Breaking News
Home / Amharic / የኢትዮጵያ ምሁራን የሃገር ኪሳራ ነን ወይ? ኪሳራ ነኝ ወይ?

የኢትዮጵያ ምሁራን የሃገር ኪሳራ ነን ወይ? ኪሳራ ነኝ ወይ?

የኢትዮጵያ ምሁራን የሃገር ኪሳራ ነን ወይ? ኪሳራ ነኝ ወይ?

ባለፉት አርባ አመታት አድገናል፣ አረንጓዴ አሻራና የወንድማማችነት ፓርክ፣ የዳቦቤት ተሰርቷል፣ ኅዳሴ ከመፍረስ ድኗል፣ ኮንዶሚኒይም፣ አውራጎዳና ተሰርቷል፣ ስንዴም ተዘርቷል የሚሉ እንዳሉ አልጠፋኝም። ነገር ግን አሁን፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን እያየ ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ የምትበለጽግ አገር ናት የሚል ምሁር ችግሩ ሌላ አካሉ ውስጥ ነው።

የሃገር ኪሳራ ነን ወይ?

በኢትዮጵያ አገራዊ ጉዳይ ውስጥ ያለን ምሁራን የኪሳራም ኪሳራ፥ ኣጥፊ ፍጡሮች ነን፡፡ ራሳችንም ባንሆን፣ የክፍል ጓደኞቻችን የነበሩ፣ አሁንም የምናውቃቸው አብረን ዲግሪ የተጫነልን ምሁራን፣ ወይ ሰርቀው፥ ወይ ቀምተው ያገኙትን የተቀመጡበትን ዙፋን ካልደፋን የሚሉ፥ በሙሉ ጉልበት የሚገዙትን ሃገር ካልበታተን ሰው ኣይደለንም! ብለው ሰላማዊ ሰው የሚጨፈጭፉ፥ የሚያፈናቅሉ፥ የድሃ ዛኔጋባ እላዩ ላይ የሚያፈርሱ  የምሁራን ጥርቅም በፈለገው መመዘኛ፣ ጋብቻችንም ቢሆኑ ዘመዶቻችን፣ ከኪሳራም በላይ አረመኔ ምሁራን ናቸው። በነፃነት ስም ቢነሱ በጭቆና፣ ሰላማዊ ሰው የሚያስጨፈጭፉ ምሁራን አራዊት ናቸው። ዝም አይባሉም።

ይህ አንዱ ፈርጅ ሲሆን፥ ሁለተኛው ከነዚህ ውጭ ያለውስ ምሁር ጤነኛ ነው ወይ ቢባል፥ እኛም ኢትዮጵያ-ኢትዮጵያ የምንል ምሁራን ብንሆን ከለቅሶና እርጥባን በስተቀር  ተባብረን ለአገሪቷ የፈጠርነው ቁም ነገር የለም፡፡ ቅን ትብብር የማይችል የምሁራን ክምችት ደግሞ ኪሳራ ነው፡፡ ኪሳራ ነኝ፥ ኪሳራ ነን! ከግል ጥቅማችን በቀር ያሳደግነው ነገር የለም፡፡

ማስረጃ? ሂድ ኣገርህን እይ! ኣሻራህን ፈልግ፡፡

ከዚህ መንደርደርያ ሃሳብ -ሃይፖቲሲስ- ላይ ተነስተን ምርምር ውስጥ መግባት ይቻላል። አንዳንድ የበሰሉ ምሁራን በጻፍዋቸው ውስጥ ጉዳዩን በጨረፍታ ነካክተውታል፡፡ ለምሳሌ ካነበብኳቸው፣ መሳይ ከበደ፣ ባሕሩ ዘውዴ፣ ገብሩ ታረቀ፣ አሰፋ ጫቦ፣ ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ ተሻለ ጥበቡ…ሌሎችም ጥናታዊ ጽሁፎች፣ ስነጽሁፍ ወዘተ….

ምርመሩን ማድረግ ቢፈለግ ግን ሃሳቡ ራሱ ከወዲሁ ራሱን ጠልፎ ይጥለዋል፡፡ ለምሳሌ፣

የምርምሩ ዉጤት ቢቀርብ ማነው የሚያዳምጠው? ኢትዮጵያዊ ምሁር ራሱን የመለወጥ፣ምክርና አዲስ እውቀት ገምግሞ፣ አገናዝቦ ቢሳሳት የራሱን ምልከታ ለመለወጥ ችሎታው አለው ወይ?  ለምሳሌ አንድ ጊዜ፣ ዳንኤል ካነማን (የኖቤል ሽልማት ያገኘ ተመራማሪ ሳይኮሎጅስት) ስለትምህርት/ስለመማር አንስቶ ያለውን፣  the ultimate outcome of an education is to change what you believe ብሏል ብል አንድ ምሁር አምርሮ ተናገረ። እሽ ይሁን፣ ግን ማስረጃውስ ቢባል፣ ማስረጃዉ ለብዙ አመታት ማስተማሩ ብቻ ነበር! ጥያቄና ማንነት ቢነጣጠል ምናለ?

