ያኔም የምለው ነው፣ አሁንም እላለሁ፣ የዘር ፖለቲካ እያለ ችግር አይፈታም #ግርማካሳ
ከሁለት አመት በፊት ከሲዳማ ውዝግብ ጋር በተገናኘ የጻፍኩት ጽሁፍ ነበር፡፡ “የዘር አወቃቀሩና ፖለቲካው ከቀጠለ አገር ትፈርሳለች፣ ደም ይፈሳል ” በሚል ርእስ፡፡ በዚያ ጽሁፍ የሚከተለውን አስፍሬ ነበር፡፡ ካርታውንም ያኔ ያወጣሁት ነው፡
“ሕብረ ብሄራዊ የሆኑ፣ አንዱ ጋር አንዱ ብሄረሰብ፣ እልፍ ብሎ ሌላው የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ብዙ ስላሉ፣. የይገባኛል ጥያቄዎች ስፍር ቁጥር አይኖራቸውም። ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ሞያሌ፣ ወልቃይት፣ ራያ፣ ሸዋ፣ ጉርሱም፣ ባቢሌ፣ ሻሸመኔ፣ ወሎ፣ መተከል፣ ሃረር…ብዙ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸው ናቸው። እነዚህን ሁሉ ለአንዱ ሰጥቶ ፣ ለሌላው እየነፈጉ እንዴት ነው ማስተናገድ የሚቻለው ? ስለዚህ የጎሳ ግጭቶች በሽ በሽ እንደሚሆኑ መገመት አያስቸግርም። በሶማሌና በኦሮሞ ክልል መካከል ከ400 በላይ ቀብሌዎች የይገባኛል ውዝግ እንዳለ መጥቀሱ ብቻ ይበቃል።
ስለዚህ አሁን ያለው በዘርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፣ የኔና የናነተ መሬት የሚል የፌዴራል አወቃቀር ቀርቶ፣ ዘመናዊ፣ ለአስተዳደር አመች የሆነ፣ የሁሉንም ባህል፣ ቋንቋ የሚያከብር፣ በእኩልነትና በአንድነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል አወቃቀር ያስፈልገናል።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ የወሰንና ማንነት ኮሚሽን አቋቁመዋል። ይሄ ኮሚሽን ስራውን እየሰራ አይመስልም። በመሆኑም ራሳቸው ዶ/ር አብይ አህመድ በአስቸኳይ አገራዊ ጉባዬ ጠርተው ይሄ አገርን ወደ ገደል እየከተተ ያለውን፣ የዘር አወቃቀር እንዲቀየር ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ። አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ …መባባል መቆም አለበት።”
ይሄ እንግዲህ ከላይ እንዳልኩት ከሁለት አመት በፊት የጻፍኩት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ መጻፍ የጀመርኩት ከ97 በኋላ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጽሁፎችን ጦማሮች አቅርቢያለሁ፡፡ የተለያዩ ቃለ ምልልሶች ሰጥቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ ያለኝና የማስተጋባው አቋም፣ ኢትዮጵያ ከዘር ፖለቲካ ካልወጣች ከደም መፋሰሶች ወደ ደም መፋሰሶች እንደምነሻገር ነው፡፡
የሶማሌና የኦሮሞ ነው በሚል ስንት ደም እኮ ፈሷል ከጥቂት አመታት በፊት፡፡ አዳይቱ ከተማን መቼም አትረሷትም፡፡ የአፋር ነው የሶማሌ ነው በሚል እኮ ነው የወደመችው፡፡ “ፊንፊኔ የኦሮሞ ናት ፣ አይደለችም” ወዘተ የሚለው ክርክር አሁንም አለ፡፡ ወልቃይት የትግሬ መሬት ነው፣ የአማራ መሬት ነው .እየተባለ ይኸው ደም እየፈሰሰ ነው፡፡
የዘር ፖለቲካ የዘር ሕገ መንግስትና አወቃቀርን ይዘን ከቀጠልን፣ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ደራ፣ ሰላሌ፣ ፈንታሌ.። በአጠቃላይ ሸዋ ፣ ድረዳዋ፣ ሃረር፣ ምእራብ ጉጂ ፣ ቤኔሻንጉል ኧረ ስንት ቦታ ነው ያለው መሰላችሁ የኔ ጎሳ ነው ያንተ አይደለም የሚል ውዝግብ የሚያስነሱ፡፡
አሁንም ደግሜ እላለሁ የዘር ፖለቲካ ፣ በዘር ፖለቲካ ቀመር የሚፈታ ችግር የለም፡፡ አሁን እስቲ አስቡት የወልቃይት ጉዳይ አንዱ በጉልበት ይዞ ካልቀጠለ እንዴት ተደርጎ ነው ነው መስማማት የሚቻለው፡፡ ወቅላይት ለትግራይ ከተሰጠ አማራው እዚያ ጋር አገር አልባ ይሆናል፡ ለአማራ ከተሰጠ ትግሬው አገር አልባይ ይሆናል፡፡ ለምን አሁን ያለው ሕገ መንግስት ለሕብረ ብሄራዊነት ይሁን ለዉህድ ኢትይጵጵያዊነት እውቅና አይሰጥም፡፡ ወልቃይት የትግሬም፣ የአማራም እንድትሆን አይፈቅድም፡፡