የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ለሥራ ጉብኝት ወደ ትግራይ ክልል ጉዞ ሊያደርጉ የነበሩ የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን አባላት በፌደራል መንግሥት ትዕዛዝ ወደ ክልሉ እንዳይጓዙ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ እገዳ ተደርጎባቸዋል ለሚለው የትግራይ ክልል መንግሥት ቅሬታ ከሱ ዕውቅና ውጪ መሆኑን አስታውቋል።
የፌደራል መንግስቱ በውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኤዥያና ፓስፊቅ ሀገራት ጉዳዮች መምሪያ እና የቻይና ፔኪንግ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሚስዮን አማካኝነት ከወራት በላይ ከግዛቲቱ ኃላፊዎች ጋር የደብዳቤ ልውውጥና ውይይት አድርጎ ለትግራይ ክልልም በደብዳቤ አሳውቆ በህጋዊ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው።
በቻይና የሻንሺ ግዛት ምክትል ሊቀመንበር የሚመራው ስድስት አባላት ያሉት ይኸው የቻይና የሻንሺ ግዛት ልዑካን ቡድን ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጋር በልማት እና አቅም ግንባታ ዙሪያ ልዩ ልዩ የትብብር የመግባቢያ ሰነዶችንም እንዲፈራረሙ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅድመ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።
ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ ለምን ተከለከሉ?
ችግሩ የተከሰተው በ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይሆን ከሱ እውቅና ውጭ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የጥበቃ አካላት ዘንድ የመረጃ መናበብ ክፍተት የፈጠረው ችግር ይመስላል። ጉዳዩን ከኤርፖት ጥበቃ አካላት እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር በመነጋገር የምናጣራው ይሆናል።
ችግሩ ከተከሰተ በኃላም የቻይናው የልዑከን ቡድን በትዕግስት እንዲጠብቅ በማድረግ እና ከትግራይ ክልል መስተዳደር ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር በምክትል ፕሬዘዳንት ማዕረግ የትግራይ ክልል የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ተከስተ የመግባቢያ ሰነዱን አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እንዲፈራረሙ በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነቱን በአግባቡ ተወጥቷል።
(አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ)