ቀን ጥር 2017
የኢትዮ_ ጅቡቲ ባቡር፣ የታከለ ኡማና የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች የግል ንብረት!!!
ማስታወሻ
የአብይ አህመድ ግፈኛ እና ዘረኛ አገዛዝ የአማራን ህዝብ በጄቶችና በተዋጊ ሄሊኮፕተሮች፣ በድሮኖችና በመድፎች በሚጨፈጭፍበት በዚህ ክፉ ዘመን፤ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ወገቧ ተሰብሮ በተሽመደመደችበት፣ ሰላም እና ደህንነቷ ተናግቶ መኖር አለመኖሯ ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት በዚ ቀውጢ ወቅት፣ የአንድን ድርጅት ጉዳይ አንስቶ ሃተታ ማቅረብ እጅግ ከብዶኝ ነበር። ሆኖም ግን የምድር ባቡር ሰራተኞች ስቃይ የሚለካው በሚሰቃየው ሰው ልክ እንጂ በሌላ ሰው ስቃይ አይደለም የሚል ሙግትና ተማጽኖ ስላቀረቡልኝ “ እያመነታሁም ቢሆን ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ወሰንኩ።
የኢትዮጵያ ጅቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት፣ በትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ በሚኒስቴር አለሙ ስሜ (የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ጸሃፊ የነበረ)፣ ከዛም በታች፣ በኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ስራ አስኪያጅ በኤንጂኔር ህሊና በላቸው ስር የሚተዳደር ድርጅት ነው። ባሁኑ ወቅት ግን ይህ ህጋዊ የእዝና የመዋቅር ስንስለት የምድር ባቡር ድርጅትን አይገዛውም።
ሰራተኞች በምድር ባቡሩ ላይ የሚፈጸመውን ስርአትና ደንብ ያልተከተለ አሰራራ፣ ውንብድና ዘረፋ በተመለክተ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትርም ሆነ፣ ለምድር ባቡር ኮርፖረሽን ቢያሳውቁም፣ በቅርቡ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡርን በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንዲመራ በአብይ አህመድ የተሾመውን እና ተቋሙን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገው ያለውን ታከለ ኡማን የሚያስቆመው ጠፍቷል። ታከለ ኡማ “ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ደጅ ታሳድራለች” እንደሚባለው፣ በአሰራሩ ቅሬታ የሚያሳድሩ ሰራተኞች ስብስቦ “እያንዳንድሽ ለፈለግሽው አካል መናገር ትችያለሽ እኔን ማንም ምንም አያደርገኝም” በማለት እስከመናገር ደርሷል።
የምድር ባቡር ሰራተኞች እንደገለጹልኝ ታከለ ኡማ የኢትዮጵያ ጅቡቲ ባቡር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆኖ ከተመደበ በኋላ በምድር ባቡሩ ላይና በምድር ባቡሩ ውስጥ የሚፈጸመው ውንብድና፣ ሙስና፣ ዘረፋና አድሏዊ አሰራር በከፍተኛ ደረጃ ከማደጉ የተነሳ የራሱንን የምድር ባቡሩን ህልወና ሊናጋ የሚችል መሆኑን ነው።
