በመስከረም አበራ
የመጀመሪያው የኦዴፓ እውነተኛ ማንነት የተገለጠው ስልጣን በያዘ ማግስት ህግ ጠረማምሶ የአዲስ አበባ ምክርቤት አባል ያልሆነ ሰው የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሲሾም ነው፡፡ ኦዴፓ የፌደራል ስልጣን ላይ ተስተካክሎ ሳይቀመጥ ገና እንዲ ያለ ህግ የመጣስ ድፍረት ያሳየው በአዲስ አበባ ላይ የነበረውን አላማ ለማስፈፀም ካለው ጉጉት አንፃር ነው፡፡
>>
ሃገራችን ኢትዮጵያ ከህወሃት አረመኔያዊ አገዛዝ ለመላቀቅ ባደረገችው የትግል ምጥ “የለማ ቡድን” የተባለ የድንገቴ ልጅ ታቀፈች፡፡ይህ ቡድን አለ ወይስ የለም የሚለው ራሱ ሲያጠራጥር ነበረ፡፡መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ደግሞ ከህወሃት ባርነት ነፃ የመሆን አለመሆኑ ነገር ብዙ ሲያከራክር ቆየ፡፡ከህወሃት ነፃ መሆኑን ፈጣሪ ጌታውን ራሱን ህወሃትን ከስልጣን ገፍትሮ ጥሎ አሳየ፡፡በስተመጨረሻው እንደ አውሬ አድርጎት የነበረውን ህወሃትን ገፍትሮ በጣለ ቅፅበት ኦዴፓ የኢትዮጵያን ህዝብም በአደንዛዥ ፍቅር ጣለ፡፡የፍቅር ብዛት ትንታግ ተቃዋሚውን ገራም ባለሟል፣አዋቂውን አላዋቂ፣ተጠራጣሪውን አማኝ አደረገለት፡፡የወዳጅ ጠላቱ በፍቅር ሰመመን ውስጥ መውደቅ ኦዴፓ የሚሰራው ሁሉ በመላዕክት ጉባኤ የተወሰነ ቅዱስ ሃሳብ ተደርጎ እንዲወሰድ አደረገ፡፡ብዙው ሰው በፅኑ ፍቅር መመታቱን ያጤነው ኦዴፓ ከአባቱ ኦነግ፣ከጌታው ህወሃት የወረሰውን ዘረኝነቱን ፈራ ተባ ሳይል ያስኬደው ጀመር፡፡
የመጀመሪያው የኦዴፓ እውነተኛ ማንነት የተገለጠው ስልጣን በያዘ ማግስት ህግ ጠረማምሶ የአዲስ አበባ ምክርቤት አባል ያልሆነ ሰው የከተማዋ ከንቲባ አድርጎ ሲሾም ነው፡፡ ኦዴፓ የፌደራል ስልጣን ላይ ተስተካክሎ ሳይቀመጥ ገና እንዲ ያለ ህግ የመጣስ ድፍረት ያሳየው በአዲስ አበባ ላይ የነበረውን አላማ ለማስፈፀም ካለው ጉጉት አንፃር ነው፡፡ታከለ ዑማ የአዲስ አበባ ከንቲባ ተደርጎ የተሾመው ሰውየው ከኦሮሞነቱ በተጨማሪ የሰፈረበት የኦነግ መንፈስ ብርታት ስለተፈለገ ጭምር ነው እንጅ በአዲስ አበባ ካውንስል ውስጥ ኦሮሞ ፈልጎ ማግኘት አስቸግሮ አይደለም፡፡ከሁሉም በላይ ግራ አጋቢው አዲስ አበባን መምራት ያለበት ኦሮሞ ብቻ ነው የሚለው ህግ ከየት እንደመጣ ነው፡፡
የኦዴፓ ክንብንብ የወረደበት ሌላው አጋጣሚ የኦነግ ሼኔ አመራሮችን ወደ አዲስ አበባ መግባት ተከትሎ በቡራዩ የተደረውን አሳዛኝ ጭፍጨፋ ማዳን ሲችል አለማዳኑ፣ነገሩ ከተከሰተ በኋላም ጉዳዩን በጥብቅ የህግ ክትትል ስር ለማድረግ ወገቤን ማለቱ ነው፡፡ይህ ሳያንስ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ለቃቅሞ ከሃገር ዳር አውጥቶ ሁለትም ወር ሙሉ በበረሃ እስርቤት ማጎሩ ነው፡፡በበኩሌ የኦዴፓ ነገር የበቃኝ የዚህ ጊዜ ነው፡፡ ኦዴፓ መራሹ መንግስት ያንን ሁሉ የአዲስ አበባ ወጣት ያለምክንያት ሲያስር ለመታሰራቸው በቂ ምክንያት ያላቸውን የቡራዩ ነፍሰ-ገዳዮች በብር ዋስ እየፈታ ነበር፡፡በዚህ ላይ የአዲስ አበባ ልጆች መታሰራቸው ትክክል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የኦዴፓ ዋና ዋና ባለስልጣናት እየተፈራረቁ ያስረዱን ነበር፡፡የአዲስ አበባ ወጣቶች እስር ደግሞ ማንን ለማስደሰት እንደሆነ ግልፅ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ ኦዴፓ ከህወሃት ባላነሰ ስልጣን እና ዘረኝነት የሚያመጡትን ብልግና የመድገም “ብቃት” እንዳለው መገመት ከባድ አልነበረም፡፡ አሁን እያደረገ ያለውም ይሄንኑ ነው፡፡
በሶስተኝነት የማስቀምጠው በግሌ ኦዴፓን የመረመርኩበት አጋጣሚ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ቤተ-መንግስት መግባታቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ የተናገሩት ንግግር ነው፡፡ጠ/ሚ አብይ በፓርላማ ተገኝተው “የወታደሮቹን ቤተ-መንግት ሰተት ብሎ መግባት እንደቀላል ነገር በቴሌቭዥን ያወራሁት በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ኦሮሞዎች መንግስታችን ወደቀ ብለው በፈረስ እንዳይደርሱ ፈርቼ ነው” ብለዋል፡፡ፍቅር አይኑን ላልሸበበው ሰው ይህ ንግግር ብዙ ትርጉም አለው፡፡ከሁሉም በላይ ግን አብይ “የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ” ሲሉ የባጁትን ንግግር ልባዊነት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡አብይ ቦምብ ሲወረወርባቸው በእጁ የተከላከለላቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ቢሆንም ለእርሳቸው የክፉቀን ደራሽ፣የዙፋናቸው ደጀን ሆኖ የሚታያቸው የሆሎታ እና የሱሉሉታ ፈረሰኛ ኦሮሞ ነው፡፡ከዚህ መረዳት የሚቻለው የዘር ፖለቲከኛ የአንገት እና የአንጀት ወዳጅ እንዳለው ነው፡፡የዘር ፖለቲከኛ ከዘሩ ህዝብ ጋር እኩል ያየኛል፣የእኩልነት ፖለቲካ ያመጣልኛል ብሎ መድከምም ለቂልነት የሚዋሰን ነገር ነው፡፡
አራተኛው እና ዋናው ክንብን አውራጅ ስራ የተሰራው ህግን እና ደምብን ባልተከተለ መንገድ ከኦሮሚያ ክልል ለመጡ ሰዎች የአዲስ አበባ ነዋሪነት መታወቂያ በገፍ መታደል ሲጀምር ነው፡፡ነገሩን በጣም አሳፋሪ የሚያደረገው ነገር ደግሞ መታወቂያው የተሰጠው ከንቲባው በገዛ አንደበታቸው “በአዲስ አበባ ማንኛውንም አይነት መታወቂያ መስጠት አቁመናል” እያሉ በሚያወሩበት ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ከዚህ የባሰው አስገማች ነገር ደግሞ ይህን የእብሪት እና ማንአለብኝነት ህገወጥ አሰራር ያጋለጠችን ወ/ሮ ሰናይት የተባለች የእውነት ሴት ከስራ ማባረሩ ነው፡፡ከስራ መባረሯ ተሰምቶ በህዝብ ዘንድ ጉም ጉም ሲያስነሳ ሴትዮዋን ወደ ስራዋ ለመመለስ ተብሎ የተፃፈው ደብዳቤ አስተዛዛቢ ነው፡፡የደብዳቤው ይዘት ኦዴፓ በህወሃት ቤት በአሽከርነት ሲያድግ እንዴት ጌታውን መስሎ እንዳደገ አመላካች ነው፡፡የህወሃትን መልክ ጠልቶ ቢቸግረው ኦዴፓን ያመነው ህዝብ ደግሞ በማንም ውስጥ መልሶ የህወሃትን መልክ የማየት ፍላጎትም ትዕግስትም የለውም፡፡ይህን አለመረዳት የውርደት ሞት ይገድላል!
