ሰሞኑን በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ መደፍረስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ የክልሉ የፀጥታ ኃይል የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ የአማራ ክልል የደህንነትና ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በወቅታዊ የክልሉ የፀጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በጎንደር ገንዳ ውሃ አካባቢ ችግር ተፈጥሮ ነበር፤ መንስ ኤው ምንድነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- የተከሰ ተውን ሁኔታ በተለያየ አግባብ ለመግለጽ ሞክረናል፡፡ እዚያ አካባቢ ሱር ኮንስትራክሽን የሚባል ድርጅት መንገዶችን ይሰራ ነበር፡፡ ሕብረተሰቡ በድርጅቱ ላይ ከአንዳንድ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ ስለነበረው መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቋል፡፡ ጥያቄው ታምኖበት ስለነበር በተወሰነ መንገድ ለማጣራት ሲሞከር፤ ድርጅቱ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የሕዝብ ተወካዮችንና የፀጥታ ተቋሙን ይሄማ አንድ ነገር ቢኖር ነው የሚል ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ የተለያዩ መሳሳቦች ተፈጥረው ሱር ኮንስትራክሽን በስፍራው ሥራውን ለመስራት ብዙም ፈቃደኛ ባለመሆን ለመውጣት ፈልጎ ነበር፡፡ ሕብረተሰቡ ልማት እንዲቆም አይፈልግም፡፡ መንገዱ መሰራት አለበት፡፡ ግን ደግሞ አካባቢው በሕግ ጥላ ስር ሆኖ መፈተሽ አለበት የሚል እምነት ነበረው፡፡ መኪኖችን እንለቃለን-አንለቅም በሚል ግጭቱ ተፈጠረ፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአለዎት መረጃ መሰረት በተፈጠረው ግጭት የመጀመሪያውን ጥይት የተኮሰው ማነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- እኔ አሁን ገበሬዎች ናቸው፤ ሚሊሺያዎች ናቸው የተኮሱት አልልም፡፡ በኋላ እንደተታኮሱ ሰምቻለሁ፡፡ ምንም ይሁን ምን ገበሬዎች በመጀመሪያ ደረጃ ቢተኩሱም፤ መነሻ ቢሆኑም ያልተመጣጠነ እርምጃ ነው የተወሰደው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግጭቱ ከቀላል መሳሪያ ውጭ ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ነበሩ ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- አዎ፤ ፀረ አየር መቃወሚያ ሁሉ ተጠቅመዋል፡፡ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ስድስት ሰዎች ሞተዋል፡፡ ሕብረተሰቡን ለመበተን ወይንም ለማረጋጋት የተጠቀሙበት ቴክኒክ ሊሆን ይችላል፡፡ ሕብረተሰቡ በክላሽ ጥይትም ሊበተን ይችላል፡፡ ብዙ የታጠቀ ኃይልም አይደለም፡፡ የታጠቀ ተቋምን መቋቋም የሚችል ተፈጥሮአዊም ወቅታዊ ሁኔታም ያለው ሕዝብ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ግጭቱን የፈጠረው ማንም ይሁን ማን ያልተመጣጠነ ነገር ተፈጥሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምንም የማያውቁ ንጹሀን የሆኑ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ሕጻናትና ሴቶች በዚህ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ የላቸውም፡፡ የታጠቁት ተኮሱ የተባሉት አይደሉም የሞቱት ሌሎች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉና መከላከያ ሚኒስቴር የሰጣችሁት ሀሳብ የተለያየ ነው፡፡ የአንድ መንግሥት አካል ናችሁ፡፡ ተናባችሁ መስራት ያልቻላችሁበት ምክንያት ምንድነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- አንደኛው ይህ ተቋም ሲወጣ ማሽነሪዎች ሲጓጓዙ የፀጥታ ተቋሙ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ አሁን እያነጋገረህና ቃለመጠይቁን እየሰጠህ ያለው የፀጥታ ተቋሙ ተወካይ ነው፡፡ እኔ የዚያ አካል ነኝ፡፡ እንደ ተቋም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ምናልባት የተቆራረጠና መደበኛ ያልሆነ ግንኙነት ይኖራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይሄ በውስጣችንም በውጭም ከመከላከያ ጋር ያለን የቅንጅት ወይም ተግባብቶ የመሄድ ጉዳይ እንደ እጥረት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሁሉም እውነትና ተገቢ ነው ብሎ የመሰለውን ነው የሚያደርገው፡፡ እውነት የሚባለው ግን የሚዳሰስ የሚጨበጥ የሚታይ ከሆነ እኔም ልናገረው ማንም ይናገረው እውነት እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ ተናቦ የመሄድ ጉዳይ ላይ ነው፡፡
በሌላም በኩል በኃይል መንገድ ጥሶ ለማለፍና ጉልበት ለመጠቀም መሞከር ሕብረተሰቡን አበሳጨው ብዬ አስባለሁ፡፡ መግባባት እየቻልን መነጋገር እየቻልን የተፈጠረ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ መርሳ ላይ ገጥሞን ነበር፡፡ የቱርክ ድርጅት በአዋሽ ወልዲያ ሀራ ገበያ መንገድ ኮንትራታቸውን ጨርሰው ማሽኖቹ እንዲወጡ ይፈለግ ነበር፡፡ ሕብረተሰቡ ባለማወቅ ለሁለት ሳምንት አገታቸው፡፡ እነኝህን ማሽኖች ተነጋግርን ተግባብተን ሕብረተሰቡ አምኖበት በጅቡቲ በኩል ተሸኝተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በገንዳውሃ ጉዳይ ግን ተኩስ ከተከፈተ በኋላ ውይይት ማድረግ አስቸጋሪ ነበር ተብሏል፡፡ በእርግጥ ተኩስ ከመከፈቱ በፊት በውይይት መፍታት ይቻል ነበር ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ጉዳቱ ከመከሰቱ በፊት ውይይት ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ገንዳ ውሀ የሚባለው የዞኑ ከተማ አለ፡፡ ሕዝቡ ቁጭ ብሎ እየመከረ እየተነጋገረበት ነበር፡፡ በጎን አጅበው ማስወጣት ጀመሩ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ይሄን ሰማ፤ አየ፡፡ እነዚህ ሰዎች እኛን እያነጋገሩ በጎን እንዲህ እያደረጉ የሚል ነገር ተነሳና አባባሰው፡፡ ውይይቱ መፍትሄ ያመጣል ተብሎ ሳይሆን በዚህ አጋጣሚ ሕብረተሰቡ በዚህ እንዲቆይ የታሰበ ታክቲክ ወይንም ስትራቴጂ ነበር ማለት ነው፡፡ ይህ አለመግባባት የውጥረቱን ደረጃ ከፍ አደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሱር ኮንስትራክሽን በመከላከያ ሠራዊት ጥበቃ ይደረግለት ነበር፡፡ለሥራ እንዲንቀሳቀሱ የተፈቀደላቸው ድርጅቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ክልሉ ተጠይቋል?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፡- ክልሉ አልተጠየቀም፡፡ ብንጠየቅ እናደርጋለን፡፡ ማንም አደረገው ማን ችግር የለብንም፡፡ መከላከያ፣ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሺያው፣ ገበሬውም ቢያጅበው ችግር የለውም፡፡ የሚፈለገው ነገር መውጣታቸው ብቻ ነው፡፡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ወደዚያ ወደተፈለገው አካባቢ መሄዳቸው ነው የሚፈለገው፡፡ ግን በጉዟቸው ሂደት