Breaking News
Home / Amharic / 53 ቢሊዮን ብር ተበላ!!

53 ቢሊዮን ብር ተበላ!!

53 ቢሊዮን ብር ተበላ!! በአዲስ አበባ ከተማ ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወጪ ሆኗል የተባለው 53 ቢሊዮን ብር ምን ላይ ወጪ እንደሆነ እንደማይታወቅ ተገለጸ።
******************
BBC Amharic
ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወጪ ሆኗል የተባለ 53 ቢሊዮን ብር ሳይወራረድ ቀረ
 
12 የካቲት 2021
 
በአዲስ አበባ ከተማ ለተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወጪ ሆኗል የተባለው 53 ቢሊዮን ብር ምን ላይ ወጪ እንደሆነ እንደማይታወቅ ተገለጸ።
 
ይህን ያለው ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለባለ እድለኞች ተላልፈው የሚሰጡበትን ውስብስብ ጉዳዮች እንዲያጠና የተጠየቀው ቡድን ነው።
 
ይህን ጥናት ያካሄደው ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ሲሆን፤ የጥናት ቡድኑን ሲመሩ የቆዩት ቱሉ ቶላ (ዶ/ር) ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና መኖሪያ ቤቶቹ ተላልፈው የሚሰጡበትን ውስብስብ ችግር ለማጥናት ከአራት ወራት በላይ መፍጀቱን ይናገራሉ።
 
በጥናት ውጤቱም መሠረት ለጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ወጪ ሆኗል የተባለ 53 ቢሊዮን ብር አለመወራረዱን፣ አልያም ለወጪው ሰነድ አለመገኘቱን ቱሉ ቶላ (ዶ/ር) ለቢቢሲ ተናግረዋል።
 
በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ21ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው መገኘታቸውን በጥናት መረጋገጡን አስታውቆ ነበር።
 
“ለ15 ዓመታት ኮንዶሚኒየም እየጠበቅኩ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ” የአዲስ አበባ ነዋሪ
በአዲስ አበባ ከ21 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘው ተገኙ
በአዲስ አበባ ሕገወጥ የመሬት ወረራ የወጣው ሪፖርት “ሃሰተኛ” ነው- የቀድሞው ምክትል ከንቲባ
 
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ 13 ሚሊየን 389 ሺህ 955 ካሬ ወይም 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት በሕገ-ወጥ መያዙን አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም 322 ግንባታቸው ያለቀና ያላለቀ ህንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን እና 14,641 መኖርያና ለንግድ የተከራዩ የቀበሌ ቤቶችን ያለ አግባብና በሕገ-ወጥ ይዞታነት የሚገኙ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
ቱሉ ቶላ (ዶ/ር) መንግሥት ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ ያለውን ውስብስብ ችግር ለመለየት በገለልተኛ አካል ጥናት እንዲካሄድ ሲወስን ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መመረጡን ይናገራሉ።
 
በጥናቱ ላይ 7 የዩኒቨርሲቲው መምህራንን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ3ሺህ 500 ሰዎች በላይ በጥናቱ ላይ መስራታቸውንም ጠቅሰዋል።
 
ጥናቱ ምን አመላከተ?
 
ከአራት ወራት በላይ የፈጀው ጥናት ከ1996/97 ጀምሮ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ተመልክቷል።
 
በከተማዋ የሚገኘው እያንዳንዱ የጋራ መኖሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ የቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የባንክ እና የባለቤትነት ሰነድ ጋር የማነጻጸር ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ።
 
ይህ የአጥኚ ቡድን በከተማዋ የተገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለተጠቃሚዎች ተላልፈው ከሚሰጡበት ሂደት በተጨማሪ ለግንባታ የተደረገውን ወጪ እና በመሬት ላይ ያለውን የግንባታ ሂደት ደረጃ መርምሯል።
 