ቀድሞ ከተገለፁት በልጦ በኦዴፓ እውነተኛ ማንነት ላይ ግልፅ ምስክር የሆነው የለገጣፎ ቤት የማፍረስ ክስተት ነው፡፡ይህ በምላስ ሊጋርዱት የማይችሉት ያፈጠጠ ገበና ነው፡፡የለገጣፎው ነገር ኢህአዴግን የመሰለ ዘረኛ ድርጅት ዙፋን ላይ አስቀምጦ ስለ ሰብዓዊ መብት ማውራት ለቅሶቤት እንደመዝፈን ያለ ዕብደት እንደሆነ ያስመሰከረ ሃቅ ነው፡፡የለገጣፎው ቤት የማፍረስ ዘመቻ ኢ-ሰብአዊነት ብዙ የተባለለት ስለሆነ ወደዛ መግባቱ ላያስፈልገኝ ይችላል፡፡ይልቅስ ጉዳዩን አስመልክቶ የኦዴፓ መራሮች የሚናገሯቸውን ንግግሮች ተንተርሰን የፓርቲውን ማንነት ወደመመርመሩ ማለፉ የተሻለ ይሆናል፡፡
የለገጣፎው ቤት የማፍረስ አካሄድ እንዴት ትክክል እንደሆነ የሚያስረዱ የኦዴፓ ባለስልጣናት በተለይ ከንቲባዋ ወ/ሮ ሃቢባ ነገራቸውን የሚጀምሩት የለውጥ/የተሃድሶ አመራር መሆናቸውን በመጥቀስ ነው፡፡የለውጥ አመራር ነኝ ባይዋ ሴትዮዋ ወ/ሮ አዜብ እንዳደረጉት በኢሳቷ ጋዜጠኛ ኢየሩሳሌም ተክለፃዲቅ ጆሮ ላይ ስልክ ጠርቅመው ዘግተዋል፡፡ስልክ መዝጋቱን ያመጣው ጋዜጠኛዋ የማያፈናፍን ጥያቄ በማቅረቧ ነው፡፡ ወ/ሮ ሃቢባ ስልክ ከመዝጋታቸው በፊት ምንም አይነት ሰው እንዳላፈናቀሉ፣የመፈናቀሉን ወሬ የሰሙት በኢሳት እንደሆነ ተናግረው ሳይጨረርሱ ደግሞየፈረሰው ቤት ሁለት መቶ ሆኖ ሳለ ኢሳት አራትመቶ ብሎ ማውራቱ ልክ እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡ሁለት መቶ ቤት ፈርሶ ምንም ሰው የማይፈናቀለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ እንጓጓሁ ስልኩን ጠርቅመው ዘግተው አረፉት፡፡
ከኢሳት እንዲህ የተሰናበቱት የለገጣፎ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ የቡራዩውን ከንቲባ አስክለው “OMN” በተባለው ቴሌቭዥን ላይ በአካል ቀርበው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ቤት ማፍረሱ እንዴት ትክክል እንደሆነ ለማስረዳት ሁለቱም ከንቲባዎች ከ2004 በፊት እና በኋላ የሚል ነገር ያስቀምጣሉ፡፡ከ2004 በፊት ግንባታ ያደረጉ ሰዎች ህጋዊ ካርታ እንዳገኙ ጠቅሰው ከ2004 በኋላ የሰፈሩቱ እና ከከተማው ማስተር ፕላን ጋር ግጭት ያለው አሰፋፈር የሰፈሩ (ለምሳሌ በማስተር ፕላኑ የኦሮሞን ባህል ለማሳደግ ሲባል የፈረስ መጋለቢያ፣የአረንጓዴ መናፈሻ ቦታዎች ተደርገው የተቀመጡ ቦታዎች ላይ የገነቡ) ሰዎች ቤታቸው መፍረሱ ህግን የማስከበር ስራ እንደሆነ ደጋግመው አስረድተዋል፡፡
