Breaking News
Home / Amharic / ኢትዮጵያዊነት የአማራ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም – ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

ኢትዮጵያዊነት የአማራ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም – ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

ኢትዮጵያዊነት የአማራ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም

ከሰሞኑ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) በባህር ዳር በተደረገ መስራች ጉባኤ የተመሰረተ ሲሆን የፓርቲውን ሊቀ መንበርና የስራ አስፈፃሚ አባላትንም መርጧል፡፡ ፓርቲውን በመመስረት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አሁን በሊቀ መንበርነት የተመረጡትን ጨምሮ 16 ሰዎች በኮማንድ ፖስት ታስረው መፈታታቸው የሚታወስ ሲሆን ፓርቲው ሲመሰረት የክልሉ መንግስት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ትብብር አድርጎላቸዋል፡፡
ለመሆኑ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) አላማና ግብ ምንድን ነው? የትግል ስልቱስ? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር፣ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ መምህሩን ዶ/ር ደሣለኝ ጫኔን፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በአጭሩ አነጋግሯቸዋል፡፡

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄን (አብን) ለመመስረት ምክንያታችሁ ምንድ ነው?

መሠረታዊ መነሻ ምክንያታችን፣ በአማራ ህዝብ ላይ ባለፉት ዓመታት እየደረሰ ያለው፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ግፍና መከራ ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ያንን ደግሞ በአግባቡ ይዞ መታገልና ለህልውናው መከበር የሚሠራ ድርጅት ስለሌለ፣ ክፍተቱን ለመሙላት ነው ድርጅቱን የመሰረትነው፡፡

የፓርቲያችሁ ዓላማና ግብ ምንድን ነው?

ዓላማዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ አንደኛው፤ አሁን የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ተገልሏል፡፡ ጥቅሞቹ እየተከበሩ አይደለም፤ ስለዚህ እነዚህን ጥቅሞቹን ማስከበር የመጀመሪያው አላማ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ማንነታቸውን እየጠየቁ ያሉ አማሮች መገለጫዎቻቸው እየተከበሩ አይደለም። የአማራን ህዝብ ሁለተንናዊ ማንነት ማስከበርና ማስጠበቅ ሌላው ነው፡፡ ሌላው አጠቃላይ በአማራ ክልልም ሆነ ከክልላችን ውጪ ያሉ ወገኖቻችን የመገደል፣ የመሠደድ፣ የመፈናቀል፣ ሃብታቸው የመውደም ችግር እየደረሰባቸው በመሆኑ፣ እነዚህን የመመከት፣ የመከላከልና እንዲቆም የማድረግ ትግል ነው፡፡ የአማራ ህዝብ ለኢትዮጵያ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ አስተዋፅኦና በዚህች ሃገር ሊኖረው የሚገባውን ድርሻ ማሳደግም አንዱ ዓላማችን ነው፡፡

ከፕ/ር አስራት ወልደየስ (መዐህድ) በኋላ፣ አማራውን እወክላለሁ ብሎ የተቋቋመ ድርጅት የለም። ለምን ይመስልዎታል?

በእርግጥ የተወሠኑ የዳሠሣ ጥናቶችን ለማድረግ ሞክረናል፡፡ አንደኛ፤ በሂደት ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ተኮር ፖለቲካ ቀስ በቀስ እየከሠመ፣ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ስርአት ይተከላል የሚል ተስፋ ህዝባችን ነበረው፡፡ ያ ማለት ኢትዮጵያዊነትን የሚወድ፣ ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት ያደረገ ህዝብ ስለሆነ፣ ይሄን መፈለጉም ተገቢ ነበር። ሌላው፤ አማራው ላይ ሲፈጸም የቆየው ዘርን መሠረት ያደረገ መፈናቀልና ጥቃቶች በሂደት ሊቀንሱ ይችላል የሚል እሳቤም ነበረ፡፡ የአማራ የህልውና ጥቅሞች በኢትዮጵያዊ የአንድነት ማዕቀፍ ውስጥ ይፈታሉ የሚል ግምት ነበረው ማህበረሠባችን፡፡ እውነቱን ለመናገር ባለፉት 27 ዓመታት ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ሲተከል፣ በመሠረታዊነት የቆመበት ምሰሶ፣ አማራን በጨቋኝነት ፈርጆ፣ ሌሎቹን በተጨቋኝነት የሚፈርጅ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ጥላቻ በሂደት ስር እየሠደደ ነው የመጣው፡፡ አማራ ጠልነት ምን ያህል ስር እየሠደደ እንደመጣ መገንዘብ አለመቻሉና በተለይ ባለፉት ሁለት ሶስት አመታት የበለጠ ጉዳዩን እየተረዳው መምጣቱ፣ በተጨማሪም አማራ ክልል ውስጥም፣ አማራ በሚኖርባቸው አካባቢዎችም የተነሡ እንቅስቃሴዎች፣ የኛን ፓርቲ እንዲወልድ አድርጓል ብዬ አስባለሁ፡፡

እነዚህን መብቶች ለማስከበር የምትጠቀሙበት የትግል ስልት ምንድን ነው?

