠቀም እንድንችል በምናደርገው ሰላማዊ ትግል ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ክቡር ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ ሃገር የሚቀናውና የሚበለጽገው በሚተገበር ሕግ እናበዜጎች መሃል ልዩነት በማያደርግና በማያበላልጥ መዋቅር መሆኑን በመገንዘብ የአዲስአበባ ከተማ ነዋሪ መብቶች ችላ መባላቸው እና ሕጎች አለመከበራቸው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ እርሶ የሚሰብኩት ርዕዮት በተግባር እንዲገለጥና እኛም የምናልማትን የእኩልነትና ፍትህ ሃገር እንድናይ ከተፈለገ እነኚህን መሰል መሰረታዊ የዜግነት መብቶች ችላ ተብለው ሊሳካ አይችልም ስንል ማሳሰቢያችንን እናስተላልፋለን::

Check Also

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

ድሮን ሲያስተኩስ የነበረው ባንዳ በፋኖ ተያዘ ! እኔን ያየህ ተቀጣ !

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.