Breaking News
Home / Amharic / የተከበራችሁ የአሥራት ሚድያ ቤተሰቦችና ወዳጆች፤

የተከበራችሁ የአሥራት ሚድያ ቤተሰቦችና ወዳጆች፤

አሥራት ሚድያ ከአንድ ዓመት ከጥቂት ወራት በፊት ለወገናቸው ችግር ቀድመው ደራሽ በሆኑ የአማራ ልጆች ርብርብ ሲመሰረት፤ ተስፋ የተደረገው የአማራ ሕዝብ ልጆች ብቸኛ የሆነውን የሕዝባቸውን ድምጽ በገንዘባቸው፣ በጉልበታቸውና በጊዜያቸው ደግፈው እንደሚያስቀጥሉት በመተማመን ብቻ እንደነበር እናምናለን። ለዚህም በቂ የሰው ኃይል፣ የገንዘብ፣ የዕውቀትና የአንድነት አቅም እንዳሉትም በማመን እንደሆነ እናምናለን።

ባለፉት ጥቂት ወራት አሥራት ሚድያን ለመምራት ኃላፊነት ስንረከብ ተቋሙ የነበሩበትን የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት ካለዕረፍት ዘርፈ-ብዙ ጥረት ስናደርግ ቆይተናል። በተለይ በውጭ ከሚኖሩ የማኅበረሰባችን ክፍሎች ጋር የመተማመንና የመደጋገፍ መንፈስን ለማጠናከር ብዙ ጥረቶች አድርገናል። ለወደፊትም ለመቀጠል ፍላጎትና ቁርጠኝነት አለን። በዚህ ጥረታችን ቀላል የማይባል የማኅበረሰባችንን አባላት ቁጥር ወደአሥራት ደጋፊነት ለመመለስ ችለናል። ተጨማሪ ኃይል በማሰባሰብ በአመራርና በድጋፍ ለማሳተፍ ከተለያዩ አካላት ጋር የሚደረጉ ጥረቶችም ቀጥለዋል።

ሆኖም “ገብስ የሚደርስ በፍልሰታ፤ እኔ “…” ነገ ማታ” አለ እንደሚባለው ወገናችን፤ ልናሰባስብ የቻልነው አቅም፤ ከሚያስፈልገን እጂግ ያነሰ ነው። በሌላ ወገን፤ አቅዶና ተልሞ ተቋሙን የማዳከም ፍላጎት ያለ እስኪመስል ድረስ፤ ፈረንጆቹ “ተንሸራታች ዒላማ” ብለው የሚጠሩትን ተለዋዋጭና ተከታታይ አጀንዳ በማምጣት ሕዝባችን ተቋሙን እንዳይረዳ ከማሳነፍ ጀምሮ እስከ ስም ማጉደፍ ድረስ የዘለቁ የተለያዩ የፈጠራና ጸጉር የመሰንጠቅ ትርክቶች ሲሰራጩ እያየን እንገኛለን።

ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ፤ ተቋሙ የፋይናንስ ግዴታዎቹን ለመወጣት አቅሙ እየደከመ መጥቷል። ወጮቹን ቢቀንስም አሁንም ያልተከፈሉ ዕዳዎች አሉበት፤ የሥራ ማስኬጃ ወጮቹን ለመሸፈንም እየተቸገረ ይገኛል። በመሆኑም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተቋሙ ነጻነት አደጋ ላይ የሚወድቅበትና የአሥራት ቴሌቪዥን ከሳተላይት ሊወርድ የሚችልበት አደጋ ተጋርጦበታል። ኃላፊነቱን ከተረከበበት ጥቂት ወራት ጀምሮ የአሥራት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ይህን ተቋም ለማቆየት የሚችለውን ሁሉ ያደረገ ቢሆንም ከላይ በጠቀስናቸው ውስብስብ ችግሮች፤ እንዲሁም የትብብርና የድጋፍ ማነስ ምክንያት የቴሌቪዥኑን የሳተላይት ስርጭት ለማስቀጠል እንደተቸገረ ሲያሳውቅ በክፍተኛ የቁጭት ስሜት መሆኑን ይገልጻል።

ድር ቢያብር፤ አንበሳ ያስር!
የአሥራት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ።
ግንቦት ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት።

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.