የአማራ ህዝብ ሃገሩ ኢትዮጵያ ናት፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በስፋት የሚኖር ህዝብ ነው። ስለዚህ የአማራ ፓርቲ ቢባልም ቅርንጫፎቹን በመክፈት ትግሉን የሚያደርገው አማራዎች በሚኖሩባቸው መላ የኢትዮጵያ ክፍሎች ነው፡፡ ለምሳሌ ለምርጫ ቦርድ የመስራች አባላት ፊርማ ስናሰባስብ 40 በመቶ ከአማራ ክልል፣ ሌላውን ደግሞ ከአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ነው። ስለዚህ አማራ በሚኖርባቸው አካባቢዎች በሙሉ፣ በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጡ መብቶችን ለአማራው ማስከበር ነው፡፡ የትግል ስልታችን ህገ መንግስቱ ላይ መሠረት ያደረገ ሠላማዊ የትግል ስልት ነው፡፡ ያ ማለት ግን ህገ መንግስቱ ላይ እንዲሻሻሉ የምንጠይቃቸው ነገሮች የሉም ማለት አይደለም፡፡ ህገ መንግስቱ ከመግቢያው ጀምሮ የአማራን ጨቋኝ ትርክት ያሠፈረ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት አንቀፆች መሻሻል አለባቸው፡፡ አማራ በአግባቡ ሳይወከል ጥቅሙን ያጣባቸው ህጎችን መርምረን እንዲቀየሩና እንዲሻሻሉ በሁለገብ የሠላማዊ ትግል አማራጮች እንታገላለን፡፡

በሌሎች ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ ተወላጆች፣ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ እንታገላለን ብላችኋል፡፡ ምን ማለታችሁ ነው?

የፌደራል ስርአት አወቃቀሩ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን አረጋግጧል፡፡ ያ ደግሞ መረጋገጡና መተግበሩ የሚታየው አማራ ክልል ላይ ነው፡፡ በክልሉ የተለየ ብሔረሰባዊ የኋላ ታሪክ ያላቸው በቁጥር አነስተኛ የሆኑ፣ራስን በራስ ለማስተዳደር ልዩ ዞን፣ ልዩ ወረዳ ሆነው እያስተዳደሩ ነው፡፡ ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን የማዳበር መብታቸው ተከብሯል፡፡ አማራ ክልል ላይ ይህ ከተከበረ፣ ሌሎች አማራ በስፋት በሚኖርባቸው ክልሎች ላይ የማይከበርበትና ልጆቹን በራሱ ቋንቋ ማስተማር፣ በራሱ ባህል ማሣደግ መብቱ የማይከበርበት ምክንያት የለም፡፡ በህገ መንግስቱ ላይ የተረጋገጠና በአማራ ክልል ላይም የተተገበረ ስለሆነ፣በሌሎች ክልሎች ያሉ አማራዎች ያንን ማግኘታቸው ተገቢ ነው፤ ለሱም መታገል ፍትሃዊ ነው፡፡

የአማራን ታሪካዊ ቦታዎች ማስመለስ የሚል ዓላማም ይዛችኋል፡፡ የትኞቹ ቦታዎች ናቸው? በምን ዓይነት መንገድስ ነው የምታስመልሱት?

በሽግግሩ ጊዜ ክልሎች ሲካለሉ፣ አማራ ባለመወከሉ፣ ስህተት ተፈጥሯል ብለን ከምናስባቸው አንዱ፣ በአብዛኛው አማራ በሚኖርባቸው በቋንቋ፣ በባህል፣ በስነልቦና የአማራ ማንነት ባላቸውና አማራ ነን ብለው ያስቡ የነበሩ እንደ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ መተከል፣ ራያ፣ አላማጣና ሌሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ቦታዎች ወደ አማራ ክልል መከለል የነበረባቸው ናቸው፡፡ ብዙ ሰው የወልቃይትን ጉዳይ የመሬት ጉዳይ አድርጎ ይወስደዋል፤ ነገር ግን ህዝቡ እያለ ያለው አማራዊ ማንነታችን ይከበርልን ነው። ዘፈናችን፣ ለቅሶአችን፣ ቋንቋችን አማራ ስለሆነ፣ በአማርኛ እንናገር፤ መብታችን ይከበር ነው ጥያቄው፤ ነገር ግን በአማርኛ መናገር ብዙዎቹን አሳስሯቸዋል፡፡ ግፍ አስፈፅሞባቸዋል፤ አማርኛ ዘፈን ማዳመጥ ወንጀል ሆኖባቸዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ታሪካዊ ቦታዎች፣ በሂደት ወደ ታሪካዊ ቦታቸው እንዲመለሱ እንታገላለን፡፡ ይሄን የምናደርገው ደግሞ ህገ መንግስቱ በፈቀደውና በሠላማዊ መንገድ ነው፡፡

ምናልባት እንደ ህዝበ ውሣኔ ዓይነት መንገድ ማለታችሁ ነው?