ቤት የፈረሰባቸውን ሰዎች ገበሬውን አታለው በትንሽ ዋጋ መሬቱን ገዝተው የሰፈሩ መሬት ወራሪዎች እንደሆኑ ሁለቱም ከንቲባዎች ያስረዳሉ፡፡ይህ የዘር ፖለቲካ አይነተኛ መገለጫ ነው፡፡መሬት የብሄር ብሄረሰቦች ነው በሚለው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ መሰረት ገንዘብ ሲፈልግ መሬቱን መጤ ለተባለ ሰው የሸጠ ብሄር ብሄረሰብ ገንዘቡ ሲያልቅበት መሬቱንም የመከጀል መብት ያለው ይመስለዋል፡፡ይሄን አስቂኝ ክርክር ከገበሬው እሻላላሁ ብሎ ስልጣን ላይ የተወዘፈ የዘር ፖለቲካ ባለስልጣንም እንደሚጋራው የለገጣፎዋ ከንቲባ ወ/ሮ ሃቢባ እና ቢጤዋ የቡራዩው ከንቲባ ምስክር ናቸው፡፡ወ/ሮ ሃቢባ ህዝብን ማፈናቀላቸው፣ከቤት ጋር ህይወት ማፍረሳቸው ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የመስራታቸው መገለጫ እንደሆነ፣ከዚህ በፊትም እንዲሁ ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም ሲታገሉ እንደኖሩ፣ወደፊትም በዚህ እንደሚቀጥሉ ኮራ ብለው ተናረዋል፡፡ከዚህ የምንረዳው የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብየው በዘረኝነቱ ህወሃትን የሚያስንቅ እንደሆነ ነው፡፡
“ገበሬው ተታሎ በዝቅተኛ ዋጋ መሬት ሸጠ” የሚለው ከእውቀት ነፃ የሆኑ ዘረኛ ባለስልጣናት ክርክር አስቂኝም አስገራሚም ነው፡፡ ገበሬው ተታሎ በትንሽ ዋጋ የሚሸጠው መሬቱን ብቻ የሆነው እንዴት ነው?ገበሬው ምነው ተታሎ ኩንታል ጤፉን በአምስት መቶ ብር ሸጦ አያውቅ? ምነው ተታሎ ሰንጋ በሬውን በአንድ ሽህ ብር ሲሸጥ አልታየ?ይህ ከአዝጋሚ ጭንቅላት የሚመነጭ ክርክር አላማው “ወገንን” አድኖ “መጤን” ለማጥቃት ነው፡፡ገበሬው ተታለለ የሚለው መሬት መሸጥ ህገወጥ መሆኑንም ሳያውቅ ነው የሸጠው፣ተታሎ በትንሽ ዋጋ ስለሸጠ የሚገባውንም ጥቅም አላገኘም በሚል መሬቱን ሼጦ የበላውን “ወገን” አርሶ አደር ነፃ በማድረግ “መጤው” ላይ እርምጃ ለመውስድ ያለመ አካሄድ ነው፡፡እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ገበሬው መሬቱን የሚሸጠው ግራቀኝ አስቦ፣የሚጠቅመውን አውቆ ነው፡፡በተለይ ከ1997 ወዲህ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ የአዲስ አበባ ዙሪያ መሬቶችን በኢንቨስትመንት ስም እየቀማ፣ለገበሬው የአይብ መግዣ የማይሆን ካሳ ከፍሎ ማፈናቀል ጀምሮ ነበር፡፡ይሄኔ ገበሬው መንግስት መጥቶ በማይረባ ገንዘብ ሳያፈናቅለው በፊት መሬቱን በጣም በተሻለ ዋጋ ለግለሰቦች መሼጡን አማራጭ አድርጎ ወስዶ ነበር፡፡እንዲህ ጥቅም ጉዳቱን አመዛዝኖ የሸጠው ገበሬ ነው እንግዲህ ተታሎ በርካሽ ሸጠ የሚባለው፡፡
ከገበሬው ቀጥሎ ማዳን የተፈለገው ደላላም፣ባለስልጣንም ሆኖ መሬቱን ሲቸበችብ የነበረውን የኦህዴድ ባለስልጣን ነው፡፡ከገዥም ከሻጭም የበለጠው ጥፋተኝነት ያለው በነዚህ ካድሬዎች ላይ ሆኖ ሳለ የእነሱ ጥፋተኝነት በለሆሳስ ይታለፍና ጦሱ ሁሉ የሚወድቀው ኦደፓ ከቆመለት የኦሮሞ ህዝብ ውጭ የተወለዱ፣”ያለግዛታቸው መጥተው ቤት የሰሩ ሰዎች” ላይ ነው፡፡ይህ የኢህአዴግ ዘረኝነት አይነተኛ መለያ ነው፡፡እነዚህ በበስልጣናቸው ላይ ደላላነት እና ሌብነት የደረቡ ባለስልጣናት ላይ የማይጨከነው አሁን ደግሞ ተገልብጠው “የለውጥ አመራር” ተብለው የአብይን እና የለማን ዙፋን የሚሸከሙ ስለማይጠፉ ነው፡፡
