የሕዝብ እና የቤት ቆጠራን አስመልክቶ፣ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የተሰጠ የአቋም መግለጫ ፦
በ1998/9 ዓ.ም የተደረገውን የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ተከትሎ፣ መንግሥት ባወጣው ይፋዊ የቆጠራ ውጤት፣ 2.5 ሚሊየን የሆነ የአማራ ሕዝብ ጠፍቷል ተብሎ ለአገራችን ፓርላማ ሪፖርት መደረጉ ይታወቃል፡፡ በመንግሥት የታመነው እና ጠፋ የተባለው የአማራ ሕዝብ ብዛት 2.5 ሚሊየን ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ የ1984፣ የ1994 እና የ2007ን የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ያጠኑ ምሁራን፣ የታዳጊ አገሮችን የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ፣ የሌሎች ኢትዮጵያውያን ብሔረሰቦች የዕድገት ምጣኔ እና አስቀድሞ የነበረውን የአማራ ሕዝብ ቁጥር መሰረት አድርገው በሰሩት ትንታኔ፣ እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም (በ1998/9 ዓ.ም) በተደረገው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ መኖራቸው የተካደው ወይም እንዲጠፉ የተደረጉት አማሮች ቁጥር እስከ 6.2 ሚሊየን ሕዝብ እንደሚደርስ አረጋግጠዋል፡፡
በ1998 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ በአማራ ሕዝብ ላይ ከተፈፀመው የቁጥር እልቂት (numerical genocide) በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ እና በጉራጌ ሕዝብ ላይ ተመሳሳይ የቁጥር እልቂት የተፈፀመ ሲሆን፣ የቅማንትን ሕዝብ ኅልውና በመካድ በአገራችን ከተከናወኑ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ታሪክ አስነዋሪ ወንጀል የተፈፀመበት መሆኑን፣ የመስኩ ምሁራን በጥናት አረጋግጠዋል።
የአንድ ሕዝብ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ የሚሰላው እና በመሬት ላይ የሚከናወነው ቆጠራ እውነተኛነት የሚመሳከረው፣ መሬት ላይ በሚደረግ ቆጠራ ብቻ ሳይሆን፣ አስቀድሞ ተለይቶ ታውቋል ከሚባል የሕዝብ ቁጥር እና የዕድገት ምጣኔ ጋር ተሰናስሎ (ተመሳክሮ) በመሆኑ፣ በአንድ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ወቅት የተሰራ ጥፋት የዘላለም ጥፋት ሆኖ እንደሚቀር ይታወቃል። በመሆኑም በዚህ ዓመት የሚከናወነው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ፣ ከአድልዎ እና ከሸፍጥ ነፃ ይሆናል ቢባል እንኳን፣ ቆጠራው አስቀድሞ በተከናወነው የሕዝብና የቤት ቆጠራ የተፈፀመው የቁጥር እልቂት ጥገኛ መሆኑ የታመነ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) ባለፉት የሕዝብ እና የቤት ቆጠራዎች ሆን ተብሎ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን የቁጥር እልቂት፣ ለሕዝብ ይፋ ለማድረግ እና ወንጀሉ ከፊታችን በሚደረገው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ላይ እንዳይደገም ለማድረግ ሲሰራ የቆየ ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ ከመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም መክሮበታል። ይሁንና በችግሩ ላይ ይኼ ነው የሚባል መፍትሔ ሳይገኝ፣ መንግሥት የሕዝብ እና የቤት ቆጠራውን ለማከናወን ውሳኔ ላይ መድረሱ፣ ንቅናቄያችንን በእጅጉ አሳስቦታል። ስለሆነም አብን ለመንግሥት የሚከተለውን ጥሪ ያደርጋል፡-
፩. መንግሥት የሕዝብ እና የቤት ቆጠራውን ላልተወሰነ ጊዜ እንዲያራዝመው እና ባለፈው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ በአማራ ሕዝብ፣ በአዲስ አበባ ሕዝብ፣ በጉራጌ ሕዝብ እና በቅማንት ሕዝብ ላይ የተፈፀመው የቁጥር እልቂት (numerical genocide)፣ በገለልተኛ ኮሚሽን እንዲጣራ።
፪. የ1998/9 ዓ.ም የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤት ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ እና ከፊታችን የሚከናወነው የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ የሕዝብ ዕድገት ምጣኔ ስሌት ( projection) ከ1998/9 ዓ.ም በፊት የተደረጉ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤቶችን ብቻ መሰረት አድርጎ እንዲከናወን።
፫. የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 449/97 እንዲከለስ፤ በተለይም የአዋጁ አንቀጽ 6 ላይ የተመለከተው የኮሚሽኑ አባላት ስብጥር፣ ተመጣጣኝ እና ሚዛናዊ ውክልና ኖሮት፣ ከመንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ በሕዝብ እና በመንግሥት እምነት የሚጣልባቸው ኢትዮጵያውን ምሁራን ተካተው ኮሚሽኑ እንደገና እንዲቋቋም፡፡
፬. የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለሥልጣን የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 442/97 እንደገና እንዲከለስ እና የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ በሆኑ ባለሙያ ኢትዮጵያውያን እንደገና እንዲደራጅ፡፡
፭. አስር ሺህ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማከፋፈል እምነት ያልተጣለበት የኢትዮጵያ መረብ ደኅንነት ኤጁንሲ (INSA) ያዘጋጀው የመረጃ ማሰባሰቢያና ማደራጃ ሶፍትዌር፣ ከመቶ ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለመቁጠር እምነት ሊጣልበት ስለማይችል፣ በኢንሳ የተመረተው የኮምፒውተር ሶፍትዌር ውድቅ እንዲደረግ እና ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የሕዝብ ቆጠራ መረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ ሶፍትዌር ጥቅም ላይ እንዲውል።
፮. በ1998/9 ዓ.ም በተደረገው ቆጠራ በኃላፊነት የተሳተፉ ግለሰቦች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱና እንዲጠየቁ።
፯. በወልቃይት እና በራያ ቆጠራው ከመከናወኑ በፊት፣ አካባቢዎቹ በፌዴራል መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ እየጠየቅን፤ መንግሥት ጥያቄዎቻችንን ተቀብሎ ለሚወስዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች፣ ንቅናቄያችን አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ከወዲሁ እናስታውቃለን።
መንግሥት ንቅናቄያችን ያቀረባቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች የማይቀበል ቢሆን እና ከላይ የተጠቀሱት የሕግ፣ የተቋማት እና የቴክኖሎጂ ማሻሻያ እርምጃዎች ሳይወሰዱ፣ ቆጠራውን የሚያከናውን ቢሆን፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ውጤቱን የማይቀበለው መሆኑን በአፅንዖት እየገለፅን፣ የአማራን ሕዝብ የፍትኅ እና የእኩልነት ጥያቄዎች ባለመቀበሉ ምክንያት በሕዝብና በቤት ቆጠራ ሂደቱ እና ውጤቱ ላይ ለሚደርሰው ኪሳራ መንግሥት ኃላፊነት የሚወስድ መሆኑን፣ ከወዲሁ እናስታውቃለን።
ቅፅ—13—-የካቲት 11/2011 ዓም
አዲስ አበባ፤ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