Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ፤

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ፤

የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን በተመለከት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ መግለጫ፤
*****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በአገራችን ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከመሰረቱ እንዲቀየር እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት እና አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚቀበለው አዲስ እና አካታች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመሰረት የሚሰራ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል። አብን የአማራን ሕዝብ በጨቋኝነት እና በጠላትነት የፈረጁ የፖለቲካ ቡድኖች እና ግለስቦች፥ «ጨቋኝ ብሔር መብት የለውም» በሚል መርኅ ላይ ተመስርተው እና የአማራን ሕዝብ «አከርካሪ ይሰብራል» ብለው ያቋቋሙትን ሕገ መንግሥት በጥገናዊ ለውጥ ለማስቀጠል የሚደረግን ማንኛውንም ሂደት እና ጥገናዊ ለውጥ የማይቀበል እና በጽኑ የሚታገለው መሆኑም ይታወቃል።

የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ይቋቋማል ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ፣ ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መደላድሎችን ሊፈጥር ይችል ይሆናል በሚል ተስፋ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የኮሚሽኑን መቋቋም በበጎ ሲመለከተው ቆይቷል። ንቅናቄያችን በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትን እና አገራችን ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿን ለከፍተኛ ፖለቲካዊ ቀውስ የዳረገውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለመቀየር ምቹ ሁኔታዎችን እና መደላድል ይፈጥራል፥ የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ያመላክታል ተብሎ እምነት የተጣለበት የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ምርጫ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ እና ሚዛናዊ ስብጥር ያለው፣ በሙያቸው እና በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ያለፈ ፖለቲካዊ ታሪካቸው ከጉድፍ ነፃ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መሆን አለባቸው ብሎ ያምናል።

ይሁንና የተቋቋመው የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ምርጫ፣ አባላቶች የተመረጡበት መመዘኛ ለሕዝብ ግልፅ ካለመደረጉም በላይ፥ የተመረጡት የኮሚሽኑ አባላት ስብጥር፣ ያልተመጣጣነ እና ሚዛናዊነት የጎደለው፤ ብዙዎቹ በኮሚሽኑ ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች የኋላ ታሪክ በአማራ ሕዝብ ኅሊና ውስጥ በበጎ የማይታወሱ፤ የአማራን ሕዝብ ለከፍተኛ ጥቃት የዳረገውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የቀረፁ እና ሥራ ላይ ያዋሉ፤ በእጃቸው ሥራ የአማራን ሕዝብ ኅልውና አደጋ ላይ የጣሉ እና ሕዝባችንን ኅልቆ መሳፍርት ለሌለው ግፍ የዳረገውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በመቅረፅ እና ሥራ ላይ በማዋል ሂደት ዋነኛ ተዋናዮች የነበሩ ግለሰቦች የተካተቱበት ኮሚሽን ሆኖ ስላገኝነው፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በኮሚሽኑ አባላት ስብስብ ላይ እምነት የሚጥልበት እና የአማራን ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሆኖ አላገኝውም። አብን ፣ አገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን በማያቋርጥ ግጭት ውስጥ የከተተውን ሥርዓት የፈጠሩት ግለሰቦች፣ ችግሩን ይፈታሉ የሚል እምነትም የለውም።

ስለሆነም መንግሥት የአስተዳደር እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ምርጫን ለሕዝብ ግልፅ በሚደረጉ መመዘኛዎች ላይ ተመስርቶ፣ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ እና ሚዛናዊ ስብጥር ያለው፣ በሙያቸው እና በስነ ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ያለፈ ፖለቲካዊ ታሪካቸው ባልጎደፈ ኢትዮጵያውያን እንደገና እንዲደራጅ ወይም የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲደረግበት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥሪውን ያቀርባል።

መንግሥት ጥሪያችንን ሳይቀበል ቀርቶ፥ ኮሚሽኑ ሥራውን አሁን በተመረጡት ግለሰቦች ላይ ብቻ ተመስርቶ የሚቀጥል ቢሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሂደቱን በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚከታተለው እና የኮሚሽኑ ውሳኔዎችም እውቅና ለመስጠት የሚቸገር መሆኑን በአፅንዖት እናስታውቃለን።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
ጥር 30፣2011 ዓ/ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.