Breaking News
Home / Amharic / የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ቃለ-ምልልስ

የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ቃለ-ምልልስ

በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ የተመሰረተው አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ለሪፖርተር ጋዜጣ የሰጡት ቃለ-ምልልስ፦

‹ሕዝባዊና ግዛታዊ አንድነቱ በመገሰሱ ምክንያት የአማራ ሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ነው ብለን እናምናለን›› አቶ ክርስቲያን ታደለ፣

አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

በቅርቡ የመመሥረቻ ጉባዔውን ያካሄደው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ በይፋ መመሥረቱ ለደጋፊዎቹና ለአባላቱ ግልጽ አድርጓል፡፡ ከሳምንት በፊት በአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ መመሥረቱን ይፋ ያደረገው ፓርቲው በሙሉ ዓለም የባህል አዳራሽ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ መግባቱን ገልጿል፡፡ ፓርቲው በዋናነት ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት በተወጣጡ ምሁራን የተመሠረተ ሲሆን፣ ከሳምንት በፊት በነበረው ስብሰባም ደሳለኝ ጫኔን (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ በቀጣዩ ዘመን የአማራው ፓርቲ ነኝ ብሎ ያወጀው አብን በቅርቡ የፓርቲውን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት እንደሻው የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጀመርያ ስለፓርቲያችሁ አመሠራረት ይንገሩን?

አቶ ክርስቲያን፡- ስለአመሠራረታችን ስናወራ በመጀመርያ ድርጅቱ ወደ ህልውና ወይም ምሥረታ ለመምጣት ምክንያት የሆኑ ዓብይ ጉዳዮችን ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አማራው በዋናነት የህልውና ፈተና ውስጥ ወድቋል ብለን ስለምናምን ነው ይህን ድርጅት የመሠረትነው፡፡ አማራው የህልውና ፈተና ውስጥ ወድቋል ስንልም የተለያዩ መገለጫዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ትልቁና የመጀመርያው ጉዳይ ላለፉት ዓመታት አማራው ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ባቀናት አገር እንደ መጤ እየተቆጠ ሲገፋ፣ ሲሰደድ፣ ሲፈናቀልና የተለያዩ በደሎች ሲደርስበት ነበር፡፡ ከምንም በላይ ይኼ ሁሉ ችግሮች የሚመነጨው ከሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥቱ ከወከለው ሥርዓት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የተዋቀረው አማራ ጠላታችን ነው ብለው በሚያምኑ ብሔርተኛ ፖለቲከኞች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ሰፊ የሆኑ አሠራሮችና ድንጋጌዎች በሙሉ አማራውን ያገለሉ፣ አማራውን በሥልታዊ መንገድ ከተጠቃሚነት፣ ሁሉን አቀፍ ተሳታፊነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ያገለሉ ናቸው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አማራው አማራዊ ማንነቱ፣ ባህሉ፣ መገለጫዎቹ ከመልማት ይልቅ እንደ መጥፎ ምሳሌ እየተነሱ ዘለፋ ሲደርስበት፣ ባህሉ ሲሸረሸር፣ እንደ ሕዝብ አማራ ሕዝባዊና ግዛታዊ አንድነቱ በመገሰሱ ምክንያት የአማራ ሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ነው ብለን እናምናለን፡፡

አገሪቱ የፌዴራል መዋቅር እየተከተለች ቢሆንም ፌዴራላዊ ሥርዓቱ አማራውን ያገለለና የሚያጠቃ በመሆኑ ምክንያት፣ አማራ እንደ ሕዝብ እየተከፋፈለ በየቦታው ተሸንሽኖ ይገኛል፡፡ የማንቱ ዋነኛ አስኳልና መገለጫ የሆነው ርስተ ምድሩም ተቆራርጦ በተለያዩ ክልላዊ መስተዳድሮችና አካላት ሥር ይገኛል፡፡ ስለዚህ እንደ ድርጅት ይኼን ለማስጠበቅና ለማስከበር እንሠራለን፡፡ ሌላው እንደ ሕዝብ አማራው በአገሩ ልማት ላይ የሚኖረውን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ዓላማ አንግበናል፡፡ እስካሁን በነበረው የአማራው ወጣት ከተማ፣ ገጠር፣ ምሁር ብለን ነጣጥለን ብናይ አማራ ስለሆነ ብቻ በሥርዓቱ እየተገፋ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ይኼ ደግሞ አማራው በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ማንነቱ ተከብሮና ተጠብቆለት ሀብትና ንብረት እንዲያፈራ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ስንል ፓርቲያችንን መሥርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲውን ለመመሥረት ሐሳቡ እንዴት ተጠነሰሰ?

