Breaking News
Home / Amharic / ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ (Neurologist in Amsterdam) የአስራት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ!

ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ (Neurologist in Amsterdam) የአስራት ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ!

የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መቋቋሙን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ባለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት አማራ-ጠል ኃይሎች የፈጠራ ትርክቶች ደርሰውና የአማራን ሕዝብ ድምጽ-አልባ አድርገው ለከፍተኛ ጉዳት ዳርገውት ኖረዋል። ይሁንና ሕዝባችን ድምጽ እንዲያገኝ አሥራት በተቆርቋሪ ልጆቹ ተመስርቶና በአማራ ሕዝብ ወዳጅ ኢትዮጵያውያን ተደግፎ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲ ድምጽ በመሆን ይኸው ከአንድ ዓመት በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ይህንን የሕዝብ ሚድያ ከምሥረታው አንስቶ ሕዝብን በማስተባበር ከዚህ ያደረሰው መሥራች ኮሚቴ፤ በዘላቂነት አመራር ሊሰጥ የሚችል፤ የማኅበረሰባችንን አስረጫጨት፣ ስብጥርና አደረጃጀት ያገናዘበ ጠቅላላ ጉባዔ አዋቅሯል። ይህ ፶፩ (ሃምሳ አንድ) አባላት የሚኖሩት ጠቅላላ ጉባዔ በኢትዮጵያ ካለው ሕዝብ የተውጣጡ ግለሰቦች፣ በተለያዩ ክፍላተ-ዓለም ከሚኖረው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ከተውጣጡ ግለሰቦችና በማኅበረሳባችን ከተለያዩ አደረጃጀቶች ወኪሎች የተዋቀረ ነው። ጠቅላላ ጉባዔው የተለያዩ የስራ ክፍሎች ሲኖሩት፤ በሰብሳቢ፣ በምክትል ሰብሳቢና በጸሐፊ ይመራል።

ጠቅላላ ጉባዔው ከአባላቱ መካከል፤ ፲፭ (አሥራ አምስት) ግለሰቦች የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት በማድረግ በድምጽ ብልጫ መርጧል። ከ፲፭ቱ መካከል ዶ/ር ሰማኸኝ ጋሹና ዶ/ር አበበች በላይ ቦርዱ እራሱን እያዋቀረ በነበረበት ሂደት ላይ በመልቀቃቸው ምክንያት በምትካቸው በተጠባባቂነት በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠው የነበሩት አቶ ፍስሐ ወርቁና አርቲስት ቤተልሔም ዳኛቸው ተተክተው በቦርድ አባልነት እንዲያገለግሉ ተወስኗል።

ይህም የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በ፲፩ (አስራ አንድ) የሥራ መደቦች እንደሚከተለው ተዋቅሯል።

1ኛ) ዶ/ር አሰፋ ነጋሽ (ሊቀመንበር)፣
2ኛ) አቶ ተፈሪ ጋሻው (ም/ሊቀመንበር)፣
3ኛ) አቶ ግዛቸው ምትኩ (ጸሐፊ)፣
4ኛ) አቶ ዘላለም ስንሻው (ፋይናንስ)፣
5ኛ) አቶ ሰለሞን አያሌው (ህግ፣ ስነምግባርና ቁጥጥር)፣
6ኛ) አቶ እሸቱ ቢያድጎ (የሰው ሀይልና አስተዳደር)፣
7ኛ) ዶ/ር ጋሻው አያሌውና አቶ ፍስሐ ወርቁ (ሚዲያ፣ ቴክኖሎጂና ስነዳ)፣
8ኛ) ልጅ ተድላ መላኩ (የሕዝብ ግንኙነት)፣
9ኛ) ዶ/ር አክሎግ ቢራራ (አድቮኬሲና የውጭ ግንኙነት)፣
10ኛ) አቶ በሪሁን አዳነ (ምርምር እና አቅም ማጎልበት)፣
11ኛ) ዶ/ር ደረጀ ተክለማርያም፣ ወ/ሮ ኤደን ሲሳይና አርቲስት ቤተልሔም ዳኛቸው (ማደራጃና የሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማሰባሰብ)፣
12ኛ) ወ/ሮ ቢታንያ አበበ በቦርድ አባልነት ተመድበዋል።

አሥራት የሕዝብ ሚድያ እንደመሆኑ መጠን፤ የሕዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ፤ ቦርዱ ጠቅላላው ሕዝብ የሚሳተፍባቸው የቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎች መዋቅር ዘርግቷል። እንዲሁም፤ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች፤ ሕዝቡ በየአካባቢው የሚሳተፍባቸውን ድጋፍ ሰጭ ማዕከሎች በማዋቀር ለመሥራት ዕቅድ ይዟል።

በመሆኑም፤ መላው የአማራ ሕዝብና የአማራ ወዳጅ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ይህንን ቦርድና የአሥራትን ሚድያ ለማስቀጠል፣ እንዲሁም አገልግሎቶቹ ሰፍተው ለሕዝብና ለሀገር የሚኖረው ፋይዳ ይጎለብት ዘንድ በሚደረገው ጥረት ሕዝባዊ ተሳትፎና ትብብር እንዳይለየው በሕዝባችን ስም እንጠይቃለን።

እናመሰግናለን፤
የአሥራት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ
መጋቢት ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓመተ ምህረት

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.