በግሌም ምሳሌ አለኝ። ትምህርት ቤት አንድ ኮርስ ስንወስድ አዲስ አስተማሪ መጥቶ በስዊድን ደቡባዊ የላንቃ ድምፅ ትኩስ ገንፎ እንደዋጠ ሰው ሲጉተመተም ተማእኢው ሁሉ ከብዶት ተበሳጭቷል። ፕሮፌሰሩም ነገሩ ስለገባው ፊቱን ወደኔ አዙሮ፣ “ትከታተለኛለህ ወይስ ከብዶሃል?” ብሎ ጮክ ብሎ ሲጠይቅ፣ ዝም አልኩት። ውስጤ በንዴት ፈልቷል! ይኸ ምናምንቴ፣ ጥቁር ነው ብሎ ኮርሱ አይገባውም ብሎ አይደል ብዬ ሰአት ደርሶ እስክወርድበት ቸኩያለሁ። ጨርሶ ሲወጣ ያዝኩት፣ የሰማይ ስባሪ የሚያክል ሸበቶ ቫይኪንግ ነው። እሱ ለካስ ንዴቴ አልታየውም ገና ሳላናግረው እጁን ትከሻዬ ላይ አድርጎ ወደቢሮው ወሰደኝ። ከጠረጴዛው ላይ አንስቶ የሌክቸር ማስታወሻውን ሁሉ አንብበህ መልስ ብሎ ሰጠኝ! የሱ ስነልቦና በቅንንነት ለችግሬ መፍትሄ መፈለግ ሲሆን፣ የኔ የኩሩው ኢትዮጵያዊ ልቦና ነፃነቴ ተነካብኝ! እሱ ማን ሆኖ! ነበር።

እኛ ጥያቄውን ያነሳን ምሁራን የመልለወጥ ባሕል ቢኖረን ኖሮ ይኸ ጥያቄ ባልተነሳ ነበር፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ የሚመላሱትን ” እኔ አውቃለሁ፣ አንተ ምን ታውቃለህ? ”  “አንተ ዝም በል፣ እኔ ላስተምር!” እየተባባልን ካለማስረጃ፣ ሃሳባችንን እንኳን በጥያቄ መልክ ከማቅረብ ድፍን አድርገን ” አላልኳችሁም፥ 100% እርግጥኛ ነኝ ብላችሁ አትሰሙኝም!” የሚልን ምሁር ምርምር አይመልሰውም፣ አይቀልሰውም።

ማስረጃ? ይኸው ብዙ ሺህ ምሁራን የአገራችንን ኢትዮጵያን ሕልውና በሚመለከት፣ የወያኔና የኦነግን ኣረመኔነት እያወቅን፣ ትምህርት ሳያንሰን፣ አንድ አቋም እያለን እስካሁን በተግባር አቅማችንን ማሳየት አልቻልንም! 

አስቲ ተጠይየቅ! እርግጠኛ ሆነህ የጻፍከውን አንድ ሃሳብ አዉጣና፣ “ይኸ የማይረባ ስህተት የሞላበት ግባሶ ጽሁፍ ነው!” ብለህ ከራስህ ጋር ተፋጠጥ! ትችላለህ? እስቲ የዚህ ተቃራኒ ሃሳብ እንዳለ ልፈልግ ብለህ ተነስተህ ታውቃለህ?  እንድያው ልክ ባልሆንስ? የሚል ትንሽ ጥርጣሬ ውል ብሎብህ ያውቃል? ካልቻልክ፣ እንግዲያው ባይገርምህ፣ በአንፃር ያንተን ሃሳብ ተቃርኖ፣ ባንተው ትምህርት ካንተው ልክ በራሱ እውቀት እምነት የሚያቀርብ ሌላም አለ። የሚለያችሁ መረጃ ነው፡፡ መረጃም ቢሆን ጊዜውን ጠብቆ ሊቀየር ይችላል፡፡ ሁለታችሁም ትክክል፣ ሁለታችሁም ስኅተት ልትሆኑም ትችላላችሁ!

ስለዚህ ያለን አማራጭ ማዳመጥ፥ ኣቋምን፣ እምነትን መመርመር፣ መማር ነው። ቅንነት፥ ሃሳብን ከማንነት መለየት፥ ለጥያቄያችን መፍትሔ እንጅ ደጋፊ አለማሳደድ፣ መከባበር፣ እንደዚህ አይነቱ ትብብር ያዳብራል፡፡ በሃሳብ ደረጃ ሁሉም ይኸን ያውቃል።

