Breaking News
Home / Amharic / ፋኖ የማክሰኚት ከተማን ተቆጣጠረ!

ፋኖ የማክሰኚት ከተማን ተቆጣጠረ!

ሰበር አዲስ ዜና:-

የማክሰኝት በፋኖ ቁጥጥር ስር መዋል እንዲሁም የብአዴን የታችኛው እርከን በክልሉ ለተፈጠረው ቀውስ ዋና ተጠያቂዎች የክልሉ የላኛው እርከን ባለስልጣናትና የቢሮ ኃላፊዎች በመሆናቸው ስልጣን ይልቀቁ ሲሉ ለቋሚ ኮሚቴ አመራሮች እና ለአፈ ጉባኤዋ ስለመጠየቃቸው/
የአማራ ፋኖ በጎንደር ማክሰኝት ከተማን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረ::

ፋኖ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከዓብይ አህመድ ወራሪ ሰራዊት እና ከብልጽግና ተላላኪ የወረዳው አመራሮች ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ መግባቱም ተገለጿል:: የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነጋ ብርኃኑ በትላንትናው ዕለት የአካባቢው የፋኖ መሪና አስተባባሪ የሆነውን ፋኖ አደባባይ አበበ ከከተማው ወጣ ብሎ ወደ በለሳ ወረዳ መገንጠያ ልዩ ስሙ አርባያ በሚባለው አካባቢ በጉዞ ላይ እንዳለ ለዓብይ አህመድ ወራሪ ወታደሮች ጥቆማ በመስጠት መንገድ ላይ ተከቦ እንዲታሰር ማድረጉ በፋኖዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን በመፍጠሩ ከተማዋን መቆጣጠራቸው ሲነገር በአስቸኳይ ካልተለቀቀ ከተማውን ለቀው እንደማይወጡ ነው ያስታወቁት::

ፋኖዎቹ አመራራቸው በአስቸኳይ እንዲፈታ ለአስተዳደሩ ቢጠይቁም ከወረዳዋ አመራሮች በበኩላቸው “እንድንፈታው በቅድሚያ ፋኖ ከተማዋን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ይውጣ” የሚል ድርድር ውስጥ በመግባታቸው ነገሩ መካረሩ ታውቋል::

በአሁኑ ሰዓት በፋኖ ዓለሙ ጎዳዳው የሚመራው የፋኖ ኃይል ከተማዋን ቁልፍ ቦታዎች ጨምሮ የወረዳውን የብልጽግና ጽህፈት ቤትን እና ቁልፍ የአስተዳደር ቢሮዎችንም በመቆጣጠር የራሱን ኬላ ዘርግቶ በከተማዋ መግቢያ ላይ ፍተሻ መጀመሩም ተሰምቷል::

በዚህ የተደናገጡት የከተማዋ አመራሮችና የፖሊስ አዛዦች አካባቢውን ለቀው መሸሻቸው ነው ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ያመለከቱት:: የአማራ ፋኖ በጎንደር ሃምሌ 11 ቀን ከጧቱ 1:10 ጀምሮ ነው 30 ደቂቃ ባልሞላ ኦፕሬሽን ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ማክሰኚትን የተቆጣጠረው::

ከውጥረቱ ጋር በተያያዘ የከተማዋ እንቅስቃሴና ከባህር ዳር ጎንደር ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን ሕዝቡ የፋኖው አመራር በአስቸኳይ እንዲለቀቅ አደባባይ በመውጣት አጋረቱን እያሳየ ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ የከተማው አስተዳዳሪ ነጋ ብርኃኑ በመኪና ሲጓዝ ተኩስ ተከፍቶበት ለጥቂት ቢያመልጥም ልጁ ግን በፋኖዎች ቁጥጥር እጅ እንደሚገኝ እና መሪያቸው ካልተለቀቀ “የኦሮሙማው መንግስት ተላላኪ በሆኑ በቀሪ የወረዳው አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውንም ነው መረጃዎች የጠቆሙት::

