Breaking News
Home / Amharic / የፋኖና የመንግስት የፓለቲካ ድርድር ምን ማለት ነው?

የፋኖና የመንግስት የፓለቲካ ድርድር ምን ማለት ነው?

የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ የፖለቲካ ድርድርን አስመልክቶ በአራቱም አቅጣጫ በሚታገሉ የፋኖ አመራሮች ጥልቅና የሰከነ ውይይት ተደርጎበት፣ ጉዳትና ጥቅሙ ከሁሉም አቅጣጫ በስፋት ተዳስሶ፣ ምክንያታዊ የሆነ የጠራና ግልጽ አቋም እንዲያዝ ለማበረታታት ነው። በድርድር ጉዳይ ላይ በፋኖ መሪዎች ደረጃ አንድ ወጥ አቋም ከተያዘ፣ ለደጋፊዎችና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የፋኖን አቋም ግልጽ በማድረግ፣ ሕዝቡንና ትግሉን ከውዥንብር፣ ታጋዩን ደግሞ ከተለያዩ ኃይሎች አላስፈላጊ ተጽዕኖ በማላቀቅ፣ ፋኖ የመሪነት ሚናውን በተገቢው በመወጣት ትግሉን ለማሳለጥ ይረዳዋል።

1. የፖለቲካ ድርድር ምን ማለት ነው?

የፖለቲካ ድርድር ማለት፣ በተጻራሪ ጎራ ተሰልፈው በፖለቲካዊም ይሁን በጦር እየተፋለሙ ያሉ ቡድኖች ልዩነታቸውን በንግግር እና በ “ሰጥቶ መቀበል” ለማጥበብ ወይም መፍትሄ ለመስጠት በመወሰን የሚፈጥሩት የመወያያ መድረክ ነው ለማለት ይቻላል። እዚህ ላይ ከእያንዳንዱ ጎራ የሚወከል አንድ ቡድን ወይም ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ኃይሎች ተዋሕደው ወይም ተቀናጅተው አቅማቸውን በማጎልበት ሊቀርቡ ይችላሉ። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የአገዛዙን ሥርዓት ለማስወገድ እና ኢትዮጵያውያን ላይ የተጫነውን የግፍ ቀንበር ለመስበር እየታገለ ያለው የፋኖ ኃይል ከመንግሥት ኃይሎች እንዲሁም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የተያዘውን ትግል መቋጫ በተመለከተ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ድርድር ውስጥ መግባት ግድ ሊል ይችላል።

2. ድርድር ለምን?

የፖለቲካ ጥያቄ ይዞ የተነሳ ማናቸውም የፖለቲካ ትግል መቋጫው የፖለቲካ ሥልጣን ነው። ለፖለቲካ ሥልጣን ለመብቃት ደግሞ ሰፊ ስብጥርን ግንዛቤ ውስጥ የከተተ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የፖለቲካ ድርድር የግድ ይላል።

የአብይ አህመድ አገዛዝ በጦርነት በፋኖ ቢወገድ እንኳ፣ ፋኖ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ከሚወክሉ የፖለቲካና ሲቪክ ድርጅቶች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ወዘተ… ጋር በመደራደር የሽግግር መንግሥትና የሽግግር ቻርተር መመስረት ያስፈልገዋል።

የአብይ አገዛዝ በፋኖ ይወድቃል ወይም ፋኖ ችላ ሊባል የማይገባ ትልቅ ኃይል ሆኗል ብለው ምዕራብውያንና ጎረቤት ሀገራት ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ፣ የረጅም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የፋኖን መሪዎች በምሥጢር ወይም በግልጽ መቅረባቸው፣ መወያየታቸውና እንደ አስፈላጊነቱ መደራደራቸው የሚጠበቅ ነው። ለዚህም ከወዲሁ የኅሊና ዝግጅት ማድረግ ይገባል።

