Breaking News
Home / Amharic / ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ታወቀ !

ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ታወቀ !

ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ!
**************************
የአሸባሪው ህወሓት ኃይሎች በፀጥታ መዋቅሩና ህዝቡ መካከል ያለውን መተማመን ለመሸርሸር የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጩ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ መላው ህዝብና የፀጥታ መዋቅሩ ከመቼውም በተሻለ ተናበው እየሰሩ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ ለፀጥታ አካላትና ለህዝቡ መናበብ ዋና ማሳያ አድርገው ያነሱት በግንባር እየተገኘ ያለውን ድልና በዜጎች ጥቆማ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉትን የሽብር ቡድኑ አባሪ ወንጀለኞች ነው።
ለሽብር ማስፈፀሚያ ሊውሉ የነበሩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች እንዲሁም ተመሳስለው የተሰሩ የፌደራልና የክልል ልዩ ኃይሎች የደንብ ልብሶች በህብረተሰቡና በፀጥታ መዋቅሩ የጋራ ትብብር ሊያዙ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በግንባር እየተገኘ ባለው ድልም ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሽብር ኃይሎች በወገን ኃይል እየተደመሰሱ ከጥቅም ውጪ መደረጋቸውንና በክፍለ ጦር ደረጃ ያደራጃቸው የሽብር ቡድኑ ኃይሎችም እንዲበተኑ መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የሽብር ቡድኑ በሚሌ እና ወረኢሉ ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራዎች በወገን ኃይል ተመክተው ሳይሳኩ መቅረታቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

የሽብር ቡድኑ በጦርነት ያጣቸውን ድሎች በትግራይ ያልተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ደጋግሞ እያነሳ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖው እንዲበረታ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከሽብር ኃይሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ዜጎች በብሔራቸው ተለይተው በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ በሽብር ቡድኑና በውጭ ኃይሎች የሚናፈሰው ወሬም ፍጹም ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን የጠቀሰው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት የሌለው አንድም ሰው በቁጥጥር ስር አልዋለም ብሏል። በተቃራኒው የአሸባሪው ህወሓት ኃይሎች በወረራ በያዟቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሽብር ቡድኑ ከበባ ውስጥ ሆነው ግፍ እየተፈፀመባቸው መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
 
ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም በሽብር ቡድኑ ከበባ ውስጥ የሚገኙ ከ7 ሚሊዮን በላይ የአማራ እና የአፋር ክልል ነዋሪዎች እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ እና መከራ ከአድሏዊነት ነፃ ሆኖ ሊያወግዘው እንደሚገባ በመግለጫው ላይ ተነስቷል።
ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለወገን ኃይልና ለተፈናቃዮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ መቀጠሉን ያነሱት ሚኒስትሩ የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የቀደሞ ሰራዊት አባላትና ወጣቶችን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዘማቾች የመከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኃይሎችን እንዲቀላቀሉ በማድረግ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ምንጭ: ዋልታ
ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.