በዚህ የተደናገጠው የብልጽግና አገዛዝ ተጨማሪ የጸጥታ ኃይላትን ከአዘዞ እና ከአዲስ ዘመን አካባቢ በብዛት ወደ ማክሰኚት ማስጠጋቱም ታውቋል:: ኦሮሙማው ቀውሱን በኃይል ለመፍታት የሚሞክር ከሆነ ወደ መላው ጎንደር ሊስፋፋ ይችላል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ክልል ዓመታዊ የምክር ቤት ስብሰባውን በነገው ዕለት እንደሚያካሂድ ሲነገር ከዛ በፊት ዛሬ የቋሚ ኮሚቴዎች የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቶች እየተሰሙ መሆናቸው ተገልጿል::

በዚህ የቋሚ ተጠሪ የሴክተር መስሪያ ቤቶች በክልሉ በሰሯቸው መሰረተ ልማቶችና ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ የሚያቀርቡትን ሪፖርት በማዳመጥ እና በመገምገም የክልሉ አመራሮቹ ይወያያሉ ተብሎ ቢጠበቅም ውይይቱ ወደ ፖለቲካው ቀውስ እና የክልሉ አሁናዊ ሁኔታ በማጋደል በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ, በልዩ ሃይል መፍረስ, በፋኖ ላይ በተከፈተው ዘመቻ, አርሶ አደሩ በገጠመው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት ችግር እንዲሁም የወሰን እና ማንነት ችግር ያለባቸው ጉዳዮች እስከዛሬ አለመፈታትን በመሳሰሉ በርካታ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጎልተው የተነሱ ጥያቄዎችና ሃሳቦች ላይ ሲወያይ መዋሉ ነው የተነገረው::

በዚህም አሁን ላለው ቀውስ የክልሉ ስራ አስፈጻሚ አመራሮች እንዲሁም የቢሮ ኃላፊዎች በዋናነት ተጠያቂ በመሆናቸው ከአመራርነት ጭምር መነሳት አለባቸው የሚል ጠንካራ ሃሳብ ተነስቷል:: በነገው የክልሉ ምክር ቤት አጠቃላይ ስብሰባም ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ እና ሌሎችም ዋና አመራሮች መልስ እንዲሰጡ ተጠይቋል::

ለአብነትም “ከልዩ ኃይሉ መበተን ጋር በተያያዘም ምክር ቤቱ ሳያውቅ ጥቂት አመራሮች ከፌደራል መንግስት ጋር ተነጋግረው ያስፈጸሙት በመሆኑ እስከዛሬ ላለው ቀውስ ስራ አስፈጻሚው ነው ተጠያቂው” የሚል አስተያየት ነው የቀረበው:: “ምንም እንኳ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ስብሰባ ጠርቶ አስፈላጊውን ማብራሪያ እንዲሰጥ ለስራ አስፈጻሚው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብለትም ጆሮ ዳባ ከማለቱም ሌላ ችግሩ ሲፈጠር አምኖበት የወሰነው ውሳኔ ከሆነ ለሕዝብ አደባባይ ወጥቶ ከማስረዳት ይልቅ አመራሩ ሄዶ የተደበቀው መከላከያው ጉያ ውስጥ ነው” በማለት ተተችቷል::

ልዩ ኃይሉ ከተበተነ በኋላም አሁን ላይ “ከሕወሃት አንጻር እና ሌላም ስጋት አለብን” በሚል የጸጥታ አካላት ስልጠና ስራ አስፈስፈጻሚው እንዲደረግ የወሰነው ይህን ችግር እራሱ የፈጠረው በመሆኑ ነው” የሚልም ተቃውሞ ቀርቦበታል:: ፋኖን በተመለከተም “ፋኖ ምን ያድርግ? ፋኖ ትግላችሁን ነው እየታገለላችሁ ያለው:: ፋኖን እናጥፋ, ፋኖን እንታገል, ፋኖ ላይ ዘመቻ ይከፈት የምትሉት ነገርም አግባብነት የለውም::ፋኖ የናንተን ትግል ነው እየታገለላችሁ የሚገኘው ስንል ማሳያው አዴፓ ከአሁን ቀደም ተቀብያቸዋላሁ ያላቸው በርካታ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ነበሩ::