የፋኖን የመንግሥት ለውጥ የማምጣት ግስጋሴ ለማሳለጥ፣ ትግሉን በአነስተኛ መሥዋዕትነት ለማቀላጠፍ፣ በመላ ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በመዲናችን በአዲስ አበባ ጠንካራ ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲጎለብት፣ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከሚወክሉ ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ለመታገል ከወዲሁ የፖለቲካ ድርድር ያስፈልጋል።

ፋኖ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ይዞታውን፣ ሃይማኖቱን፣… ከጥፋትና ከውድመት ለመታደግ በሬውን/ይዞታውን ሸጦ ከታች ወደ ላይ የተደራጀ ስለሆነ፣ በድርድር ከቀዬው ወደ ቀበሌ፣ ከቀበሌ ወደ ወረዳ፣ ከወረዳ ወደ አውራጃ፣ ከአውራጃ ወደ ክፍለ ሀገር፣ ከክፍለ ሀገር ወደ አማራ አቀፍ፣ ከአማራ አቀፍ ወደ ሀገር አቀፍ ድርጅት ለመለወጥ የሚያደርገው የሸዋ፣ የወሎ፣ የጎንደርና የጎጃም ዕዝ ምስረታን የዚሁ የፖለቲካ ድርድር አካል ተደርጎ መውሰድ ይቻላል።

3. የድርድር ግብ

እንደ ጊዜው የፋኖ ትግል የእድገት ደረጃና አስፈላጊነት፣ የፋኖ መሪዎች ለተለያዩ ግቦች ከተለያዩ ኃይሎች ጋር ድርድር ሊያደርጉ ይችላሉ።

ለምሳሌ፡-

ሀ. ሀገር አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ለማግኘት

የፋኖን ትግል ከላይ ወደ ታች ለማስተሳሰርና አንድ ወጥ ለማድረግ፣ በአሁኑ ወቅት ከታች ወደ ላይ እየተደረገ ያለው የሸዋ፣ የወሎ፣ የጎጃምና የጎንደር እዝ ምስረታ የፖለቲካ ድርድር እምብርት ነው። ይሄ ድርድር ሀገር አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ለማግኘት ይረዳል።

ለ. ዓለም አቀፍ እውቅናና ተቀባይነት ለማግኘት

እድሜ ለፋኖ፣ ምዕራብውያን እና የጎረቤት ሀገራት የአማራውን ትግል ችላ የማይሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። አሜሪካኖች ስለ ወቅታዊ ጉዳይ ለመነጋገር ባሕርዳር በቅርቡ ገብተው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በኋላ ፋኖን በዋናነት ያልያዘ ማናቸውም ድርድር ፍሬ እንደማያፈራ ቢመራቸውም ምዕራባውያን እየተቀበሉት ነው።

ፋኖም አይቀሬውን የመንግሥት ለውጥ ለማሳለጥ፣ ከኢትዮጵያ ዘለቄታዊ ብሔራዊ ጥቅም ዝንፍ ሳይል፣ ተገቢውን ዓለም አቀፍ እውቅናና እገዛ እንዲያገኝ፣ በተለይ ከምዕራቡ ጋር መደራደር አስፈላጊ እንደሆነ አውቆ፣ የድርድሩ ዳራ ላይ ከወዲሁ በስፋት መወያየት ያስፈልጋል።

ሐ. የፋኖ ትግል ሲበረታ

በድፍኑ አንደራደርም ከማለት፣ በትግሉ ሜዳ ላይ ያለውን የፋኖን የኃይል ሚዛን በቅጡ ግምት ውስጥ በከተተ መልኩ፣ ፋኖ የሚያቀርባቸው የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ማተኮሩ ለትግሉ ይጠቅማል።