አቶ ክርስቲያን፡- ፓርቲውን ለመመሥረት እንግዲህ በእኛ አነጋገር ከታላቁ የአማራ ሰማዕት ከፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ በኋላ በዋነኛነት አገር ውስጥ የአማራ፣ በአማራ፣ ለአማራ የሆነ ፓርቲ አልነበረም፡፡ አንድም ይህን ፓርቲ ለመመሥረት ምክንያት የሆነን አማራን የሚወክል፣ በአማራ በልጆቹ የሚመራ፣ ለአማራ የቆመ ፓርቲ ባለመኖሩ ነው ወደዚህ የመጣነው፡፡ ይኼን ሁሉ መጋፋት፣ ይኼን ሁሉ በደል፣ ዘር ማጥራትና ግፍ እያየን ሥርዓቱ በሒደት ያስተካክላል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን ሥርዓቱ በማስተካከል ፈንታ እየባሰበት ስለሄደ፣ በሐሳብ ደረጃ ቢያንስ ይኼን ድርጅት ይዘን መንቀሳቀስ ከጀመርን ዓመት ሆኖናል፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል ውስጥ ለውስጥ ስለዚህ ፓርቲ በዓላማው ዙሪያ በማስረዳት፣ ምን መምሰል አለበት የሚለውን በመነጋገር፣ ለፓርቲው ህልውና ይጠቅማል በምንላቸው ሐሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያ ሕዝባችንን በተናጠል ስናማክር ቆይተን ነው በመጨረሻ እዚህ የደረስነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቂት ወራት በፊት አሁን በፓርቲው የተመረጡ አመራሮችን ጨምሮ አባላቶቻችሁ ታስረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ምን ነበር የተፈጠረው?

አቶ ክርስቲያን፡- አንድም የፓርቲው ምሥረታ የዘገየበት ምክንያት ይኼው ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ባህር ዳር መሥራች ጉባዔውን ለማመቻቸትና ምክክር ለማድረግ የፓርቲው የአሁን አመራሮችና አባላት ውይይት አድርገው ጨርሰው ለምግብ በተሰበሰቡበት ሰዓት ለእስር ተዳርገው ነበር፡፡ የአማራ ሕዝብ ይኼን ሁሉ በንቃትና በጥንቃቄ ይከታተል ነበር፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ያለውን ስሜት በመረዳት በወቅቱ ኮማንድ ፖስቱ ሊፈታቸው ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- የፓርቲያችሁ ምልክት የንስር ምሥል ነው፡፡ ምን ለማመልከት ነው?