የሚያጋጥም ችግር እንዳይኖር ነው ጥንቃቄ የሚደረገው፡፡ ከደህንነት አንጻር ከባድ የሆነ ችግር ያለበት አካባቢ ነው፡፡ ትንሹን ነገር በጥንቃቄ ካልያዝነው ወደአልተጠበቀ ቀውስ ውስጥ ያስገባናል፡፡ በእርግጥ ይሄ ነገር ቢኖርም ባይኖርም ቀውሱ ይቀር ነበር አይቀርም ይሄ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ በቀውስ አያያዙ ላይ ግን የተወሰነ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ሲሆን ተጋግዘህ ተረዳድተህ መስራት ችግሩን አንድ አድርገህ መሄድ ሌሎችንም ችግሮች ለመፍታት ያግዝ ነበር፡፡ እንዲህ አይነት የተናጠል ወይም ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ስለነበር ይመስለኛል ያ ቀውስ የተፈጠረው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጉዳዩን የማጣራቱ ሂደቱ ምን ላይ ነው የሚገኘው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- የማጣራቱን ጉዳይ ድርጊቱ እንደተፈጸመ በሁለተኛው ቀን ጀምረናል፡፡ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሁኔታውን የሚያጣሩ አካላት ተሰይመው ሥራ ጀምረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከመከላከያ ጋር በቅርበት እየሰራችሁ ነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- በላይኛው ደረጃ እየተሰራ መሆኑን አላውቅም፡፡ መረጃ ለጊዜው የለኝም ማለቴ ነው፡፡ ታች አካባቢ
በሂደቱ የግድ መግባታቸው አይቀርም፡፡ እኛ ሁለቱም አካላት ነጻ ሁነው ያጣሩትና በኋላም በየራሳቸው ይዘው የሚመጡትን በጋራ እንየውና ከተግባባን እንቀጥላለን ካልተግባባን ደግሞ በሌላ መንገድ እንሄድበታለን ነው ያልነው፡፡ ስለዚህ መጣራት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በመተማ ዮሐንስ አይከልና ጭልጋ አካባቢ የተፈጠረውስ ምንድነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ቀደም ሲልም አካባቢው ችግሮች ነበረበት፡፡ ከጭልጋ ወጣ ብለህ ባሉት ቀበሌዎች አካባቢ ከአይከል ወደ ሰባት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በጎንደርና በአይከል መካከል የሚገኙ ቀበሌዎች ሦስት ቀበሌዎች ናቸው ጥቃት የተፈጸ መባቸው፡፡ አንደኛው ቀበሌ ሙሉ በሙሉ ወድሟል፡፡ በቅማንት ስም የታጠቁ ኃይሎች ባሳለፍነው ጥር 4 ቀን 2011 ዓ.ም ሌሊትና በቀጣዩም ቀን በሰነዘሩት ጥቃት 200 ቤቶች አቃጥለዋል፡፡ ከ2 ሺ ያላነሰ ሰው ተፈናቅሏል፡፡ 55 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሁኔታውን እነሱ ቀድመው አስበውበታል፤ ሰልጥ ነውበታል፡፡ በዚያው መንገድ ደግሞ ቀጥተኛ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ የቡድን መሳሪያም ሳይቀር ተጠቅመዋል፡፡ ከታጣቂዎቹ መካከል ከሌላ አካባቢ መጥተው የሞቱ ሦስት አስከሬኖች አግኝተናል፡፡ ይሄ የተቀናጀና የተደራጀ እንቅስቃሴ ነው፡፡ አማራውን በየተገኘው አጋጣሚ ለማፈናቀል ነው እየተሰራ ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይሄንን ችግር ለመቋቋም፣ ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር የሚያስችል በቂ የፀጥታ ኃይል የላችሁም ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- የመቋቋም አቅም አንጻራዊ ነው፡፡ የሚገርምህ ነገር እዚህ አካባቢ እኮ ልዩ ኃይልም፣ መከላከያም አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደዚህ አይነት