Breaking News
Home / Amharic / በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የቅማንት ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ::

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የቅማንት ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ::

በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙ የቅማንት ተወላጆች የተሰጠ መግለጫ
*****
አገራችን ኢትዮጵያ ለሃያ ሰባት ዓመታት ከተጓዘችበት የውድቀት፣ የሰቆቃ፣ የዘረፋና የጥፋት ጎዳና ወጥታ የተስፋ፣ የስላምና የዴሞክራሲያዊ መንገድ ጀምራለች። ይሁን እንጂ ህወሐት ሲመራው የነበረው መንግስት የሕዝቡን የቆዩ የአንድነት እሴቶችን አደጋ ላይ ጥሎ ሕዝቧን በዘር፣ በቋንቋ፣ በሐይማኖት፣ በጎሳና በነገድ በመከፋፈል የጥላቻ ግንብ በማቆምና የቆየውን የአንድነት ትስስር በመናድ በሐገሪቱና በሕዝቧ ሕልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዲፈጠር አድርጓል። የዚህ የህወሐት እኩይ አላማና ተግባር አንዱ የሆነው በጎንደር ውስጥ በሚኖሩ የቅማንትና አማራ ወገኖቻችን መካከል እየተፈፀመ ያለው ደባ የተሞላበት ጥፋት ነው።

የቅማንት ማህበረሰብ ከአማራ ወንድሙ ጋር ለዘመናት በደም፤ በአጥንት፤ በቋንቋ፤ በሐይማኖት፤ በስነልቦናና በመልክዓምድር አቀማመጥ አንድ ሆኖ የኖረ ሕዝብ ሲሆን እጣ ፈንታውም የተቆራኘ ነው። ሆኖም ከለውጡ በፊት የአማራን ክልል ያስተዳድር የነበረው ‹‹ብአዴን›› በህወሐት አምሳል የተፈጠረ ስለነበር ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ባሉት መዋቅሮችና በመንግስት የፖለቲካ ወጥመድ ውስጥ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በገቡ ግለሰቦችና ስብስቦች ተጠቅሞ አሁን በጎንደር አካባቢ ‹‹የቅማንትና አማራ ግጭት›› እየተባለ የሚካሄደውን ሁከትና ግጭት እንዲፈጠር ረዥም አመታት የወሰደ የተለያዩ ተንኮሎችንና ሴራዎችን መፈጸሙ ይታወቃል። ይህንን የህወሐት ሴራ ለማክሸፍ የቅማንት ሕዝብ ከአማራ ወገኖቹ ጋር በመሆን ከፍተኛ ትግል ሲካሄድ ቆይቶል፤ አሁንም እያካሄደ ይገኛል።

ህወሐት በ1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ አካባቢውን ለመከፋፈል አስቧቸው ከነበሩት እቅዶች አንዱ የቅማንትን ሕዝብ በፖለቲካ አደራጅቶ የሽግግር መንግስቱ አካል የማድረግ ሴራ ነበር። ይህ ሴራ የጎንደርን ሕዝብ አማራና ቅማንት ብሎ ከፋፍሎ ለመምታት የታሰበ ተንኮል መሆኑን አርቆ አሳቢ የቅማንት ልጆች በመረዳታቸው ከጅምሩ ውድቅ አደርገውታል። በጎንደር ሕዝብ መካከል ‹‹ቅማንትና አማራ›› ብሎ በቀላሉ መለያየት አስቸጋሪ መሆኑን የተረዳው ህወሐትም ዘዴውን ቀይሮ ስውር የፖለቲካ አካሄድን ተግባራዊ በማድረግና ይህንን አስታኮ የሚነሳን ጥያቄ ተጠቅሞ የመከፋፈል አላማውን ለማስፈጸም እንዲቻለው ብዙ ሴራ ሰርቷል።

ለዚህም የሚታወቀውን የቅማንትን ታሪክ ከመዝገብ በመፋቅ፤ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ ‹‹ቅማንት›› የሚባል ህዝብ የለም የሚል አዋጅ አውጥቶ በሚዲያዎቹ በማሰራጨት፤ በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የቅማንት ሕዝብ እንዳይካተት በማድረግ፤ የቅማንትን ታሪክ እያጣመሙና እያንቋሸሹ በማቅረብ፤ ወጣቱ ትውልድ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረውና የስውር ፖለቲካ ተጠቂ እንዲሆን በማድረግ፤ ከክልል እስከ ፌዴራል የመንግስት መዋቅሮች ባስቀመጧቸው ካድሬዎች ተጠቅሞ ላለፉት 27 አመታት ሲሰራው የኖረው ተንኮል አድጎ ውጤቱ አሁን ከደረስንበት አሳዛኝና አሳፋሪ ደረጃ ላይ ሊደርስ ችሏል።

በዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት ‹‹የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ›› በሚል ሽፋን በተነሳው ግጭት ምክንያት የብዙ ሰዎች ህይወት እየጠፋና አካል እየጎደለ፤ ከፍተኛ የንብረት ውድመት እየደረሰ ይገኛል።
ይህ ለቅማንት ሕዝብም ሆነ አንድ አካልና አምሳል ለሆነው ለአማራ ህዝብ የማይጠቅም ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለና ወደፊትም የሚያስከትል ሰው ሰራሽና የህወሐት ፖለቲካ የወለደው ችግር በመሆኑ በአፋጣኝ የሚቆምበትንና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍንበትን ሁኔታ ለማገዝ በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የቅማንት ተወላጅ ተቆርቆሪዎች ከተደጋጋሚ የቴሌ ኮንፈረስ ውይይቶች በኋላ ‹‹በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የቅማንት ተወላጆች›› ተብሎ የሚጠራ ጊዜያዊ ስብስብ ተመሰርቷል።

የዚህ ስብስብ አላማ የቅማንትንና የአማራን አንድነት ለማረጋገጥና ዛሬ በኢትዮጵያዊያን ትግልና መስዋእትነት በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ የመጨረሻ መርዙን በመርጨት ላይ የሚገኘውን የህወሐትን እኩይ አላማ ለማምከን፤ አንድ አካልና አምሳል የሆንውን የአማራና የቅማንት ህዝብ አንድነት፤ ፍቅርና መተሳሰብ ማጠናከር ነው።

ከዚህ አላማ በመነሳትም የሚከተለውን መግለጫ አውጥተናል።
1. በተከሰተው ግጭት ዙሪያ ሁሉም ወገን ከጠብ ጫሪነት እና ግጭቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ ማንኛውም ድሪጊቶች እንዲቆጠቡ፤ ይህም በሶሻል ሜዲያ ከሚካሄዱ ንግግሮችና የሀሳብ ልውውጦች ጀምሮ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያነሳሱና የተለየ በደልንም ሆነ ጥቅምን የሚያንፅባርቁ እንዳይሆኑ፤ ይልቁንም የኖረውን አንድነት፤ መተሳሰብና ፍቅር የሚያጎለብቱ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባ መሆኑን እናሳስባለን።

2. ይህ ችግር ጊዜያዊና የጎንደር ህዝብ ችግር ሲሆን የሚፈታውም በራሱ በጎንደር ህዝብ (ቅማንትና አማራ) አንድነት ዙሪያ ነው። ይሁን እንጅ ችግሩን በተንኮል ላብራቶሪያቸው ፈጥረው ከዚህ ያደረሱት አካላት ለቅማንት ተቆርቋሪ በመምሰል በሌላው አካባቢ እንደሚያደርጉት ሁሉ የጎንደርን አካባቢ ብሎም የአማራን ክልል ለማወክና ሰላም ለመንሳት በፌስ ቡካቸውና በሌላ ብዙሃን መገናኛ ሚዲያቸው ተጠቅመው ቅማንትና አማራ እያሉ በማለያየት ድሀውንና ሰላም ፈላጊውን ህዝብ እያጋጩት ይገኛሉ። በመሆኑም ጊዜው እየጠለቀባቸው ያሉት ወገኖችም ሆኑ ሌሎች አካላት ተቆርቋሪ በመምሰልና ችግሩን በማራገብ ወደ ባሰ ግጭት እንዲያመራ የሚያደርጉትን ሴራና ጣልቃ ገብነት እያወገዝን ከዚህ እኩይ አድራጎታቸው እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