አቶ ክርስቲያን፡- ንስርን እንደ ምልክት መገለጫነት መጠቀም የቆየ የአባቶቻችን ታሪክ ነው፡፡ አንዳንዶች ከሃይማኖት ጋር የሚያያዙት አሉ፡፡ ነገር ግን እኛ በዋናነት የንስርና የአማራ ተፈጥራዊ ባህሪ መመሳሰል አለው ብለን ስለምናምን ነው፡፡ አማራ ችግር ሲያጋጥመው በችግሩ ከመቆዘም ይልቅ፣ ችግሩን ለመፍታት ከፍ ብሎ መብረር የሚችል ባህሪ ወይም ግብር አለው፡፡ የአማራው ግብር እሱ ነው፡፡ እኛ አማራነት የሰውነት ውኃ ልክ ነው ብለን እናምናለን፡፡ አማራ የሌላውን አይፈልግም፡፡ የሚገባውን ደግሞ ያለ ፈቃዱ መስጠት አይፈልግም፡፡ ነገር ግን በፈቃዱ ማጋራት ይችላል፡፡ ንስር ኩሩ ወፍ ነው፡፡ ከአዕዋፍ ዘር ሁሉ የራሱን ማስነካት አይፈልግም የሌላውንም አይነካም፡፡ ንስር መብረቅ፣ ዝናብ አይመታውም፡፡ ከመብረቅም፣ ከዝናብም በላይ ነው፡፡ የመንፈስ ከፍታ ወካይ ነው፡፡ እናም ምልክቱ የአማራውን የሞራል ልዕልና በትክክል ሊገልጽለት የሚችል ወካይ ነው፡፡ በተጨማሪም ንስር የመታደስና የትንሳዔ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህም አማራው ለዘመናት ከደረሰበት ግፍና ሰቆቃ እንደ አዲስ ዳግመኛ ላይወድቅ ይነሳል የሚለውንም ያሳያል፡፡ መሪ ቃላችን አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል ነው፡፡ ይኼንንም ስንል አማራው ወደ ነበረበት የመንፈስ ከፍታ ይመለሳል የሚለውን ለማስመር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ንስርን እንደ ምልክት ከመጠቀም በተጨማሪ ንስሩ ባለ ሁለት ራስ ነው፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ክርስቲያን፡- ለምሳሌ የሰው ልጅ በአንዴ 180 ዲግሪ ብቻ ነው ማየት የሚችለው፡፡ ንስር ደግሞ 340 ዲግሪ ነው፡፡ ሁለት ሲሆን 680 ዲግሪ ይሆናል፡፡ ወደ ምልከታው ስንሄድ ዙሪያ መለስ የሆነ፣ ራዕይ ያለው፣ ንቁነት፣ በጥልቀት መመርመር፣ ዝግጁነትን ለመግለጽና ችግሩ ውስጣዊና ውጫዊ ይዘት ያለው መሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው እንደ ፓርቲ ሕዝቡን ወክላችሁ በዓላማ ደረጃ መጨረሻ ላይ እናሳካዋለን ብላችሁ ያስቀመጣችሁት ግብ ምንድነው?

አቶ ክርስቲያን፡- በተለይም ከማንነትና ከግዛት ጋር በተያያዘ እንዳልኩህ አማራው የጥቃት ሰለባ የሆነው በሕገ መንግሥቱ ምክንያት ነው፡፡ ሲጀመርም ሕገ መንግሥቱ ሲዘጋጅ አማራው እንደ ሕዝብ አልተወከለም፡፡ ስለዚህም ሥልጣን ላይ ካለው ሥርዓት ጋር በሰላማዊ መንገድ ሕገ መንግሥቱ እንደ አዲስ ድርድር እንዲደረግበትና እንዲሻሻል እንታገላለን፡፡ እንደ አዲስ ድርድር ተደርጎበት የአማራውን ዘላቂ ጥቅሞች፣ ፍላጎቶችና መብቶች ሊያስከብር የሚችል እንዲሆንና በሚገባንን የማስከበር ሥራ እናከናውናለን፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ታሪካዊ የአማራ ግዛቶቹና ርስቱ ሊመለሱለት ይገባል፡፡ እነዚህ ግዛቶች ብቻ ሳይሆኑ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ ወደ ቀደመ ማንነቱ መመለስ አለበት፡፡

በሌላ በኩል አማራው በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተሰራጭቶ ይኖራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ አማሮች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ አልተፈቀደላቸውም፡፡ መንግሥት በሚያምነው እንኳን ወደ 15 ሚሊዮን አማሮች አሁን ካለው የአማራ ክልል ውጪ ቢኖሩም ውክልና ግን አላገኙም፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ መሬቱም፣ ሕዝቡም በአብዛኛው የአማራና አማራ ቢሆንም አዲስ አበባ የፌዴሬሽን ውክልና እንኳን የለውም፡፡ በተመሳሳይ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በደቡብና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች ብዙ አማሮች ቢኖሩም በተመሳሳይ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት የላቸውም፡፡