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዚያት የሚድያ እድል ባገኘሁባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የኢትይጵያ ጅቡቲ ባቡር በተመለከተ በመንግስት ባለስልጣናት የተደራጀ የዘረፋና የኮንትሮባንድ ንግድ ስራዎች የሚሰራበት ድርጅት እንደሆነ ገልጫለሁ። ቀደም ብለው በነበሩት አመታት፣ የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች፣ ጅቡቲ ላይ የተመደበው አምባሳደር ብርሃኑ ጽጋዬ፣ የፈደራል ፖሊሱ አዛዥ ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ የኦሮሞ ጄነራሎች፣ ባለስልጣናትና ባላሃብቶች በአንድ ላይ በመተባበር የምድር ባቡሩን የግል ንብረታቸው አድርገው የኮንትሮባንድና የህገ ወጥ ንግዶች እንዴት ማካሄጃ አንዳደረጉት በተደጋጋሚ አስረድቻለሁ።
የምድር ባቡሩን በመጠቀም፣ ከላይ የጠቀስኩት የዘራፊዎች ቡድን፣ ህገወጥ የጦር መሰሪያ፣ አንደንዛዥ እጽ፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ወርቅና የከበሩ ድንጋይች፣ የኮንትሮባንድ መድሃኒቶች፣ የመኪና እና የማሽነሪ መለዋወጫዎች፣ ብረታ በረቶች፣ ኤሌክትሮኒክ እቃዎች በተደራጀ መንገድ ወደሃገር እንደሚያስገባና አንዳንዶቹን ደግሞ ከሃገር እንደሚያወጣ ከአብይ አህመድና ከሌሎችም የምንግስት ባልስጣናት የተደበቀ ሚስጥር አይደለም።
የኦሮሞ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች የኮንትሮባንድ ንግድ፣ ህጋዊ ነጋዴዎችን ለከፍተኛ ኪሳራ እየዳረገ እንደሆነ ከዚህ ቀደም የደረሰኝ መረጃ ለህዝብ አጋርቻለሁ። በኮንትሮባንድ የሚገባው ብረታ ብረት ኪሳራ ውስጥ የጣላቸው 70 የሚሆኑ በብረታ ብረት ንግድ ተሰማርተው የሚሰሩ ድርጅቶች፣ ከአንድ አመት በፊት በኮንትሮባንድ የብረት ንግድ የተነሳ በደረስባቸው ኪሳራ ስራ እስከማቆም ሊደርሱ እንደሚችሉና በሸዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቻቸውን ስራ አጥ ሊያደርጉ እንደሆነ የሚያሳይ መግለጫ አውጥተው ነበር። ለዚህ ችግር የዳረጓቸው በብርሃኑ ጸጋዬና በደመላሽ ገብረሚካኤል የሚመራው የኦሮሞ የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ድርጊት ነው።
ቀደም ብለው በነበሩት ጥቂት አመታት የኢትዮጵያ ጅቡቲ የምድር ባቡር ለኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች ህገ ወጥ ድርጊት የተመቻቸበት እድል የተገኘው፣ የምድር ባቡሩን የሴኩሪቲና የደህንነት ስራ በሙሉ ሃላፊነት የሚቆጣጠረው የአብይ አህመድ የቀኝ እጅ የሆነው ኮሚሽነር ድመላሽ/ገብረሚካኤል የፌደራል ፖሊስ መሪ ሆኖ ከመሾሙ ጋር ተያይዞ ነው። ደመላሽ የራሱን ታማኝ የፌደራል ፖሊስ አባላት ጅቡቲ ላይ፣ ከጅቡቲ አንስቶ እስከ አዲአ አባባ ባሉት 19 የባቡር ጣቢያዎችና በሚንቀሳቀሰው ባቡር ላይ ጭምር መመደብ በመቻሉ እሱና ተባባሪዎቹ ድርጅቱን ተጠቅመው ያሻቸውን ውንብድና ለመፈጸም የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ አመቻችቷል።