ማስተዋል የሚገባው ዋና ጉዳይ፣ ለድርድር የሚቀርቡት ነጥቦች እና የሚቀርቡበት ሁኔታ በድርድሩ ወቅት መሬት ላይ ባለው የኃይል ሚዛን በእጅጉ እንደሚወሰን ነው። በዚህም መሠረት ፋኖ የኃይል ሚዛኑን የበላይነት በያዘበት ሁኔታ ለድርድር ቢቀመጥ ዋና የትግሉ ግብ የሆኑትን ነጥቦች፣ ማለትም፣ የአቢይን መንግሥት ከሥልጣን መልቀቅ፣ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፣ የጦር ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ወዘተ… በልበ ሙሉነት መጠየቅ የሚችልበት ዕድል ይፈጠራል።

መ. የሕዝብ ማታገያና መሪ አጀንዳዎችን ወደፊት በማምጣት ትግሉን ለማጠናከር

የተመረጡ መሪ ማታገያ አጀንዳዎችን ነቅሶ አውጥቶ የመደራደሪያ ቅድመ ሁኔታ በማድረግ ድርድርን ትግሉን ማሟሟቂያ፣ ሕዝቡን ማነሳሻ፣ ደጋፊዎችን ማሰባሰቢያ ማድረግ ይቻላል።

ለምሳሌ፣ ኦህዴድ ቤታቸውን በላያቸው ላይ አፍርሶ ያፈናቀላቸው ኢትዮጵያውያን ካሳ ተከፍሏቸው በመንግሥት ሙሉ ወጪ ቤት ተሰርቶላቸው እንዲመለሱ፤ የፈረሱ ቤተ እምነቶች በፈረሱበት ቦታ ከካሳ ጋር በመንግሥት ወጪ እንዲገነቡ፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ እንደመሆኗ፣ የኦህዴድ ፖሊስ /ልዩ ኃይል/ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች /መቀመጫ/፣ በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ እንዲወጣ፤ የሚሉ ነጥቦች እንደ “የማታገያ አጀንዳዎች” በድርድር ምክንያት ማንሳት ይቻላል።

ሠ. ብቸኛው መፍትሄ የመንግስት ለውጥ ብቻ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አስረግጦ ለማሳሰብ፣

የአብይ አገዛዝ እያበቃለት እንደመሆኑ መጠን፣ ድርድሩን “የአብይ አገዛዝ በአስቸኳይ ሥልጣን ይልቀቅ፤ የሽግግር መንግሥት ይመስረት፤ የጦር ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ፤….” ብሎ የድርድር ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ ድርድር ውስጥ መግባት ይቻላል።

4. የፋኖ የድርድር ቀይ መስመሮች

ሀ. ኢትዮጵያውያንን አገር አልባ፣ አማራውንና ተዋሕዶ ክርስቲያኖችን እንደ ሁለተኛና ሶስተኛ ዜጋ የሚያሰቃየውን የወያኔ ሕገ መንግሥት /ሕገ ሕወሐት/ አግዶ፣ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር አገር የሚያጸና፣ ዜጎችን በእኩል ደረጃ የሚያሳትፍ፣ ሰው ላይ /ዜግነት ላይ/ የተመረኮዘ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ።

ለ. የጎሳ እና የሃይማኖት ፖሊቲካ እንደ ማናቸውም የአፍሪካ ሀገሮች በሕገ መንግሥት እንዲታገድ ማድረግ፡፡

ሐ. ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በመመካከር የትሕነግን የአፓርታይድ አስተዳደር ክልል አስወግዶ፣ በምትኩ ታሪክን፣ የኢኮኖሚ መሳለጥን፣ ወንዝና ተራራን የመሳሰሉ የተፈጥሮ ወሰኖችን፣…. ግምት ውስጥ ያስገባ የፖለቲካ አስተዳደር መፍጠር፡፡