ህዝበ ውሣኔ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንደኛ፤ አማራው ማህበራዊ መሠረቱን እንዲያጣ ተደርጎ አፍርሶ የመገንባት ስራ የተሠራባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አማራው ቦታውን እንዲለቅ፣በምትኩ ሌሎች ብሄሮች ቦታው ላይ እንዲሠፍሩ የተደረገበት ሂደት አለ፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ህዝበ ውሣኔ ሊደረግባቸው እንዴት ይቻላል? ታሪካዊ ማስረጃዎችና ቀድሞ የነበሩ አስተዳደራዊ ሁኔታዎች፣ መሠረታዊ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ወሰኑ ተከዜ ነበር፡፡

የአማራ ብሄርተኝነትንና ኢትዮጵያዊነትን እንዴት ነው እያስታረቃችሁ የምትሄዱት?

አንደኛ፤ አማራ ከኢትዮጵያዊነቱ መቼም ሸሽቶ አያውቅም፣ ሊሸሽም ሊያፈገፍግም አይችልም፤ ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ፕሮጀክታችን ነው። የአማራ ፕሮጀክት ብቻ አይደለም፡፡ የሁላችንም ፕሮጀክት ነው፡፡ የሁሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሄረሰብ ፕሮጀክት እንጂ የአማራው ብቻ አይደለም። አማራ እንደ ኢትዮጵያ ብቸኛ ጠባቂ ተደርጎ የሚታይበትና፣ አማራ ለብቻው ከተደራጀ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚለው ስህተት ነው፡፡ አንደኛ፤ አማራ በተለየ መንገድ በማንነቱ እየተጠቃ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ እንደ አማራነቱ እየተጠቃ፣ ጥቃቶቹን እንደ ኢትዮጵያ ሆኖ ሊከላከላቸው አይችልም፡፡ ስለዚህ እንደ አማራነቱ ተደራጅቶ፣ መጀመሪያ ራሱን ያተርፋል፤ ራሱን ይከላከላል፣ ራሱን ይጠብቃል፤ ሲቀጥል ደግሞ ከሌሎች እህት ወንድሞቹ ጋር ሆኖ እየተሸረሸረና እየጠፋ ላለው ኢትዮጵያዊነት ሊደርስለት ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሌሎች ብሄሮች፣ በብሄራቸው ተደራጅተው፣ አማራ በኢትዮጵያዊነት ብቻ እየተወከለ ይስራ ማለት የፖለቲካ ብልጫ እንዲወሰድበት የሚያደርግ ነገር ነው፡፡
አማራ በአማራነቱ ሁነኛ የፖለቲካ ድርጅት አቋቁሞ፣በፌደራል ስርአቱ ላይ ከሌሎች ወንድም እህቶቹ ጋር ይደራደራል፡፡ የሚገባውን ጥቅም ያስከብራል፡፡ ከሃገሪቱ እድሎችና ጥቅሞች የራሱን ድርሻ እንዲያገኝ ይታገላል ማለት ነው፡፡ ይህ ሃገር ግን የጋራችን ቤት ነው፡፡

የቅርብ ጊዜ እቅዳችሁ ምንድን ነው? በምርጫ ትሣተፋላችሁ?

እሱን የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት እንደሚዳብር፣ እንዴት እንደሚቀያየር እያጠናን የምንወስነው ቢሆንም በመርህ ደረጃ ግን ሠላማዊ የሆነና በሠላማዊ መንገድ ሃገር ውስጥ የሚታገል ፓርቲ፤ ምርጫ ውስጥ መሣተፍ ግዴታው ነው፡፡ በእርግጠኝነት ህዝባችን በሚኖርባቸው አካባቢዎች እንወዳደራለን፡፡ ተወዳድረን ፍፁም በሆነ አብላጫ ድምፅ ማሸነፍ እንደምንችል፣ ከህዝባችን እስካሁን ያገኘነው ድጋፍና መነቃቃት የሚያመላክተው ነገር አለ፡፡ ግን በቀጣይ የሃገሪቱ ሁኔታ ወዴት ያመራል የሚለውን በጥልቀት እየገመገምን፣እንቅስቃሴያችንን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.