የኦሮሚያ ክልል ራሱን የቻለ ሀገርና መንግስት 40 ኮንቴነር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ያለማእከላዊ መንግስት እውቅና በቀጥታ ከቻይና ገዝቶ ራሱን እና ሸኔን ያስታጠቀው ይህንኑ የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች በውንብድና የተሳሰሩበትን የባቡር መስመር በመጠቀም ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው አብይ አህመድ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ሚኒስትሩን አለሙ ስሜን፣ (ሌላ የኦሮሞ ብልጽግና ታማኝ) ከዛም በኋላ የኦሮሞ ብልጽግና የሙስና ቁንጮ የሆነውን ታከለ ኡማን፣ በየተራ የትራንስፖርትና የሎጂስቲ ሚኒስቴርና የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር ዋና ስራ አስራ አስፈጻሚ አድርጎ የሾማቸው ።
የምድር ባቡር ኩባንያው፣ የዘውግ ማንነቷን ከማላውቀው የኮርፖሬሽኑ ስራ አስኪያጅ ከህሊና በላቸው በስተቀር ባቡሩን በተመለከተ ውሳኔ መስጠት የሚገባቸው ከፍተኛ አመራሮች በቅርበት በሚተዋወቁ የአንድ መንደር የኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች እጅ እንዲወድቅ ተደርጓል።
ይህ አይነቱ፤ ልክ እንደሃገሪቱ ፋይናንስ፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ዘርፉን በኦሮሞ ብልጽግና ሰዎች እጅ የማድረጉ ስራ አብይ አህመድ ሆን ብሎ አቅዶ የፈጽመው መሆኑ ግልጽ ነው። እቅዱ አብይ እያወቀው የተሰራ መሆኑን የሚያረጋገጠው ካልጠፋ የስራ መስክና ስልጣን ታከለ ኡማን የመሰለ፣ የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባና የማእድን ሚኒስቴር በነበረበት ውቅት፣ ራሱ አብይ አህመድ ሳይቀር ሪፖርት በተደረጉለት የሙስና ድርጊቶች የታወቀውን ቀንደኛ ሙስኛ፣ የምድር ባቡርን በመሰለ፣ በሃገሪቱ የኢኮኖሚና የደህንነት ህይወት ዙሪያ ወሳኝ ድራሻ ባለው ተቋም ላይ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርጎ ባልሾመው ነበር።
የጌቶቹ ይሁንታ ተጎናጽፎ ወደምድር ባቡር የመጣው ታከለ ኡማ ከነብርሃኑ ጸጋዬ፣ ደመላሽ ገብረሚካኤል ጋር በመሆን የሙስና፣ የዘረፋውን እና የኮንትሮባንድ ንግዱን ታሪክ ደርሶበት ከማያውቀው እጅግ ወደላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል። ዘረፋውና ውንብድናው እንዳለ ሆኖም ግን የምድር ባቡር ሰራተኞችን ያሳሰበው ጉዳይ ከዚህም የባሰ ሆኗል። የኢትዮ ጀቡቲ ምድር ባቡር ህልውናው ሊያከትም ወደሚችልበት ሁኔታ ታከለ ኡማ እየወሰደው መሆኑ ነው።
እንደሰራተኞቹ መረጃ፤
ታክለ ኡማ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር እውቅና ውጭ የራሱን መዋቅር ዘርግቶ የምደባ ኮሚቴ በማቋቋም ከቲም መሪዎች በላይ ባለው ሰራተኛ ላይ ጥናት ተጠንቶ በአስር ቀን ውስጥ እንዲጠናቀቅ የቃል መመሪያ ስጥቷል። ለእንዲህ አይነቱ ተግባር እንኳን መመሪያ በጽሁፍ አይሰጥም።
ይህ የታከለ ኡማ አዲስ መዋቅር፣ እንደ ተቋሙ ሰራተኞች ከሆነ ፣ ከተቋማዊ አሰራራና አደረጃጀት ያፈነገጠ እና የሀገርን ጥቅምን የሚጎዳ ለጥናቱም ተብሎ የሚወጣው ገንዝብ በከፍተኛ ደረጃ ድርጅቱን ለዘረፋ ያጋለጠ ነው።
