Breaking News
Home / Amharic / በአማራ ክልል የዳቦ ዱቄትን ላልተገባ ጥቅም ባዋሉ ከ600 ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ::

በአማራ ክልል የዳቦ ዱቄትን ላልተገባ ጥቅም ባዋሉ ከ600 ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ::

፨፨፨
(የአማራ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ 14/2011፣ ባህር ዳር) መንግስት በድጎማ እያቀረበ ያለውን የዳቦ ዱቄት ላልተገባ ጥቅም ባዋሉ ከ600 በሚበልጡ ዳቦ አምራቾች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ተሻሽሎ በተዘጋጀው የስንዴ፣ የዱቄትና የዳቦ ስርጭት ማስፈፀሚያ መመሪያ ላይ ከባህር ዳር ዳቦ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት ተካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርቡ 2 ሺህ 728 ዳቦ ጋጋሪዎች ይገኛሉ።

በየወሩ በድጎማ ከሚቀርበው 26ሺህ ኩንታል የዳቦ ዱቄት 60 በመቶ የሚሆነው ለዳቦ አምራቾች በትስስር እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

ቀሪው 40 በመቶ የሚሆነው የዳቦ ዱቄት ደግሞ ለመንግስት ሠራተኛው በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚሰራጭ ነው የገለጹት።

በተደረገ ጥናትና ክተትል ለዳቦ አምራቾች ከሚሰራጨው ዱቄት ከ50 በመቶ የሚበልጠው በህገወጥ መንገድ አየር በአየር ይሸጣል።

የተጋገረው ዳቦም ለተጠቃሚው ሳይደርስ ለንግድ ድርጅቶች እንደሚሸጥ መረጋገጡን ነው ያመለከቱት።

“ለተጠቃሚዎች የሚቀርበው የአንድ ዳቦ መጠንም 150 ግራም መሆን ሲገባው አንዳንድ ዳቦ አምራቾች እስከ 85 ግራም ቀንሰው እንደሚያቀርቡም ተደርሶባቸዋል” ብለዋል።

ጥናቱን መሰረት በማድረግም ከ600 በሚበልጡ ዳቦ አምራቾች ላይ እርምጃ በመውሰድ ከመንግስት የዳቦ ዱቄት አንዳያገኙ መደረጉን አስታውቀዋል።

ከባህር ዳር ከተማ የመጡት ተሳታፊ አቶ ግዛው ታደሰ በበኩላቸው በዳቦ ማምረት ስራ ፈቃድ ወስደው ከተደራጁ አንድ ዓመት እንደሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁንም ለአራት ጊዜ ብቻ ከስምንት እስከ 11 ኩንታል የዳቦ ዱቄት በትስስር ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ይህም አቅርቦቱ ወጥነት የሌለውና ከህዝቡ ቁጥር ጋር እንደማይመጣጣን ተናግረዋል።

በትስስር የተሰጣቸውን የዳቦ ዱቄትም እስካሁን ለተጠቃሚዎች በማድረስ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ መሆኑን አስረድተዋል።

“በመንግስት ድጎማ ለዝቅተኛ ነዋሪው ህዝብ የሚቀርበውን የዳቦ ዱቄት ላልተገባ ጥቅም በሚያውሉ ግለሰቦች ላይ በመንግስት የተወሰደው እርምጃም በቀጣይ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።

የባህር ዳር ከተማ ዳቦ አምራቾች ዘርፍ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ተስፋዬ ደጀን በበኩሉ የዳቦ ዋጋ ታሪፍ አለመስተካከልና ከመንግስት የሚሰጠው የዳቦ ዱቄት አነስተኛ መሆን ከሚታዩ ችግሮች ዋናዎቹ ናቸው።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ዳቦ እንዲያገኝ ከተፈለገ ዳቦ አምራቹና አመራሩ ተናቦና ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በቁጥር 05/2011 የተዘጋጀው መመሪያ በድጎማ የሚቀርቡ ምርቶች በትክክል ለተጠቃዎች ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረና እየተተገበረ ያለ መሆኑም ታውቋል፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክም በባህር ዳር ከተማ ዳቦ የሚያመርቱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆናዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

Check Also

የኮሎኔል አብይ አህመድ አስገራሚ የትምህርት መረጃዎች ! የትኛው ነው ትክክል?

ሻለቃ ውብ አንተን ስሙት።

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.