መ. የሚፈጠሩት የአስተዳደር አካላት ከፖሊስ የዘለለ ማናቸውም የታጠቀ ኃይል እንዳይኖራቸው በሕግ ማገድ።

ሠ. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ተዘዋውሮ ከሌላኛው ወገኑ እኩል የመኖር፣ የመምረጥ፣ የመመረጥ፣ የመነገድ፣…. መብቱን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና መስጠት። ብሔሮች/ጎሳዎች፤ ባህል፣ ዘፈን፣ ቋንቋ፣…. እንጂ መሬት/ግዛት እንደሌላቸው አስረግጦ በሕግ መደንገግ። በሌላ አነጋገር ማናቸውም መሬት የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ የማናቸውም ብሔር/ጎሳ እንዳልሆነ መግለጽ። ይሄ ሐሳብ 3 ሺህ ዓመት ተሻግሮ ከመጣው ከጎንደር፣ ከወሎ፣ ከሐረር፣ ከወለጋ፣…. (መጠሪያ ስማቸው ቢቀያየርም) መሬት ጽንሰ ሐሳብ ጋር አይጋጭም፤ ሁሉም ክፍለ ሀገራት ኅብረ ብሔራዊ ይዘት ስላላቸው።

ረ. ከአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ዙርያ (ከቡራዩ፣ ከሱሉልታ፣ ከሰበታ፣ ከለገጣፎ)፣ ከወለጋ፣ ከሸዋ፣ ከከፋ፣ ከባሌ ወዘተ… የተፈናቀሉ ተፈናቃዮች ስም ዝርዝራቸው ተሰንዶ፣ መንግሥት ይቅርታ ጠይቆ፣ ተመጣጣኝ ካሳ ከፍሎ፣ ማቋቋሚያ ሰጥቶ፣ ራሳቸውን ከዳግም ጥቃት የሚከላከሉበትን ዘዴ ቀይሶ፣ ወደ ቦታቸው መመለስ።

ሰ. ለፈረሱ ቤተ እምነቶች በሙሉ ይቅርታ ተጠይቆ፣ ካሳ ተከፍሎ፣ ተጨማሪ የመሬት ይዞታ በፈረሱበት አካባቢ ተሰጥቷቸው፣ ቤተ እምነታቸውን ዳግም እንዲያንጹ መርዳት፡፡

ሸ. የባሕር በር ማጣትን ጨምሮ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም አሳልፈው የሰጡ፣ ሕዝቡ ላይ ጄኖሳይድና የተለያዩ የሰብአዊ ጥሰት የፈጸሙ፣ ቤት ያፈረሱ፣ ያፈናቀሉ፣…. ሲቪሎችንና የጦር መሪዎችን ነጻ ፍርድ ቤት ማቅረብ።

5. መደምደሚያ

የፖለቲካ ትግል መቋጫው የፖለቲካ ድርድር መሆኑን በመቀበልና የድርድር ጥያቄ ከሁሉም አቅጣጫ ሊመጣ እንደሚችል በመገመት አጀንዳው ቢያንስ ፋኖን ለመከፋፈል እንዳይውል ከወዲሁ መዘጋጀት ነው።

ስለሆነም ግልጽ ግብ ያላቸው ዘርፈ ብዙ ድርድሮችን በፋኖ ተነሳሽነት እንደ አስፈላጊነቱ የማድረግ ጥቅምን ተገንዝቦ መሥራት ተገቢ ነው።

የድርድሮች ሁሉ መዳረሻ ትግሉን ማሳለጥ፣ ትግሉን በትንሽ መሥዋዕትነት ማሳጠር፣ አንኳር አንኳር ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መስማማት፣ አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ማምጣት፣…. መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

የፋኖ መደራደር አስፈላጊነቱ በሰከነ ውይይት ካልታመነበት፣ በድፍኑ አልደራደርም ብሎ የተለያየ የፖለቲካ አደጋ ከመጋበዝ፣ ተቀባይነት የማያገኙ የድርድር ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር ድርድሩ እንዲጨናገፍ ማድረግ ይጠቅማል።

አማራ በትግሉ ህልውናውን ያስከብራል!

 

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.