“ባካሄድነው ጥናት እንዳረጋገጥነው ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ወጪ ተደርጓል የተባለ 53 ቢሊዮን ብር ለምን ወጪ እንደተደረገ የሚያሳይ ሰነድ ለም። የፌደራል ኦዲተሮችም ሰነድ አጥተው ኦዲት ሊደረግ አይችለም ብለው ትተውታል። ታስቦበት ማረጋገጫ እንዲጠፋ ተደርጓል” ይላሉ ቱሉ (ዶ/ር)።
 
እንደ የጥናት ቡድኑ መሪ ከሆነ እያንዳንዳቸው እስከ 30 ቤቶችን ሊይዙ የሚችሉ 28 ሕንጻዎች (ብሎኮች) ሳይገነቡ ቀርተዋል።
 
“እነዚህ ያልተገነቡ ሕንጻዎች ለመገንባት ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተደርሶ ነበር። እነዚህ ቤቶች ለምን ሳይገነቡ እንደቀሩ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ወይም የኮርፖሬሽኑ ቦርድ የያዘው ቃለ ጉባኤ የለም። ክፍያ መፈጸሙን ወይም አለመፈጸሙን የሚያሳይ ሰነድ ጠፍቷል። ይህ የሚያመላክተው ክፍያ ሳይፈጸም እንደማይቀር ነው።” ይላሉ።
 
ቱሉ (ዶ/ር)፤ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ እና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች 99 ሕንጻዎች ጠፍተዋል ተብሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መገለጹን አስታውሰው፤ ይህን በተመለከተ የፌደራል ኦዲተሮች ከ2008 ጀምሮ የኦዲት ሥራ ሲሰሩ ቢቆዩም የተገኘ ውጤት አለመኖሩን በጥናታችን አረጋግጠናል ይላሉ።
 
ወጪ ተደርጎ ሰነድ አልተገኘለትም የተባለው 53 ቢሊዮን ብር ግንባታቸው እንዲፈጸሙ ከስምምነት የተደረሰባቸው ይሁን እንጂ በተጨባጭ መሬት ላይ ግንባታቸው ያልተፈጸሙ ቤቶች ድምር ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
 
‘… ተጠያቂነት ከሌለ ከባድ ችግር ነው።’
 
ቱሉ (ዶ/ር) በአገሪቱ ከፍተኛ ምዝበራ ከተፈጸመባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ ቤቶች ግንባታ መሆኑን ከዚህ የጥናት ውጤት መረዳታቸውን ይገልጻሉ።
 
“የተገነባው ቤት ሰነድ የለውም፤ ለተጠቃሚ ተላልፎ ተሰጥቷል ሲባል እንዴት ተላልፎ እንደተሰጠ አይታወቅም። አንዳንዱ ቤት የባለቤትነት ስነድ አለው የባንክ ሰነድ ደግሞ የለውም። እንደዚህ አይነት ውስብስ ነገሮች ምዝበራ መፈጸሙን የሚያመላክቱ ናቸው። ከፍተኛ ሌብነት የተፈጸመበት ቦታ ነው” ብለዋል።
 
የጥናት ቡድኑ መሪ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጄክት በከፍተኛ ውስብስብ ችግር ውስጥ ተቆላልፎ ስለቆየ የሕዝቡን የቤት እጦት ችግር መቅረፍ አለመቻሉን ይናገራሉ።
 
“አንድን መስሪያ ቤት የሚያስተዳድር የሥራ ኃላፊ ከተጠያቂነት ለመዳን መረጃ የሚሰውር ከሆነ ከባድ አደጋ ነው። ለሚጠፋ ሰነድ ተጠያቂነት ከሌለ ከባድ ችግር ነው”
 
ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የተወጣጠው አጥኚ ቡድን የጋራ መኖሪያ ቤትን በተመለከተ ያደረገው ጥናት ውጤት ከ2ሺህ በላይ ገጽ ያለው ሲሆን፣ ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ ማድረጉንም ቱሉ ቶላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.