ከለገጣፎ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ በ”OMN” ማብራሪያ ከሰጡት የቡራዩ ከንቲባ ንግግር ደግሞ ጉዳዩ ህገ-ወጥ ያሉትን ግንባታ ከማፍረስ አለፍ ያለ አላማ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ከንቲባው ስለጉዳዩ ሲያስረዱ መሬት ወራሪዎቹ አንድ ቤት ከገዙ በኋላ ብዙ ዘመድ አዝማዳቸውን እየጎተቱ እንደሚያመጡ፣በአንድ መሬት ግዥ ሰበብ በተገዛው ጊቢ ውስጥ ብዙ ሰው እንደሚሰፍር በምሬት ገልፀዋል፡፡ይህ ንግግራቸው የፓርቲው ጠብ ከቤቱ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በቤቱ ውስጥ ከሚኖሩ ግለሰቦች ማንነት እና ብዛት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሳያውቁት ጠቁመዋል፡፡
ወ/ሮ ሃቢባ ከተል ብለው እነዚህ ሰዎች እዚህ አካባቢ መጥተው የሰፈሩት የሆነ ድብቅ ዓላማ ይዘው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በሴትዮዋ አስተሳሰብ ሰዎቹን ለገጣፎ የወሰዳቸው የቤት ችግር ሳይሆን ኦሮሞ ሳይሆኑ ኦሮሚያን የመውረስ “እኩይ” ሃሳብ ነው፡፡በዚህ ያልበቃቸው ሃቢባ የሰዎቹ መፈናቀል ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ያገኘው(በሃቢባ አነጋገር ጫጫታ ያስከተለው) ተፈናቃዮቹ ሚዲያ ከሚጮህት ሁለት ክልል የመጡ በመሆኑ እንደሆነ ንዴት እየተናነቃቸው ተናገሩ፡፡አሁንም ሳያውቁት ማፈናቀሉ ዘር የለየ እንደነበር በገዛ አንደበታቸው አወጁ! ስልጣን ለመያዝ የዘረኝነት ልክፍት እንጅ እውቀት እና ማገናዘብ ከማይጠየቅበት ከኢህአዴግ ቤት እንዲህ ያለ ኩርማን ሃሳብ ያው ሰው ከንቲባ ሆኖ ቢገኝ ገራሚ ነገር የለውም፡፡
የሃገሪቱን ህዝብ በሰፊው ሲያነጋግር፣የኦዴፓን ማንነትም በገሃድ ሲያሳይ የሰነበተውን የለገጣፎውን የቤት ማፍረስ ተግባር አስመልክቶ ገዥውን ኦዴፓን የሚመሩት ዶ/ር አብይም ሆኑ ክልሉን ኦሮሚያን የሚመሩት የነወ/ሮ ሃቢባ አለቃ አቶ ለማ መገርሳ ትንፍሽ ሳይሉ መሰንበታቸው የሚያሳየው ከግፉ ተቃራኒ መቆማቸውን ሊሆን አይችልም፡፡ሳምንት ቆይተው ስለጉዳዩ ሲናገሩም ጠ/ሚንስትሩጭራሽ አልሰማሁም ሲሉ አቶ ለማ በዝምታቸው ቀጥለዋል፡፡ ከሁሉ የሚብሰው ደግሞ የዜግነት ፖለቲካን እናራምዳለን የሚሉ ፓርቲዎች ዝምታ ነው፡፡ይህ ነገር የዜግነት ፖለቲካ ሁነኛ ጠበቃ የሌለው የፖለቲካ አሰላላፍ ለመሆኑ ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