የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ አሞላል ሂደትን በተመለከተ ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ውይይቶች ውጤት አልባ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።
በዚህም ከግደቡ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ያለው አለመጋባባት እየጎላ መጥቷል።
ትናንት የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች የልዑክ ቡድናቸውን ይዘው አሜሪካ ከደረሱ በኋላ በጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት አድርገው የጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
የጋራ መግለጫው ምን ይላል?
በውይይቱ ላይ ከሶስቱ ሃገራት የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ባሻገር የአሜሪካ የገንዘብ ሚንስትር እና የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ተሳታፊ ነበሩ።
የሶስቱ ሃገራት ሚንስትሮች በግድቡ አሞላል እና ኦፕሬሽን ላይ የሁሉንም ፍላጎት በሚያረካ መልኩ በትብብር እና በተቀናጀ መልኩ ለመስራት ጽኑ አቋማቸውን ገልጸዋል ይላል ትናንት ምሽት በዋሸንግተን የወጣው መግለጫ።
የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮቹ በየውሃ ሚንስትሮች ደረጃ የሚደረግ አራት መንግሥታዊ የቴክኒክ ስብሰባዎችን ለማካሄድ የተስማሙ ሲሆን፤ የዓለም ባንክ እና አሜሪካ ድጋፍ እንዲሰጡ እና በውይይቶቹ በታዛቢነት እንዲሳተፉ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን መግለጫው ያትታል።
በተጨማሪም ሚንስትሮቹ ጥር 6 2012 ዓ.ም. ድረስ ከስምምነት ለመድረስ እንደሚሰሩ እና ኅዳር 29 እና ጥር 4 ዳግም በዋሽንግተን ለመገናኘት እና ሂደቱን ለመገምገም ቀጠሮ ይዘዋል።
እስከ ጥር 6 2012 ዓ.ም. ስምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ በ2008 ተፈርሞ የነበረው የጋራ አቋም መግለጫ አንቀጽ 10 ተግባራዊ እንዲሆን ሚኒስትሮቹ ተስማምተዋል።
• ሱዳን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ አቋሟን ትቀይር ይሆን?
• በአባይ ግድብ ላይ ለዓመታት የተካሄድው ውይይት ውጤት አላመጣም፡ ግብጽ
የ2008ቱ ጋራ አቋም መግለጫ አንቀጽ 10 ምን ይላል?
ስምምነቱ የተፈረመው በሱዳን ካርቱም ሲሆን፤ የመርሆ መግለጫ አንቀጽ 10
ሶስቱ ሃገራት በአተረጓጓመ ወይም አተገባባር ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በመልካም መንፈስ ላይ ተመስረተው በውይይት ወይም በድርድር ይፈታሉ። ሶስቱ አካላት አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ቢሳናቸው፤ አደራዳሪ ሊጠይቁ ወይም ጉዳዩ ለየ ሃገራትቱ መሪዎች ወይም ለርዕሳነ ብሔሮቻቸው ሊያሳውቁ ይችላሉ ይላል።