ድርጅቱ ከተመሰረተ ባለፉት 6 አመታት ውስጥ የመዋቀር ጥናት ተብሎ ሲጠና የአሁኑን የታከለ ኡማን ጥናት ጨምሮ ሁለተኛው ነው። የመጀመሪያ ጥናት ከ300 ሽ ዶላር በላይ የወጣበት ሲሆን ፣ ውጤቱ በየደረጃው የነበሩ ልምድ ያላቸውን አመራሮች ከማባረርና በሃይማኖት በዘር በጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች ድርጅቱን እንዲቆጣጠሩት ከማድረግ የዘለለ የፈየደው ነገር አልነበረም። ይህ የመዋቅር ጥናት ስራ ላይ ከዋለ በኋላ የባቡሩ ገቢ የቻይና ኩባንያ (A.M.C) በሚያስተዳድርበት ግዜ ከነበረው ከ16-20ሚሊዮን ዶላር የወር ገቢ አሽቆልቁሎ ወደ 10 ሚሊየን ወርዷል።
አሁን በታከለ ኡማ እንዲጠና የተደረገው መዋቀር እንደሰራተኞቹ ገለጻ በ2.2 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየተጠና እንደሆነ ይነገራል። ሙሉ በሙሉ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ከጥቂት አመታት በፊት 300 ሽህ ዶላር ያወጣ የመዋቅር ጥናት ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት 2.2 ሚሊዮን ዶላር መድረስ እንደቻለ ታከለን የሚጠይቀው አካል ግን የለም።
ይህ አዲሱ የታከለ ኡማ መዋቅር ገና ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይሆን፣ ታከለ ኡማ ድርጅቱን ወዴት ሊወስደው እንዳሰበ የሚያሳዩ ፍንጮች እየታዩ ነው። ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን በቀላሉ ተፈልገው የማይገኙ ኤንጂኔሮችን ያስወገደ፣ ተቋሙን ከአንድ መንደር በመጡ አክራሪ ብሄረተኞች የተሞላ እያደረገው ነው። ከገቢ እንፃር የድርጅቱ የወር ገቢ ከጥቂት ጊዚያት በፊት ከነበረው በወር 10 ሚሊዮን ዶላር ወደ 4ሚሊየን ዶላር ማሽቆልቆሉን የድርጅቱ ሰራተኞች ገልጸዋል።
በቅርቡ ታከለ ኡማ የድርጅቱን ትርፋማነት በተመለከተ ለሚዲያ ተቋማት የሰጠው መረጃ፣ ከእውነት የራቀ መሆኑን ሰራተኞቹ የሚቀጥሉትን ዝርዝር ነጥቦች በማስረጃነት ያቀርባሉ።
ታከለ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ትርፍ እገኝተናል በማለት የሰጠውና በማህበራዊ ሚድያ በስፋት የተሰራጨው ዜና በሃሰት የተሞላ የሚያደርገው የሚከተለው ጭብጦች ናቸው።
1ኛ_ የቻይና ኮንትራት ማነጅመንት አንድ መቶ ሰባ ሚሊየን ዶላር(170ሚሊዩ፣ዶላር)ወጪ ሳይከፈል፤
2ኛ_ ለሕንፃ እድሳት የሚወጣውን ሰባት መቶ ሚሊየን ብር ወጪ ያላካተተ፣
3ኛ_ የባቡር የመለዋወጫ እቃዎች ግዢ ሳይፈፀም የተሰላ ቁጥር መሆኑ ነው።
ታከለ ኡማ ከመጣ በኋላ በተቋሙ ውስጥ የሚካሂደው ሙሳና ከመቼውም በላይ እየባሰበት መጥቷል። ለማሳያ ያክል ድርጅቱ የንብረት አወጋገድ ስርአትን ባልተከተለ መንገድ፣ በቃል በሚሰጡ መመሪያዎች የድርጅቱ ተረፈ ምርቶች ለጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ሸጠው እንዲጠቀሙ በመደረግ ላይ ነው።
የግዥ ስርአት የሌለው ስራና ህንጻ ለማሳደስ ሲባል የሚወጣው ወጪ ተቋሙን ለኪሳራ፣እየዳረገው፣ነው። ለምሳሌ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 1.800.000 ዶላራ (አንድ፣ነጥብ፣ስምት፣ሚሊየን፣ዶላር) ያለምንም ኦዲት ወጪ ተደርጓል።
ይህ አልበቃ ብሎ ክታከለ ኡማ ጋር የስጋ ዝምድና ያላቸው ግለሰቦች ያለምንም ውድድር በድርጅቱ የሚቀጠሩበትና በተቀጠሩበት መስክ ሳይሆን ታክለና ጓደኞቹ ዘረፋ ማካሄድ በሚችሉበት መስክ ተሰማርተው እንዲሰሩ ይደረጋል። ለምሳሌ ወ/ት አባቦ መግስቱ የምትባል፣ የታከለ ኡማ የአጎት ልጅ፣ የፕርቶኮል ሰራተኛ ሆና ብትቀጠርም በመደበኛ ስራዋ ላይ ተገኝታ አታውቅም። በታከለ ፈቃድ አንዳንዴ ለበርካታ ሳምንታት ፈቃድ እየተሰጣት በኮንቴነር ኮንትሮባንድ እቃዎች ከጅቡቲ እያስገባች ሞጆ ላይ መቀመጫዋን አድርጋ እንድትቸበችብ ተፈቅዶላታል። ንግዱ የግሏ እንደማይሆን መገመት ከባድ አይሆንም።
ተቋሙን በዘረፋ ለማዳከም ከሚሰራው እኩይ ተግባር በተጨማሪ ችሎታና ብቃት የሌላቸው በዘር የተሰባስቡ ሰዎች በከፍተኛ ሃላፊነት ስራ ላይ መመደባቸው ስራ እንዲበደል እያደረገ ነው። በጥናት ላይ ያልተመሰረቱ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ በማድረግ ተቋሙ ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ እንዲወድቅ እየተደረገ ነው። በቅርቡ የገበያ አዋጭነቱ በሰከነ መልኩ ሳይጠና በደንበኞች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በደረቅ ጭነት ላይ በመደረጉ፣ የተቋሙ ደንበኞች የሸሹበትና የድርጅቱ ገቢ ያሽቆለቆለብት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ጀቡቲ ባቡር ቀደም ባሉት አመታት በመሰረተ ልማት ውድመት፣ በመስመሩ ላይ በእንሳሳት ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ጉዞ ይገታና ይጓተት ነበር። እንዲያም ሆኖ እነዚህ ከጉዞ ጋር የተያያዙ ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ በመፍታት ባቡሩ ከተያዘለት የመድረሻ ሰአት ሲበዛ ግማሽ ሰአት አርፍዶ ይደርስ ነበር። ታከለ ኡማ ወደ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ከተመደበ ወዲህ ከላይ ከተባሉት የጉዞ ችግሮች በተጨማሪ የኮንትሮባንድ እቃ ለማራገፍና ለመጫን ባቡሩ በየቦታው ስለሚቆም፤ ባቡሩ ከስድስት ሰአታት በላይ አርፍዶ ከመዳረሻው መድረሱ የተለመደ ሆኗል። ይህ አሰራራ ተቋሙን ከፍተኛ የገንዝብ ኪሳራ እንዲያስተናግድ አድርጎታል።
በተቋሙ ውስጥ ዘረፋ መጨመሩን እና የመልካም አስተዳደር መጥፋት የተመለከቱና “ለምን ይህ ይሆናል” የሚሉ ሰራተኞች እየታደኑ ከስራ ማባረር፣ ከዛም አልፎ ሰበብ ፈጥሮ ማሳሰር የተለመደ አሰራር ሆኗል። ዛሬ የምድር ባቡር የከፍተኛ የመካከለኛና የዝቀተኛ የስራ ሃላፊዎች የዘውግ ስብጥር 80 ከመቶ ኦሮሞች 15 ከመቶ የሱማሌና የአፋር ተወላጆች 5 ከመቶ አማራ ትግሬና ሌላው የተቀረቱ የኢትዮጵያ ዘውጌ ማህበረሰብ ተወላጆች ሆነዋል። ይህ የሰራተኛ ቅጥርና ምደባ በትምህርት ዝግጅትና በስራ ልምድ ለቦታው በማይመጥኑ በዘር መስፈርት በተመለመሉ ሰዎች በመያዙ የድርጅቱን ህልወና ይበልጥ እያናጋው እንደሆነ በፋይናንስ በአስተዳድር፣ በኦፐሬሽን ስራዎች ዙሪያ በሚታየው መዳከም ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