ትልልቆቹን የጽንሰ ሃሳብ ልይነቶችን፣ የፍልስፍና ልዩነቶችን የፈጠራቸው፣ ወይ እውነትን ፍለጋ ሲመራመሩ ወይም የሰው ልጅ ሳይበዳደል አብሮ ማደግ የሚችልበትን መንገድ ፍለጋ ነው ይባላል። ዲሞክራሲውም ኃይማኖቱም የዚያ ውጤት ነው፡፡ ያም ሆኖ፣ በቅንነትም ቢኬድ አንድ አስማሚ መፍትሄ ብቻ አለመኖሩ ራሱ የሰው ልጅ የፈጠራ ችሎታው ስፋት ውበትና የስነልቦናው ውቅር መለያየት ነው፡፡ ብሎም ሁሉም የተያያዘ ስለሆነ፣ ወደድንም ጠላንም አንዳችን በሌላችን እቅፍ ውስጥ ነን።

(በቅንፍ፣ አንድ የገረመኝን ምሳሌ ላንሳ፡፡ መቸስ ኤምፓቲን -ርሕራኄን- የሚጠላ ሰው ጤነኛ ሰው አይመስለንም፡፡ ነገር ግን አንድ ታዋቂ ሳይኮሎጅስት ” ፀረ-ኤምፓቲ ” የሚል ግሩም መጽሀፍ ጽፎ በምሁር ጉድ ተብሏል – በጉጉት እንዳላንጠለጥላችሁ፣ የ ፖል ብሉም የ 2016 መጽሃፍ በድፍኑ ፀረ-ርኅራኄ ሳይሆን፣ ፍሬነገሩ  “ርኅራኄ ወደ ደግነት -ኮምፓሽን- በተግባር ካልተለወጠ፣ እድገትን ይገታል፣ አቋምን/ፍርድን ያጣምማል” ለማለት ነው።)

ስለዚህ ሁለቱም የከፈትኳቸው ፋይሎች ምክንያታቸው ትምህርት ሳይሆን ትምህርት የማይቀይረው የስነ-ልቦና ችግር ፥ ከራስ መጣላት ይሆን ይሆን እላለሁ? ይህ ከሆነ ደግሞ ማነፃፀርያችን ምን ይሁን? ብንል መሬት ወደረገጠው፣ አለንልህ እያልን ራሳችንን ወደምናጭበረብርበት ወደ ገበሬ አጎታችን ይመራናል።

በኣስኳላ ካልተማሩት ኢትዮጵያውያን የባላገር ድሃ ወገኖቻችን ስነልቦና ጋር ስንወዳደር፣ እነሱን ፃድቃን ማድረጌ ሳይሆን፣ የኛን  hyphenatedEthiopians የተበላሸ ትውልድ በምሳሌ ማየት ይቻላል።  

በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል፣ ምስራቅ-ምዕራብ፣ ሰሜን-ደቡብ፣ ያልተበከለውን ሰላማዊ ገበሬ የቀን ተቀን ኑሮ ብናይ ፥ የማያስቀናው የድህነት ኑሮው፥ ሳይንስ የደረሰባቸውን አይን ከፋች እውቀቶች እንኳን ሳይቋደስ የስነልቦና ጥንካሬና ኩራት አለው። (የኤግዞቲክ ኖስታልጅያ ዝባዝንኬ ኣይደለም፥ 
እሱን ለፈረንጁ ተውለት!) አንዳንዶቻችሁ ፈረንጆች ይህንን ኩራቱን እንደ ድክመት ታዩታላችሁ፡፡ ይህ ስለናንተ የነፃነት አረዳድ ያሳብቃል እንጅ ስለሱ ሁዋላቀርነት አይናገርም።

የአገሬ ረሃብተኛ ገበሬ እኮ ኩርማን እንጀራ ዘርግቶ ማዕድ ሲቀርብ “ተመስግን አምላኬ!” የሚለው፣ የፈላስፋዉን ንጉስ የአፄ ማርከስ ኦሬሊየስን “ሱባኤ” አንብቦ ወይም የሕንዶቹን ሱትራ አነብንቦ አይደለም፤ በባሕሉ የወረሰው እሴት ስለሆነ ነው እንጅ! እኔና አንተ ግን፣ ከአባቶቻችን ተገንጥለን፣ መጽሐፍት ሸምደደን ዲግሪ ተሸክመን፣ በችግር ውስጥ ምስጋና፣ በጥጋብ ውስጥ ፀሎት፣ በጉልበት ጊዜ ርኅራኄ፣ በዕውቀት ውስጥ ሱባኤ፣ በድል ውስጥ ይቅርታ… አልገባንም።

ስለዚህ ራሳችንን ለመለወጥ፣ ከኢጎአችን ፈቀቅ ብለን ለመተባበር ካላቀድን ጥያቄውን ማብጠልጠል ምን ፋይዳ አለው? መፍትሔ በተግባር በትብብር መፈለግ ጉዞ ላይ ካልሆንን፣ በትምህርታችን ሕዝብን ከእልቂት ካላዳንን ሙሾ ለማውረድ መቀባበል ለኛ እንጅ ለሟች ምን ይጠቅማል? //

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.