Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሰራዊት የተሰጠ መግለጫ።

ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሰራዊት የተሰጠ መግለጫ።

ከአማራ ፋኖ ህዝባዊ ሠራዊት የተሰጠ መግለጫ
መጋቢት 7, 2016 ዓ ም
አማራ፣ ኢትዮጵያ።
የተከበርከውና በህልውና ተጋድሎ ላይ ያለኸው የአማራ ሕዝብ

በህልውና ትግል ላይ ከሚገኘው የአማራ ሕዝብ በመንፈስ ለአፍታም ቢሆን ያልተለየኸው የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ!
መነሻው አማራ፣ መዳረሻው ኢትዮጵያ የሆነው የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የተመሠረተው፣ ባለፉት ዓመታት ብዙዎቹ የሃገራችን የፖለቲካ መሪዎች በዘረኛው የኦህዴድና በተንበርካኪው ብአዴን ላይ ቀቢፀ ተስፋ መጣላቸው ሥህተት ነው ብለው በቆራጥነት በታገሉ ታማኝ የሕዝብ ልጆች መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚከታተሉ ሁሉ የተሠወረ ባለመሆኑ፣ ግንባሩ በተመሠረተ ማግሥት መንግሥታዊ የጅምላ ዘር ፍጅት እየተፈጸመበት የሚገኘው የአማራ ሕዝብም ሆነ ከጎኑ የቆሙ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ አጋሮቹ ላቅ ያለ ድጋፍ ችረውታል።
በዚህ አውድ ውስጥ ሆኖ ግንባሩ ያሰባሰበው ገንዘብ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበ ቢሆንም፣ ግንባሩ ወደትግል ሜዳ ይዞ የገባው ትልቁ ዕሴት ገንዘብ አልነበረም። ትልቁ አቅሙ በአማራም ሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ያለው የፖለቲካ ተቀባይነትና ታማኝነት፣ እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ለአማራው ትግል የሚመጥን የፋኖ አደረጃጀት ሆኖ መገኘቱ ነበር።
ይህ የግንባሩ ቁመና ከተለያዩ አቅጣጫዎች ለተለያዩ ዓላማዎች የተሰለፉ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ዋና ዒላማ እንዲሆን አድርጎታል። ከእነዚህ መካከል ቀዳሚ ሆነው ብቅ ያሉት ሁለት ተዋናዮች ሲሆኑ፣ እነሱም፣ በአንድ በኩል፣ በንፁሃን ደም የሰከረው መንግሥታዊው ኅይል ሲሆን፣ በሌላ በኩል፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር ሆነው ገንዘብ ማምታታትን እንደቋሚ ሥራ የያዙ እና በግንባሩ ምሥረታ የገንዘብ ምንጫቸው አደጋ ላይ የወደቀ የመሰላቸው “የደም ነጋዴዎች” ነበሩ።
እነዚህ ሁለት ኅይሎች ተቀናጅተውም ሆነ ተናበው ላለፉት ወራት ባካሄዱት ርብርቦሽ፣ ግንባሩን የፖለቲካ ተቀባይነት ለማሳጣትና የገንዘብ አቅሙን ለመናድ አብዝተው የባዘኑ ቢሆንም፣ ግንባሩ በአራቱም የአማራ ጠቅላይ ግዛቶች (በወሎ፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በጎንደር) አሻራውን በተግባር ለማሳረፍ የቻለ አማራዊ ቁመና ያለው የፋኖ አደረጃጀት ለመሆን በቅቷል።
በዚህ ሂደት፣ ይህን አማራዊ ቁመናውን በአራቱም ጠቅላይ ግዛቶች ብቻ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያና በውጭ ዓለምም በሰፊ መሠረት ላይ ለመጣል ከአጋር የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር ሆኖ “የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሠራዊት” ወደሚለው አዲስ አደረጃጀት ማሳደጉን እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር ኦክቶበር 29, 2023 ዓ.ም. በዋሺንግተን ዲሲ በተደረገ ስብሰባ ከመላው አሜሪካ የተውጣጡ አንድ ሺህ ተሳታፊዎች በተገኙበት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ከእነዚህ አጋር የፋኖ አደረጃጀቶች መካከል አንዳንዶቹ ሃሳባቸውን የቀየሩ ቢሆንም፣ ሃሳባቸውን በቀየሩት ላይ ምንም ቂምና ቅሬታ ሳንይዝ፣ የአማራ ሕዝባዊ ግንባርን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትን ያቀፉ የፋኖ ብርጌዶችና ክፍለ-ጦሮች በቃላችን ፀንተን እንገኛለን።
በዚህም መሠረት፣ “የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሠራዊት የዓለም አቀፍ ድጋፍ ግብረሃይል” የተመሠረተ ሲሆን፣ ግብረሃይሉ ከዚህ በፊት በመላው ዓለም የተቋቋሙትን የአማራ ሕዝባዊ ግንባር የድጋፍ ቻፕተሮች ከእነአመራራቸውና ሙሉ ቁመናቸው ጠቅልሎ የሕዝባዊ ሠራዊቱን የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲና የፋይናንስ ሥራዎች በላቀ ብቃትና አቅም እንዲሠራ ተልዕኮ ተሠጥቶታል።
በዚህ መሠረት፥
1ኛ/ ዶ/ር አምሳሉ አስናቀ – ሰብሳቢ፣
2ኛ/ አቶ ሙሉጌታ አያሌው – ምክትል ሰብሳቢ፣
3ኛ/ ልዑል ዶ/ር አስፋው ወሰን አሥራተ ካሳ – የዲፕሎማሲ ዘርፍ ኅላፊ ተደርገው የተሰየሙ ሲሆን፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሙሉ ትብብራቸውን እንዲያደርጉላቸው አደራ እንላለን።
በዚህ አጋጣሚ፣ በሃሰት የተፈጸመብንን የስም ማጥፋት ዘመቻ ሁሉ በጨዋ ቋንቋ ተመጣጣኝ ምላሽ መስጠት እንችል የነበረ ቢሆንም፣ እየተጎዳንም ቢሆን ለአማራና ለፋኖ አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ሁሉን መቻላችንን ሕዝቡ እንዲያውቅልን እንሻለን። ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ሙሉ ትኩረታችን በፈጣሪ ፈቃድ በድል ለማጠናቀቅ ቆርጠን በተነሳነው የህልውና ትግል ላይ ይሆናል።
መነሻችን አማራ፣
መዳረሻችን ኢትዮጵያ!!
ክብር ለአማራ ህልውና ሲታገሉ ለተሰውት ፋኖ ሰማዕታት!!
የፈጣሪ ጥበቃ ኢትዮጵያን አይለያት!!
እስክንድር ነጋ፣ ከትግል ሜዳ!!

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.