Breaking News
Home / News / የአብን መግለጫ – የመንግሥት መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት!

የአብን መግለጫ – የመንግሥት መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት!

ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ኢትዮጵያውያን!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ብሔራዊ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 26 እና 27 ቀን 2012 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የአገራችንን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ አውዶችን በጥልቀት በመገምገም፤ የአማራ ሕዝብን ወቅታዊ አቋምና ዘላቂ ጥቅሞችን፤ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችና ኃይሎች ፍላጎቶችን እና የቀረቡ አማራጮችን በፅሞና በመመርመር፤ በዚህም መሠረት፦

 ለሰላማዊና ጠንካራ አገራትና መንግሥታት እንኳን የሚያዳግቱ ግዙፍና አሳሳቢ ብሔራዊ ተግዳሮቶች የተደቀኑብን መሆኑን በማመን፤

 የዴሞክራሲያዊ ውድድር፣ የልሂቃን ውይይትና ድርድር ባኅል ባልዳበረበት በጥልቅ በተከፋፈለ ብሔራዊ ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንገኝ በመገንዘብ፤

 የኢትዮጵያ ቀጣይ ሁኔታ በምርጫ ወይም በይስሙላ ማሻሻያዎች ብቻ እንደማይወሰን፣ የአሸናፊዎችና የጉልበተኞች ጫናም ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በማመን፤
 ከምንም ከማንም በላይ የአማራን ሕዝብ ሰላም፣ደኅንነትና ዘላቂ ጥቅሞች መከበርና የአገራችንን ኅልውና ቀጣይነት በማስቀደም፤

አብን እነዚህንና ሌሎችንም ተጓዳኝ ታሳቢዎችን በማድረግ አገራችን ከገባችበት አጣብቂኝ በአስተማማኝ ልትወጣ የምትችልባቸውን መንገዶች በተመለከተ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡

1ኛ. የሽግግር ጊዜ (transitional period) አስፈላጊነት
ንቅናቄያችን አብን ሌሎች በአገራችን የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተቋማት ላቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ክብር ያለው ቢሆንም አሁን ለገባንበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት (transitional government) መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት የለውም፡፡

ከዚህ ይልቅ የተወሰነ የሽግግር ጊዜ መፍጠር የተሻለ አማራጭ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ምክንያቱም የኽዝባችንና የአገራችን እጣፋንታ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንዲቆም ሁኔታዎችን በማመቻቸት፣ ነባራዊ ውጥረቶችና ክፍተቶች እንዲረግቡና የጥሞናና ውይይት መንፈስ እንዲሰፍን ያስችላል፡፡ የሽግግር ጊዜ ያላሰለሰ ሕዝባዊ ውይይት ፣ ልሂቃዊ ምክክርና ድርድር እንዲደረግና ሊያሰራ የሚችል ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር እድል ይሰጣል፡፡

2ኛ. የመንግሥት መር (state-led) ሽግግር አስፈላጊነት
አብን ከገባንበት ብሔራዊ አጣብቂኝ ለመውጣት የአገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ አካል መኖር እንዳለበት ያምናል፡፡ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍጠር በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ አውድ ሊሳካ እንደማይችል ይገነዘባል፡፡

ስለዚህም ምንም እንኳን ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ የታየው መንግሥት መሩ የለውጥ ሂደት የከሸፈና የማያሰራ እንደነበር ብንረዳም፣ ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝባችንና አገራችን ሰላምና ደህንነት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለው ነው ብለን እናምናለን፡፡

3ኛ. የመዋቅራዊና ሁሉን አካታች ሽግግር ሂደት አስፈላጊነት
አብን የአማራ ሕዝብና የሌሎች ወንድም ህዝቦች መሰረታዊ ጥያቄዎች ስርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆናቸው በዋነኝነት የሚፈቱት በልሂቃን መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ያምናል፡፡
ብሔራዊ ፖለቲካችን ከጥሬ የስልጣን ትግል ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሻገር ከታሰበ ከአጭር ፖለቲካዊ ትርፍ ይልቅ ዘላቂ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን ያማከለና አዲስ ቅርፅና አቅጣጫ ያለው ሰፊና የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት ያስፈልጋል፡፡
በተለይም የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ማሻሻል፣ አጠቃላይ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማድረግ ያሻል፡፡ ከሁሉም በላይ በአሳሳቢ ሁኔታ እየወደቀ የመጣውን ምጣኔ ኃብታችንን እንዲያንሰራራ ማድረግ የግድ ነው፡፡
ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማኅበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ድርጅታችን አብን ይጠይቃል፡፡

4ኛ. መሠረታዊ የሕዝባችንን ጥያቄዎች በተመለከተ
ሀ. የኮቪድ – 19 ወረርሽኙ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ በመሠረታዊ የሕዝቦች ጥያቄዎች ላይ ቅርፅ ያለውና ተቋማዊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት (national dialogue) እንዲጀመር ለማድረግ ዋስትና እንዲሰጥ ንቅናቄያችን አበክሮ ይጠይቃል፡፡

ለ. የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ፣ ንቅናቄያችን የ1999 ዓ.ም ብሔራዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሳይንሳዊ ያልሆነና ሸፍጥ የተሞላብት የሕዝባችንን ቁጥር በእጅጉ የቀነሰ በዚህም ፖለቲካዊ ውክልናውን እና ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነቱን ያሳጣ በመሆኑ ውጤቱ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ፤ ለተከሰቱት ጉዳቶች ፍትኃዊ ማካካሻ (restorative justice) እንዲደረግና ቀጣዩም ቆጠራ ሳይንሳዊና ገለልተኛ በሆነ ተቋም እንዲካሄድ ይጠይቃል፡፡

ሐ. የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ፤ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ሕዝባችንን የማይወክልና በሂደትም ቅቡልነትን ያላተረፈ፣ በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሰረተ፣ ለአገር አንድነትና ኅልውና የማይበጅ፣ እንደዚህ ያለ ፈታኝ ወቅት ሲያጋጥም እንኳን በአግባቡ ሊያሻግር የማይችል በመሆኑ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የሕገ መንግሥት ለውጥ ወይም ማሻሻያ እንዲደረግ ይጠይቃል፡፡

መ. የአገራችንንና ሕዝባችንን የሰላምና ደኅንነት ዋስትና በተመለከተ፤ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሕግና ሥርዓት በማስከበር ረገድ ያሳየው ድክመት ተገቢ አለመሆኑንና በፍፁም መቀጠል እንደሌለበት በማመን፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥት ግንባር ቀደም ኃላፊነቶች መካከል መሆኑን በመገንዘብ፤ አገራችን ባለችበት የስጋት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለየ ዝግጁነት እንዲደረግ አበክሮ ይጠይቃል፡፡
አብን በሕዝባችን ትግል የተሸነፉ ቋሚ የአማራ ሕዝብና የኢትዮጵያ ጠላቶችና ግብረ አበሮቻቸው አገራችንን ለማተራመስና እንደገና የጭቆና መንበራቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚታገለው በአፅንኦት ያረጋግጣል፡፡
ንቅናቄያችን ከላይ የገለፃቸውን አቋሞች በተመለከተ ከመንግሥትና ከተለያዩ የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ንግግሮችንና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን እያሳወቀ የተከበረው የአማራ ሕዝብ፣ የድርጅታችን አባላት፣ ደጋፊዎችና መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በአሁኑ ወቅት የተደቀነብንን ብሔራዊ አደጋ በማጤን ላቀረብናቸው አማራጭ ኃሳቦች ስኬት ከጎናችን እንድትሰለፉ በአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.