በወቅታዊነትም የሚታዩት አሁን የወልቃይት ጠለምት ራያና የዋግ አካባቢ የመንነት ጥያቄዎችን ነው ፋኖዎች ያነሱት:: በተደጋጋሚም የፋኖ አባላት እነዚህ አካባቢዎች ዋስትና ካላቸው የአማራ ማንነታቸው ተረጋግጦ የሚመለሱ ከሆነና ውሳኔ ከተሰጠባቸው ወደ መደበኛ ሕይወታችን እንመለሳለን ብለዋል:: እናንተ ናችሁ መተማመን ያቃታችሁ ስለዚህ አሁን ፋኖን እየታገለ ያለው የእናንተን ትግል ነው::

እናንተ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብላችሁ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች በማዕቀፍ ይዘናቸዋል በማዕከል ይፈታሉ ነው የምትሉት:: እስከመቼ ድረስ ነው ይህ ማዕቀፍ የምትሉት የሚቀጥለው? በአንድ ሌሊት በርካታ ክልሎች ተፈጥረው በሚያድሩበት ሁኔታ የክልል ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እያገኝ በሚታይበት አግባብ እነዚህን የወልቃይትና ራያ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸውን ችግሮች ለዓመታት መፍታት እና እልባት መስጠት ያልተቻለው ለምንድነው? ይዋል ይደር ባላችሁ ቁጥር በማዕቀፍ ይታያል ባላቹ ቁጥር በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳ እየተፈጠረ ችግሩ እየተደራረበና እየተወሳሰበ መጥቷል” ሲሉ ተችተዋል:: ሌላው ከክልሉ ምክር ቤት ዕውቅና ውጪ መከላከያው ህግ ማስከበር በሚል ወደ ክልሉ የገባበት ሁኔታም ነገ በሚጀመረው የክልሉ ምክርቤት ስብሰባ ላይ እንዲብራራ ለክልሉ አፈ ጉባኤዋ እና የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተጠይቋል:: ከዚሁ ሃሳብ ጋር በተያያዘ የተነሳው ሌላው ሞባች ጥያቄ “አሁን መከላከያው ኦፕሬሽንኔን አጠናቅቄያለሁ ብሎ ቢወጣ ከዛ በኋላ በነጻነት የምታስተዳድሩት አካባቢ ይኖራል ወይ?

በተለይም እገሌ የተባለን በማህበረሰቡ ዘንድ ቅቡል የሆነ የፋኖ አመራር ቢገደል /የፋኖዎችን ስምና አካባቢ ቃል በቃል በመጥቀስ/ የዛን አካባቢ ሕዝብ እና ክልሉን ማስተዳደር እንችላለን ብላችሁ ነው የምታስቡት? እንደኛ በጦርነት እና ዘመቻ ሳይሆን በፖለቲካ ውይይት ነው ችግሩና ቀውሱ ቢፈታ የሚሻለው” የሚል ጠንካራም ጥያቄና አስተያየትም ለዋና አመራሮቹ ተነስቷል:: ከአርሶ አደሩ ከፍተኛ የማዳበሪያ እጥረት ጋር በተያያዘ ዋና የችግሩ ምንጭ ነው ያሉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ከስልጣን እንዲለቅ ጭምር ጠይቀዋል:: “የቢሮው ኃላፊ ስራውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ምክር ቤቱን ዋሽቷል” የሚል ጠንካራ አስተያየት ጭምር የተሰነዘረ ሲሆን “ገበሬው በ 14ተኛው እና 15ተኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ የቀረ የጅራፍ አብዮት አማራ ክልል ውስጥ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲነሳ ያደረገው የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ በተደጋጋሚ ምክር ቤቱን በመዋሸቱ ነው” የሚለውን የተሰብሳቢውን ዱላ ቀረሽ ትችትን እና ወቀሳ መቋቋም ያቃተው የቢሮው ኃላፊ ስብሰባውን አቋርጦ ወጥቶ አየር ወስዶ እንዲመለስ አስገድዶታል::

ይህ ነውረኛ ኃላፊ ክልሉንም ፌደራል መንግስቱንም በመዋሸት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ቀድሞ እንዳይደረግ እንቅፋት በመሆኑ አሁን ላለው የማዳበሪያ እጥረት ችግር እንዲሁም ማዳበሪያ ለወለደው የክልሉ የጸጥታ ቀውስ ዋና ተጠያቂ ነው የሚል የወቀሳ ውርጅብኝ ወርዶበታል:: እነዚህ ሁሉ አጀንዳዎች ነገ በሚጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል::

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.