ስለዚህ ፓርቲያችን የአማራ ሕዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ ባህላቸውን የማበልፀግ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበርና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ይታገላል ይደራደራል፡፡ ሌላው አሁን ክልሉ በኢኮኖሚ የተነጠለና በመሠረት ልማት ከሁሉም ጭራ የሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ፍትሐዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖርና ያለው ፀጋ የሚለማበት አሠራር እንዲፈጠር እንታገላለን፡፡ ሥልጣን የምንይዝ ከሆነም ለዚህ መረጋገጥ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከግዛት ጋር በተያያዘ የአማራ ክልል ግዛት የምትሉት የቱን የቱን ነው? ቅድም የጠቀሷቸው በተለይ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ አማራ የሆኑ ዜጎች እንዴት መወከል አለባቸው ነው የምትሉት?

አቶ ክርስቲያን፡- እዚህ ላይ ግልጽ እንዲሆንልን የምንፈልገው ነገር አለ፡፡ እኛ ነባራዊና ታሪካዊ ይዞታዎች ውስጥ የሚኖረው ሕዝቡም መሬቱም የአማራ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ይኼ በውክልና የሚፈታ አይደለም፡፡ ከዋናው አማራ ጋር ወደ ቀደመው ይዞታና ማንነቱ መመለስ አለበት፡፡ ይኼ ለድርድርም የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይኼ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አማሮች አሉ፡፡ ይህም ሲሆን የትም እንደሚደረገው እነሱ ውክልና የሚያገኙበት ሁኔታ ሊፈጠር ይገባል፡፡ በየቦታው ባለው የሥልጣን ተዋረድ መወከል አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ እንደ ፓርቲ የትኞቹን ግዛቶች ወይም ቦታዎች ነው ለአማራ ክልል ነው የሚገቡት የምትሉት?

አቶ ክርስቲያን፡- በመሠረታዊነት እገሌ ወይም እገሌ ይገባናል ከማለታችን በፊት በሀቅ ላይ የተመሠረቱ ጥናቶችን ማድረግ እንፈልጋለን፡፡ ከጥናት በተጨማሪም ከሕዝቡ ጋር እንወያያላን፡፡ እንዲሁም ታሪካዊ ሰነዶችን እናገላብጣለን፣ እናጣቅሳለን፡፡ ይኼን ካየንና ሰነዶችን ካላገላበጥን በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ውጤቱን በቅርብ ይፋ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው የአማራ ክልል መዋቀር ወይም መካለል ሲገባቸው ሌላ ሥፍራ የተካለሉ ቦታዎች አሉ ነው የምትሉት?

አቶ ክርስቲያን፡- አዎ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ክርስቲያን፡- አሁን ከላይ እንዳልኩህ እገሌ እገሌ እያልን መናገር አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ጥናታችንን ስናጠናቅቅ እናሳውቃለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፓርቲያችሁ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ምንድነው?

አቶ ክርስቲያን፡- እኛ እንግዲህ የህልውና ፈተና ውስጥ ላለ ሕዝብ የርዕዮተ ዓለም ጥያቄ የቅንጦት ነው ብለን የምናምነው፡፡ ለእኛ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች የቅንጦት ናቸው፡፡ ያ ማለት ግን እንዲሁ በደመነፍስ እንንቀሳቀሳለን ማለት አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት የምንከተለው መስመር ዓለማዊ ዕይታው ከአማራ ሕዝብ ነባራዊ ማንነት፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና ዓለምን የሚቃኝበት ዘዬ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተነስተን ነው የርዕዮተ ዓለም መስመራችንን የወሰድነው፡፡ አማራ እንደ ሕዝብ በግለሰብ ነፃነት የሚያምን ሕዝብ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ሕዝቡ አሁን እየደረሰበት ያለው በደል ደግሞ በቡድን ደረጃ የሆነ ነው፡፡ እንደ ግለሰብ ሳይሆን አማራ ስለሆነ ብቻ የሚፈናቀል ሕዝብ አለ፡፡ ይህ ችግር ደግሞ መሪ ቢቀያየርም፣ እንዲሁም ሥርዓቱ ቢቀየርም መቀረፍ አልቻለም፡፡ ምንም እንኳን አሁን አሁን መልካም የሚመስሉ ብልጭታዎችን እያየን ቢሆንም ችግሮቹ አሁኝም ድረስ አሉ፡፡