3. መላው የጎንደር ህዝብም አባቶቻችን ገብርየና ገልሞ በአንድ ቀንበር ተጠምደው ያቆሙትን አገርና ያቆዩትን ታሪክ በከፋፍለህ አጥቃው የጠላት ሴራ እንዳይፈርስ የመጠበቅ ዳግማዊ የታሪክ አደራ የወደቀብህ መሆኑን ባለመዘንጋት፤ እርስ በርስ ጣት ከመቀሳሰርና ከመተናነቅ ወጥተህ፤ ተንኮሉን ተረድተህ፤ አሁንም እንደ ጥንቱ በአንድ ቀንበር ገብተህ አንድነትህን ማስከበር ብቻ ሳይሆን ምሳሌነትህን ዳግም ሊያንጸባርቅ በሚችልበት ሁኔታ ተባብረህና ተያይዘህ እንድትቆም አጥብቀን እናሳስባለን።

4. የቅማንት ህዝብ የሚፈልገው እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመልካም አስተዳደር፤ የዲሞክራሲና የህግ የበላይነት፤ በአጠቃላይ በሀገራችን መልካም ሰራዓት ሰፍኖ ማየትና የዚያ ስርዓት የጋራ ተጠቃሚ የመሆን እንጅ የተለየ ፍላጎት ኖሮትም አያውቅ፤ ሊኖረውም አይችልም። ከዚህ ጽኑ እምነቱ የተነሳ የቅማንት ህዝብ በአንዲት የጋራ ኢትዮጵያ የሚያምን፤ በረዥሙ ታሪኩ ይህን ያረጋገጠ እንጅ ወርዶ ለቀበሌና ለወረዳ የሚናቆር ህዝብ አለመሆኑን ታሪክ ይመሰክራል። አገራችን አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ያደረሳት አንቀጽ 39 ነገ ከነገ ወዴያ ሊለወጥ የሚችል ሲሆን በሕዝባችን መሐከል እየተረጨ ያለው መርዝ ግን ካሁኑ ካልተገታ ለዘመናት የሚቆይ ጠባሳ ሊፈጥር ይችላል ብለን እናምናልን። በመሆኑም የቅማንት ህዝብ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ተብሎ አሁን ለተከሰተው ችግር እንደምክንያት የቀረበው አጀንዳ ስውር ሴራ ያለው፤ መስመሩን የሳተና የቅማንትን የማንነት ጥያቄ በቅጡ ያላገናዘበ መሆኑ እየታወቀ፤ ይህን ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ የቅማንት የማንነት ጥያቄ አቅራቢ ወገኖቻችን ሕዝባችን ወዴት እየወሰዱት እንደሆነ ቆም ብለው እንዲያስቡ እናሳስባለን።

5. የህዝብ ፍላጎት የሚወሰነው ሁሉንም አካል ባሳተፈ ጥልቀትና ስፋት ባለው ውይይትና ምክክር እንጅ፤ በነውጥና በኃይል ወይም እኛ እናውቅልሀለን በሚሉ ጥቂት ከማህበረሰቡ በወጡ ግለሰቦች ፍላጎትና ስውር አላማ መሆን የለበትም። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፕብሊክ መንግስት ማህበረሰቡ መክሮና ዘክሮ ከሚወስነው ውሳኔ ውጪ የሚሰጥ ውሳኔ በቅማንት ሕዝብ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ሊያውቁ ይገባል። በዚህ የተነሳ ማንም አካል ማህበረሰቡን እወክላለሁ በሚል ከዚህ በፊት የተወሰኑ ውሳኔዎችም ሆኑ የተደረሱ ስምምነቶች ካሉ በቅማንት ሕዝብ ዘንድ ምንም አይነት ዕውቅናና ተቀባይነት እንደሌላቸው ሊታወቅ ይገባል። አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጊዜያዊ ችግርን ከመፍራትም ሆነ ኃላፊነትን ከመሸሽ የተነሳ ቀደም ሲል በተንኮል የተፈጸሙ ሴራዎችን በማባበልና በማሳደግ አንድ የሆነውን የቅማንትንና የአማራን ህዝብ የሚያፋጅ፤ የኖረውን የጎንደርን ታሪክ የሚያጎድፍ፤ ክልሉን አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ከመወሰን እንዲቆጠብ፤ ከዚህ በፊት የተላለፉትን የመለያየትና የመከለል ውሳኔዎችን ሰርዞ ቅማንትና አማራ ሳይባል በቆየው የአንድነት አስተዳደር የሚቀጥል መሆኑን ለህዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ እንጠይቃለን።

6. በህወሐት ካድሬዎችና በነበረከት ሰሞዖን የተቀነባበረው ጎንደርን ብሎም የአማራን ክልል የማፍረስ ሴራና በወንድማማቾች መካከል እየታየ ያለውን ግጭት ህብረተሰቡ ተገንዝቦ ተገቢውን የሰላም ውይይት እንዲያካሂድ ወደ ህብረተሰቡ ገብቶ በመስራት የአካባቢውን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት የማስጠበቅና ህግ የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።

