የኢትዮጵያ ኖሚናል ጂዲፒ (የዋጋ ንረትን ታሳቢ ያላደረገ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት) በዶላር ሲተመን፣ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ከነበረበት 207 ቢሊዮን ዶላር በሦስት ወራት ውስጥ ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር መውረዱ ተገለጸ፡፡
የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ከመደረጉ አንድ ወር በፊት ማለትም በሰኔ 2016 ዓ.ም. የአገሪቱ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በገንዘብ (በዶላር) ሲሰላ 207 ቢሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ከተደረገ በኋላ በ2017 ዓ.ም. መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ወደ 100 ቢሊዮን ዶላር መውረዱን የገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው የሩብ ዓመት አጠቃላይ የመንግሥት የዕዳ ሰነድ አስታውቋል።
የአገሪቱ ጂዲፒ በዶላር ሲተመን ያሽቆለቆበት ምክንያትም ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ተግባራዊ በመደረጉ እንደሆነ ሰነዱ ያስረዳል።
በዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. የአገሪቱን ጂዲፒ 32.9 በመቶ ይዞ የነበረው አጠቃላይ የመንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ (Public Debt) በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. ወደ 50.3 በመቶ አሻቅቧል።
የመንግሥት (የአገሪቱ) የውጭ ዕዳ መጠን ለብቻው ተነጥሎ ሲታይ፣ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ከነበረበት 28.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ 31 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያለ ሲሆን፣ ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። አንደኛው ምክንያት ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተግባራዊ መደረጉ ሲሆን፣ ሌላው በተጠቀሱት ሦስት ወራት ውስጥ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጅት (IMF) እና ዓለም ባንክ በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ብድር የተለቀቀለት መሆኑ ናቸው።
በዚህ ምክንያት የውጭ ብድር ክምችቱ በ7.5 በመቶ ከመጨመሩ ባለፈ፣ የውጭ ምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ የአገሪቱ ጂዲፒ በዶላር ሲተመን፣ በሰኔ ወር ከነበረበት 207 ቢሊዮን ብር በመስከረም ወር 2017 ወደ 100 ቢሊዮን ብር በማሽቆልቆሉ፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከጂዲፒው ጋር ያለው ጥምርታ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. የአገሪቱ የውጭ ዕዳ (የአገር ውስጥ ዕዳን ሳይጨምር) ከጂዲፒው ጋር የነበረው ጥምርታ 13.9 በመቶ ሲሆን፣ በመስከረም 2017 ዓ.ም. ላይ ግን ወደ 30.9 በመቶ ማደጉን ሰነዱ ያመለክታል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭ ዕዳ ከጂዲፒው ያለው ጥምርታ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የዓለም ባንክ ለደሃ አገሮች ካስቀመጡት 30 በመቶ እንዳለፈ ከዚሁ መንግሥታዊ ሰነድ ለመረዳት ተችሏል።
በተመሳሳይ የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ ከጂዲፒው ያለው ጥምርታም ለደሃ አገሮች ከተቀመጠው ጣራ ማለፉን ሰነዱ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የውጭ ምንዛሪ ለውጡ ከተደረገ በኋላ የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ መጠን በዶላር ሲሰላ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል። የመንግሥት የአገር ውስጥ ዕዳ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ከነበረበት 2.29 ትሪሊዮን ብር ወደ 2.3 ትሪሊዮን ብር ያደገ ቢሆንም፣ በዋናነት በውጭ ምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የአገር ውስጥ ዕዳው በዶላር ሲተመን በሰኔ ወር ከነበረበት 39.9 ቢሊዮን ዶላር ወደ 19.8 ቢሊዮን ዶላር ማሽቆልቆሉን መረጃው ያመለክታል።