የታከለ ኡማን ድርጊት፣ ለበላይ አለቃው ለኢንጂኤር ህሊና በላቸውና ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ በማቅረብ አድማጭ ያጡት የድርጅቱ ሰራተኞች ችግራቸውን ከሚስቴር መስሪያ ቤቱ ውጭ ላሉ ተቋማት ለመውስደ ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ከላኩልኝ መረጃ መረዳት ችያለሁ።
እነዚህ የውጭ ተቋማት መፍትሄ እንደማይሰጧቸው ቢያውቁም እርምጃቸውን “ሲሰምጥ ሰምበሌጥ ይዞ ለመትረፍ እንድሚሞክር ሰማጭ” ሆኖ እንደሚታይባቸው እያወቁም፣ በዘር መድሎና ዘርን በተመለከተ እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት፣ “የብሄሮች የእኩል ተጠቃሚነት የሚለውን ህገ መንግስት የተጻረረ ነው” በሚል ለፌደራሽን ምክር ቤት ለማቅረብ ወስነዋል።
ድርጅቱ ላይ ያንጃበበውን የህልውና አደጋ ለተወካዪች ምክር ቤት ለመሰረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ፣ እንዲሁም ያለአግባብ ስብአዊ መብታቸው ተጥሶ ከስራ የተባብረሩትንና በግፍ በእስር እየማቀቁ ያሉትን የስራ ባልደረቦቻቸውን ከእስር ለማስፈታት ጉዳዩን አለም አቀፍና የሃገር ውስጥ ሚድያዎች እንዲውቁት፤ ከዛም አልፎ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነው።
የድርጅቱ ሰራተኞች፣ በኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስሪያ ቤት ውስጥ በማፊያ አደረጃጅት መልኩ ተዋቅሮ በሚንቀሳቀሰው የታከለ ኡማ አስተዳደር ወስጥ ሃሳብ የመስጠት ነጻነታቸው ተገፎ በፍርሃትና በስጋት ተጨማደው ከመኖር አልፈው በታከለ ኡማ ትእዛዝ የተወሰኑት በግፍ ለእስር ተዳርገው የሚሰቃዩ መሆኑ አስታውቀዋል።
ለምሳሌ ዘርን ያነጣጠረ ጥቃት በሚመስል መልኩ በጥር 14 2017 አ.ም በድርጅቱ አጠራር K151±100m “ከአዳማ እስከ ፊጦ ወረዳ በሀዲድ ላይ የተፈጠረው ዝርፊያ ያቀነበራችሁት እናንተ ናችሁ” በሚል ከጉዳዩ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌላቸው 9 ኤንጂኔሮች በታከለ ኡማ ትእዛዝ በሽገር ሴቲ ገላን ፖሊሶ ጣቢያና ፉሪ ፖሊስ ጣብያ እንዲታሰሩ ተደርጓል።
1ኛ፣ኤንጄነር፣መብራቱ፣ደለለኝ
2ኛ፣ኤንጅነር፣ዳዊት ጌታቸው
3ኛ፣ኢንጅነር፣መስፍን አረጋ
4ኛ፣ኢንጅነር፣ቃላብ ወ/ማሪያም
5ኛ፣ኢንጅነር ያሬድ ተስፋዬ
6ኛ፣ኢንጅነር፣ድጋፌ ከበደ
7ኛ፣ኢንጅነር ሀየሎም ታደሰ
8ኛ፣ኢንጅነር፣አስግድ ውበቱ
9ኛኜ፣ኢንጅነር፣እዪኢል ተስፋሁን ናቸው።
እነዚህ 9 ኤንጂኔሮች ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት ተቋሙ ባዘጋጀውና በአዲሳ አበባ ዩንቨርስቲ በተሰጠው ፈተና ላይ ለመገኘት ተቋሙ ባዘጋጀላቸው የሰርቪሽ መጓጓዣ ተጉዘው ፈተናቸውን ሲወስዱ የነበሩ ቢሆኑም፣ ይህ ሃቅ ወደ ጎን ተደርጎ፣ ታከለ ኡማ ድርጅቱን ኦሮሞ ካልሆኑ ኤንጂኔሮች ለማጥራት የጀመረውን እቅድ ተፈጻሚ ለማድረግ ስለታሰበ ብቻ እነዚህ ግለሰቦች በግፍ እስር ቤት እንዲወረውሩ ተደርጓል።
የምድር ባቡሩ ሰራተኞች ህዝብ እንዲያውቃላቸው የፈለጉት በደል ይህን ይመስላል። ሁላችሁም ላልሰሙ በማጋራት አሰሙላቸው። ሚድያዎችም አሰራጩላቸው።
አንዳርጋቸው ጽጌ