7. በአሁኑ ወቅት ብዙ የመንግስት ሰራተኞች ከስራ ገበታቸው ተፈናቅለው በመጠለያና በዘመድ አዝማድ ቤት ተጠግተው ይገኛሉ። መንግስት እነዚህን የተፈናቀሉ ሰራተኞች ክፍያ ከቆመበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ደመወዛቸውን በመክፈል ወደነበሩበት የስራ ገበታቸው እንዲመለሱ እንዲያደርግ እንጠይቃለን።

8. በተፈጠረው ችግር ብዙ ሰዎች ሞተዋል፤ ቆስለዋል፤ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ ንብረቶች ወድመዋል፤ ከማሳ ላይ የነበረ እህል እና የእህል ክምሮች ተቃጥለዋል። በአጠቃላይ ጉዳቱ የደረሰባቸው ወገኖች ከዕለት ጉርስ ጀምሮ እስከ መጠለያ ማጣት ባለው ከፍተኛ ችግሮች ውስጥ ይገኛሉ። መንግስት ለእነዚህ ተጎጅ ወገኖች ልዩ ድጎማ በመመደብ እንዲቋቋሙ ይረዳ ዘንድ እናሳስባለን። ከቀያቸው የተፈናቀሉት ሁሉ ወደ ነበረ ይዞታቸው እንዲመለሱ፤ ለሞቱት ቤተሰቦችና ለአካል ጉዳተኞች ካሳ እንዲከፈል፤ ለወደመው ንብረት ግምቱ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።

9. ከማንኛውም በኩል ለዚህ ሁሉ የሰው ሞት፤ የንብረት ውድመት፤ መፈናቀልና በአጠቃላይ ስርዓት አልበኝነት መንገስ ምክንያት የሆኑ፤ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንጠይቃለን።

10. የአካባቢውን ሰላምና የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚንቀሳቀሱ የፀጥታ አካላት ችግሩ እንዲይባባስ ምክንያት እንዳይሆኑና ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተገቢው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲመደቡና እንዲደራጁ እናሳስባለን።

11. የኢትዮጵያ ሕዝብ ታግሎ ያገኘውን ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ፤ ለአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፈን፤ የቅማንት ሕዝብ ከሌሎች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ለዕርቅና ለሰላም እንዲሰራና የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪያችን እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም በአንድነቷ ጸንታ ትኑር፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ፤
በሰሜን አሜሪካ የምንገኝ የቅማንት ተወላጆች፤
ጥር 10 ቀን 2011 ዓ.ም።

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

2 comments

  1. Concerned Ethiopia

    My tip to Dawit Abebaw and wuhibegzair (exclusive to their interview by the Amahra Mass media):
    The ANM disrespect the Qimant question. First it recognizes the question otherwise it is going to bring the previous regime. After all who is ANM – does it have any concern for the millions who live in different parts of Ethiopia. Are you curios for the millions or for only your self. Who is Dawit Abebaw, who is wuhibegzair Ferede. Are they educated personnel. They requested for the national defense to leave the Amahara region especially in Chilga. Because they are unhappy as the extreme genocide on Chilga qimant community has not been occurred, like on other qimant community. Who Dawit and wuhibegzair are? Please think for your community who live in Oromia and other parts of Ethiopia.
    The Amahara mass media please be genuine and particpate both parties (the Qimant representatives and the Amahra), not only the extremists.
    Thank you

  2. Concerned Ethiopia

    My tip to the Amahra Mass media:
    The ANM disrespect the Qimant question. First it recognizes the question otherwise it is going to bring the previous regime. After all who is ANM – does it have any concern for the millions who live in different parts of Ethiopia. Are you curios for the millions or for only your self. Who is Dawit Abebaw, who is wuhibegzair Ferede. Are they educated personnel. They requested for the national defense to leave the Amahara region especially in Chilga. Because they are unhappy as the extreme genocide on Chilga qimant community has not been occurred, like on other qimant community. Who Dawit and wuhibegzair are? Please think for your community who live in Oromia and other parts of Ethiopia.
    The Amahara mass media please be genuine and particpate both parties (the Qimant representatives and the Amahra), not only the extremists.
    Thank you

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.