ስለዚህ አማራ እንደ ቡድን ጠንካራ የሆነ ማኅበራዊ ትስስር ስላለው ቡድናዊ መብቶችን የሚያስጠብቅ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ፓርቲያችን የሚከተለው መስመር ሁለቱንም ማለትም ግላዊና ቡድናዊ መብቶችን ማስከበርና ማጣጣም የሚችል ነው፡፡ ከዚህም ተነስተን ሁለቱን የሚመጣጠን ሆኖ ያገኘነውን ለዘብተኛ ሊብራሊዝምን መከተል ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ የርዕዮተ ዓለም መስመር ለዘብተኛ ሊብራሊዝም ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፓርቲያችሁ መመሥረት ይፋ ከሆነ በኋላ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያው የተለያዩ ቡድኖች ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡ ወደ ፊት ከሌሎች ሐሳባችሁን ከሚደግፉ ቡድኖች ጋር አብራችሁ ለመሥራት ያሰባችሁት ነገር አለ ወይ? በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚታወቁ አንዳንድ ቡድኖች ጋር በምልክት የመመሳሰል ነገር አላችሁ?

አቶ ክርስቲያን፡- ንስር የትውልዱና የዚህ ዘመን አማራዊ ትውልድ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ፓርቲ ቢመሠረት የዲዛይን ለውጥ ካልሆነ በስተቀር ንስርን ይዞ መገኘቱና ተመሳሳይነት መፈጠሩ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ከግንኙነትና አብሮ ከመሥራት ጋር በተያያዘ በመርህ ደረጃ አንዱ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ የሚል አቋም አለን፡፡ እናም ከድርጅታችን ፕሮግራምና መተዳዳሪያ ደንብ ጋር እስከተጣጣመ ድረስ የአማራ በሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ላይ አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ከሁለት ዓመታት በኋላ ጠቅላላ ምርጫ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በቀጣይ ዕቅዳችሁ ምንድነው?

አቶ ክርስቲያን፡- እንግዲህ የመጀመርያ የሚሆነው ፓርቲያችን ተመሥርቷል ብለን ከምርጫ ቦርድ ዕውቅና ለማግኘት የመመሥረቻ ስብሰባችንን ካደረግን በኋላ፣ አስፈላጊውን ዕውቅና ለማግኘት ሰነዶችን ለምርጫ ቦርድ ልከናል፡፡ ከዚህ በመቀጠል ትልቁ ሥራችን የሚሆነው አደረጃጀቶችን መፍጠር ነው፡፡ እኛ ራሳችንን እንደ አገራዊ ፓርቲ ነው የምንቆጥረው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው የአማራ ክልልና አማሮች አሉበት በሚባሉ የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አደረጃጀቶችን ለመፍጠር እንሠራለን፡፡ ከሕዝባችን ጋር ወሳኝ በሚባሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖረን እንነጋገራለን፡፡ በተጨማሪም የሕዝቦችን ዘላቂ ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅ ከሚመለከተው አካል ጋር ድርድሮችን እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ በምርጫ እንሳተፋለን፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ከያዝንም ሕዝባችንን ተጠቃሚ ለማድረግ ጠንክረን እንሠራለን፡፡

Check Also

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

በአሜሪካን ሀገር የምትኖሩ የአማራ ማህበራትና የአማራ ልጆች የት ነው ያላችሁት?? Share!

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.