በሕዝብ ላይ ጥቃት ሲደርስ የመከላከልና የማስቆም ግዴታና ኃላፊነት አለባቸው፤ ምን ይሰራሉ ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ቤቶቹ ሲቃጠሉም እኮ አንዳንዴ መከላከያ ያያል፡፡ ለመግባት አልታዘዝንም ይላል፡፡ ወይንም ደግሞ የተወሰነ ይሞክርና አቅም አንሶት ይመለሳል፡፡ የሽምቅ ውጊያ ስልቶች ይታወቃሉ፡፡ መተህ ሩጥ ነው (ሂት ኤንድ ራን) ሰው ባለበት አካባቢ ሳይሆን ሰው በሌለበት አካባቢ ያቃጥላል፤ ሰው ይገድላል ፤እርምጃ ይወስዳል ፤ የተደራጀውና መደበኛ የሆነው ኃይል ወደዚያ ትኩረት ሲያደርግ ደግሞ ወደሌላ አቅጣጫ ሄዶ ደግሞ ይሄንኑ እርምጃ ይወስዳል፡፡ እርምጃ መውሰድ ላይ የራሱ ውስንነት ይታያል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግሩን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ምን ይመስላል ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ጉዳዩ መሰረታዊ በመሆኑ ኃይል በስፋት አስገብተናል፡፡ ተደራጅቶ የበለጠ ጥፋት ሲፈጽም የነበረው ኃይል ለጊዜው ለማቆም ተሞክሯል፡፡ ከጥር 7 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግጭት ይቀሰቅሳሉ የተባሉት በቅማንት ስም የሚንቀሳቀሱ አካላት ከቀላል መሳሪያዎች ውጭ ከባድ መሳሪያዎች አላቸው የሚባለው እውነት ነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- አለ የሚባለውን እኛም እንሰማለን፡፡ አንድ ሞርታር እንዳላቸው ግን አረጋግጠናል፤ ተጠቅመውበ ታል፡፡ ባለፈው የነበረው ውጊያ በክላሽን አልነበረም፡፡ ብሬን፤ ስናይፐር (አልሞ ተኳሽ)፤ ብዙም ባይሆን ድሽቃ ሁሉ ተጠቅመዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በከፍተኛ ደረጃ አለ ነው የሚባለው፡፡ ይሄንን ለመግታት በእናንተ በኩል ምን እየተሰራ ነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ህገ ወጥ የጦር መሳሪያን ለመቆጣጠር ምንጩን መቆጣጠር ነው የሚገባው፡፡ በዚህ ረገድ ጥናት ላይ ነን፡፡ ከውጭ ነው የሚገባው አቅጣጫዎቹ ይታወቃሉ፡፡ አንደኛ ከሚመለከታቸው የጎረቤት ሀገራት የፀጥታ አካላት ጋር ለመነጋገር ተሞክሯል፡፡ እነርሱም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉና እንደሚያግዙን ቃል ገብተዋል፡፡ በሱዳን አቅጣጫ ነው በስፋት የሚገባው፡፡ ሁለተኛው በምስራቅ በጅቡ እና በአፋር በረሀማ አካባቢዎች ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ለማነጋገር ተሞክሯል፡፡ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ ግን ግብረ መልሱ ፈጥኖ ተግባራዊ የሆነ አይደለም፡፡ እኛ በየአካባቢው በተለመደው ብቻ ሳይሆን ከዛ ውጪ ወጣ ብለን አንዳንድ ሥራዎችን ለመስራት እየሞከርን ነው ያለው፡፡ ሕብረተሰቡ ደግሞ ይሄን ለማጋለጥና ለሕግ አካላት አሳልፎ ለመስጠት በጣም ዝግጁ ነው፡፡ ይህ በጣም የተደራጀ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሲስተም የተዘረጋ ኃይል ነው፡፡ ዝም ብሎ አዩ አላዩ ተብሎ የሚሰራ ሥራ አይደለም፡፡ የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ የሚሰራ የማፍያ ቡድን ዓይነት አለ ይባላል፡፡ ምልክቶቹንም እያየን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የጦር መሳሪያ በህጋዊ መንገድ አስመዝግቡ ከተባለ ወዲህ ያለው ሁኔታ እንዴት ነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ያለውን መረጃ እያጠቃለልን ነው፡፡ በአማራው ክልል በስፋት መሳሪያ ይኖራል ተብሎ እንደሚ ታሰበው አይደለም፡፡ አሁን የአንድ ክላሽ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ገበሬው በቂ አቅም ስለሌለው መሳሪያ አሳልፎ ይሸጣል፡፡ ሰሞኑንም እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ድህነት መሳሪያውን ያሸጠዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ህገወጥና ድብቅ የሆኑ በመንግሥት የማይታወቁ የወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ተገኝተዋል ተብሏል፤ ቢነግሩን ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- በተለያዩ አካባቢዎች አለ ይባላል። ያው በተወሰነ መንገድ ተሄዶበት ለጊዜው የፈረሰ ቢሆንም ዞሮ ዞሮ አካባቢው ለዚያ የሚመችና የሚስማማ ስለሆነ እሱን እየተጠቀሙበት ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌሎችስ የአማራው ክልል አካባቢ እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ የለም ብላችሁ ትገምታላችሁ ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- አለ፡፡ በባቲ አካባቢ የማሰልጠኛ ጣቢያ ተገኝቷል፡፡ ዞሮ ዞሮ ከክልሎችም ከሌሎችም ጋር ተቀናጅተን እየሄድንበት ስለሆነ አሁን በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ወይ አቅጣጫውን ቀይሯል ወይንም ቀንሷል፡፡ እኛም በከፍተኛ ደረጃ ጉዳዩን እየተከታተልነው ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ኃላፊነቱን ከተረከቡ ወዲህ የክልሉን ፀጥታ በማረጋገጥ ረገድ የተገኙ መልካም ስኬቶችና ተግዳሮቶች ምንድናቸው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- እኔ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ለውጥ መጥቷል ብዬ አላምንም፤ ስለሌለ፡፡ ነገሮች ቀጥለዋል፡፡ አሁን የእኔ ሥራ እንደ ክልል በመጀመሪያ ያለውን ሁኔታ ማወቅ ነው፡፡ ይሄንን ለማወቅ እንደ ተቋም ጥረት አድርገናል፡፡ ሁለተኛ ከአወቅን በኋላ ይሄንን የአወቅነውን እውቀት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ድርጅታዊና ተቋማዊ ቁመና እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ተቋሙን እንደ አዲስ ከላይ እስከታች ለማደራጀት እየጀመርን ነው፡፡ ይሄን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ሦስተኛ ይሄንን አደረጃጀት ተጠቅመን ደግሞ ይሄንን ሊያግዝና ሊመራ የሚችል የሰው ኃይል ማብቃትና ማሰልጠን ነው፡፡ ይሄን የክልል የፀጥታ ኃይል ለማስጠበቅና የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር የሚያስችል በርካታ ሰው ማሰልጠኛ ውስጥ ገብቶ እየሰለጠነ ነው ያለው፡፡
ውጤታችንን በሂደት የምናየው እንጂ አሁን በእነኚህ አንድና ሁለት ወራቶች ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ በዚህ አካባቢ ያሉ ሁኔታዎች የበለጠ ተሰቅዘው እንዲያዙ ለማድረግ ደግሞ ሰፊ ሥራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡
ሌሎችም አካባቢዎች የድርጅቶችን አቅም በመጠቀም ከሁኔታዎች ወጣ ለማለት የሚፈልጉ ኃይሎችን በመጠቀም እያደራጁ ገንዘብ ሁሉ እየበተኑ ሥራ እየሰሩ ናቸው ያሉት፡፡ ለምሳሌ ምንም አይነት ተልዕኮ የሌላቸው በአካባቢው የማይታወቁ ግን ደግሞ በቀጥታ ከዚያ አካባቢ እየመጡ የታሰሩ ሰዎች አሉ፡፡ የሚያዙ ሰዎች አሉ፡፡ ተልእኮ ይዘው፡፡ ለምሳሌ ጎንደር ላይ በቅርቡ አንድ ሰው ተያዘ፡፡ ይሄ አንድ ሰው ዘጠኝ መታወቂያ አለው፡፡ ዘጠኝ ስም አለው፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎች አሉ በየቦታው፡፡ በየጊዜው የጦር መሳሪያ ተኩስ ታያለህ፤ ትሰማለህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ስምሪት የሚሰጡ ኃይሎች ሁሉ ተመድበው ይሄን ሥራ ይሰሩታል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የእዝ ጣቢያ እንዲቋቋም አላደረጉም ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ተቋቁሞአል፡፡ መቋቋሙ በራሱ መፍትሄ አያመጣም፡፡ ለሁኔታዎች ቅርብ ካልሆነ በቀር በፊትም በተደጋጋሚ ተሞክሯል፡፡ ሆኖም በበለጠ ከስልጠናው ጋር ተያይዞ አብሮ የምንሰራው ሥራ ነው፡፡ ምንም ኃይል በሌለበት የእዝ ጣቢያ (ኮማንድ ፖስት) ብታቋቁም የነበረው ነው የሚቀጥለው፡፡ የነበረው ደግሞ አዲስ ለውጥ የሚያመጣ ሳይሆን ገና እራሱንም እየበላ ያለ ኃይል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን በክልሉ በተለየ መልኩ ከባድ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ያው ብልጭ ድርግም እያለ ብዙ ቦታዎች ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የግለሰቦች ነው የተደራጀ ነው ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- የተደራጀ አይደለም፡፡ አሁን ከባድ የሆነ ችግር ያለው ምእራብ ጎንደርና ማእከላዊ ጎንደር ነው፡፡ ሁለቱም አንደኛ ተያያዥ በመሆናቸው ሁለተኛ የቅማንት ማህበረሰብና የአማራ ማህበረሰብ በስፋት ስለሚኖርባቸው ወደፊት ሊደርባቸው ይገባል ተብሎ የታሰቡ ሥራዎች በመሀል ላይ በመቆማቸው በብዙ ምክንያት ያው ጠረፍም ስለሆኑ ሌሎች ሌሎችም ሁኔታዎች ተጨምረው እዛ አካባቢ ችግሩ ከባድ ነው፡፡ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አርማጮሆና አንገረብ አካባቢስ ?
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- እሱ ከምእራባዊ ጎንደርና ከማእከላዊ ጎንደር በተለይ ምስራቃዊ አካባቢ ጋር ሲወዳደር የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ አሁን ከሰሞኑ ቀደም ሲል ያልነበሩ አዳዲስ ክስተቶች ታይተዋል፡፡ የተወሰኑ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶች ተነሳስተው የቅማንት ቤተሰቦቻችን ወንድሞቻችንን ንብረት አውጥተው አቃጥለዋል፡፡ ያ እንግዲህ እያደገ መጥቶ እዚህም አካባቢ ቅማንት አማራውን ጎዳ በሚል ላይ አርማጮሆ አካባቢ ትክል ድንጋይ አካባቢ መንገድ የመዝጋት የመጥለፍ የማፈን መንገድ መዝጋት ነገር አለ፡፡ ጠንካራ አይደለም ለማለት ነው እንጂ እዚህም ችግር አለ፡፡ ይህ ቅማትና የአማራውን ማህበረሰብ አይወክልም፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት የመስተዳድሩም የፀጥታ ኃይሉም የሃይማኖት አባቶችም የሚመ ለከታቸው አካላት ተቀናጅተው ሰሞኑን ሥራ ጀምረዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን!
ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው፡- እኔም አመሰግናለሁ!
አዲስ ዘመን ጥር 10/2011
ወንድወሰን መኮንን
ምንም አይነት ገበሬ ሆነ ሚንሻ አልተኮሰም። መኪናወቹ የታጀቡት በመድፍ እና በአየር መቃወሚያ ጭምር ነው።
መጀመሪያ አንድ መፈተሽ አለብን ብሎ ወደ መኪናው ሲወጣ ሹፌሩ ከጋቢና ወጥቱ ልጁን በሽጉጥ መተው። ከዛ አከታትለውም ጠባቂዎች ጥይት ወደ ህዝቡ ተኮሱ።
ከዛ በሃላ ህዝቡ በየ ቤቱ ጥይት ይዞ ወጣና ገጠማቸው ።
በቃ ይህ ነው