Breaking News
Home / News / የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞችን የኢትዮጵያ ሠራዊት መቆጣጠሩን መንግሥት ገለጸ

የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞችን የኢትዮጵያ ሠራዊት መቆጣጠሩን መንግሥት ገለጸ

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞችን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ከህወሓት ኃይሎች አስለቅቆ መቆጣጠሩ ተገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰኞ ኅዳር 27/2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ እንዳስታወቀው የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው የደሴ ከተማ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችው የኮምቦልቻ ከተማ ከአማጺያኑ ነጻ መውጣታቸውን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በጥምረት ባካሄዱት ዘመቻ በምሥራቅ ግንባር ባቲን፣ ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንን እንዲሁም በሐርቡ ግንባር የቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን መንግሥት አሳውቋል።

ከአንድ ወር በላይ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር የቆዩት የደሴ እና የኮምቦልቻ ከተሞች በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች አማካይነት ነጻ መውጣታቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደሴ ከተማን የህወሓት ኃይሎች የተቆጣጠሯት ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም ሲሆን፤ በማስከተልም በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው የኮምቦልቻ ከተማም በአማጺያኑ መያዟ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተጀመረው ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተስፋፋ በኋላ ከባድ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቶ አማጺያኑ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችለው ነበር።

ከአንድ ወር በላይ በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር የቆየችው የደሴ ከተማ ከአዲስ አበባ 385 ኪሎ ሜትር የምትርቅ ሲሆን በአማራ ክልል ውስጥ ካሉ ትልልቅ ከተሞች መካከል አንዷና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ናት።

በዚህ ዓመት በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ የተባባሰው ጦርነት ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ወሎ በመስፋፋት ወሳኝ የሚባሉት የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ ወደ ሰሜን ሸዋ ተስፋፍቶ ቆይቷል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን መምራት መጀመራቸውን ተከትሎ የአማጺያኑ ግስጋሴ ከመገታቱ በተጨማሪ ይዘዋቸው ከነበሩ የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።

በህወሓት መሪዎች በኩል ግን ኃይሎቻቸው እንዲወጡ የተደረገው “በስልታዊ ውሳኔ” መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ለቢቢሲ “አማጺው ሽንፈት ገጥሞት” እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ የተቀሰቀሰው ጦርነት ባለፈው ሰኔ ወር ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ እስካሁን እየተካሄደ ይገኛል።

የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልል በመግባት ዘመቻ በማካሄዳቸው በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን ይዘው ወደ አዲስ አበባ ለማቅናት ፍላጎት እንዳለቸው ሲገልጹ ቆይተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጦር ግንባር በመሄድ ሠራዊቱን ለመምራት መወሰናቸውን ተከትሎም በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ለማስለቀቅ ውጊያዎች ተጠናክረው እየተካሄዱ ነው።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማን ጨምሮ ቁልፍ ወታደራዊ ጠቀሜታ አላቸው የሚባሉት በአፋር ክልል ጭፍራ በአማራ ክልል ደግሞ የጋሸና ከተሞች በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብ እና በሰሜን ወሎ ውስጥ በህወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችም በመንግሥት ቁጥጥር ስር መግባታቸው ተገልጿል።

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.