የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በባህርዳር ከተማ ለሁለት ቀናት ያክል ያደረገውን ጉባኤ ተከትሎ የተሰጠ የአቋም መግለጫ!!
——————–
የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከባለፋት 18 ዓመታት በላይ ጀምሮ አምባገነኑና አፋኙን ቡድን ህወሃትን በነፍጥ ሲታገል መቆየቱ ይታወቃል።በዚህ እልህ አስጨራሽና ፈታኝ የትግል ሂደት “ውርሳችን አርበኝነት ትርፋችን ታሪካዊነት ነው!! እያሉ፤ ለህይወታቸው ፈጽሞ የማይሳሱ ድንቅና ብርቅዬ፣አያሌ አርበኛዎቻችን ለቃላቸው ታምነው በጀግንነት ጥለው፣እንዲወድቁ ሆነዋል።በጀግንነት የወደቁት አርበኞቻችን ራሳቸውን እንደ ሻማ አቅልጠው ያለፉት በአገራችን ፍትህ፣ እኩልነት፣ነጻነት፣የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት መብት እውን እንዲሆን እንጂ በመቃብራቸው ላይ ስልጣኑን ለመገንባት ለቋመጠና ለባለ ስውር የስልጣን ተስፈኛ ቡድን አልነበረም።
የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ባሳለፋቸው ፈታኝ የትግል አመታት በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ አድርሷል።ይህን ሃቅ እንኳን ወዳጅ ነውና ጠላትም በተደጋጋሚ መስክሮታል።ኢ.ህ.አ.ግ የኢትዮጵያ ህዝብ እምቢ ለነጻነቴ ብሎ እንዲነሳ፣ አምባ ገነንነት አምርሮ እንዲዋጋ አድርጓል። በመሆኑም በአገራችን ዛሬ ለመጣው የለውጥ አየር፣የንብረት፣ የአካል፣የህይወት መስዋእትነት ከፉሏል።በደምና በአጥንቱ ጉልህ ታሪክ ጽፏል። ኢ.ህ.አ.ግ ነብሰ-በላውንና አሸባሩውን የህወሃት ቡድን ለዘመናት ነፍጥ አንግቦ በመገዝገዙ ምክንያት ዛሬ መቀሌ ላይ ቁራጩ ተጭኖ ሂዶ እንዲወድቅ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ይሁንና በ2007 ዓ.ም የኢ.ህ.አ.ግ. አመራር በደንብ ሳይመካከርበት፣ሰራዊቱ ሳይወያይበት ከግንቦት ሰባት ጋር በተደረገው ውህደት መሰል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እንደ ድርጅት ኪሳራ እንዲያጋጥመው አስችሏል።በዓላማና በምክንያት ህይወቱን ለመስጠት የማይሳሳው የኢህአግ ሰራዊት ከግንቦት 7 ጋር በተደረገው ስመ-ውህደት ምክንያት ብቻ፣ ለፖለቲካ ነጋዴዎች የስልጣን ትርፍ ማጋበሻ አልሆንም በማለት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አርበኛ ትግሉን ጥሎ እንዲሸሽ ሆኗል።
“ትግላችን የአርበኝነት እንጂ የስልጣን አይደለም።” ያሉት የኢዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር አመራሮችና የሰራዊት አባላት ደግሞ፣በባለ ስውር እጆቹ፣በሴረኞቹ የግንቦት 7 አመራሮች ግፍና በደል ተፈጽሞባቸዋል።በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግባር ንብረቶች በግንቦት 7 አመራሮች እንዲዘረፉ ሆነዋል።የፖለቲካ ቁማርተኞቹ አርበኛውን አርቀው ለመቅበር ጥረዋል።ኧረ እንዲያውም ከእነ ነብሱ ቀበርነው ብለው ጮቤ እረግጠዋል።ግን አርበኛው ላይ በግንቦት 7 መሪዎች ከፍተኛ በደል ቢፈጸምመበትም እንኳን፣ ከእነ ነብሱ ሊቀበር ነውና የሞራል ጭረትም እንዳልደረሰበት ይህን ደማቅና የተሳካ ጉባኤ በማድረግ ይኼው ለወዳጅም፣ለጠላትም አሳይቷል።
ይልቁንስ የፖለቲካ ሸቃጮቹ አርበኛውን ለመቅበር አርቀው በቆፈሩት ጉድጓድ፣አርበኛውን ለመጥለፍ የዘረጉት የተንኮል ድር እራሳቸውን ጠልፎ ጥሏቸው በቆፈሩት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ጨምሯቸዋል።ዛሬ በየቦታው ለመንቀሳቀስ እግራቸው አጥሯል።አከርካሪያቸውም ተሰብሯል።አንጓቸው ደቋል።ነገር ግን ምላስ አይሰበርምና አሁንም ህዝባችን የሚያምታቱበት ቅቤ ምላሳቸው አብሯቸው አለ።በምላሳቸው ጤፍ መቁላት የለመዱት እነኝህ የፖለቲካ ነጋዴዎች በተቀመጡበት እየተልሞሰሞሱ ቢሆን በስማችን መነገዳቸውን አላቆሙም። ምንም እንኳን ንግዱ እንደ በፊቱ ተሟሙቆ ትርፉ ባይዛቅም።ምንም እንኳን በዚህ የፖለቲካ ሽባነታቸው ወደ ስልጣኑ ማማ የሚያወጣውን መሰላል ጨብጠው ከከፍታው ቦታ ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት ባይኖረነም።ግን ከዛሬ ጀምሮ ፣ኑሮአችን ባጣነበት፣በየዱር ገዱሉ በተንከራተትነበት፣ በታስርነበት፣ በቆሰልነበት በሞትነበት በአጠቃላይ ሁልቆ መሳፍርት ዋጋ በከፈልነበት የአርበኝነት ትግል መነገድ ባይሳካላቸውም፣ መሸቀጣቸውን ግን እንዲያቆሙ በጽኑ እናሳስባቸዋለን።እራሳችሁን ቻሉም እንላቸዋለን።
የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ኤርትራን ደጀን አድርጎ ለዘመናት በየዱር ገደሉ ሲያደርገው የነበረውን የመሳሪያ ትግል አቁሞ ይሄው ጉባኤውን በጣናዋ ፈርጥ በውቢቷ ባህርዳር ማድረግ ችሏል።ይህም የሆነው አንድም በጀግኖች አርበኞቻችን ደምና አጥንት፣ሁለትም በህዝባችን መራር ትግል፣ሶስተም ከእራሱ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በተፈጠሩ የለውጥ ሃይሎች ነው።ይህ ለውጥ ከዳር እንዲደርስና የህዝባችንን ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ፣ህልውናውን እንዲያስጠብቅ ድርጅታን ዛሬም እንደ ትላንቱ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው።
ኢ.ህ.አ.ግ በባህርዳር ከተማ ለሁለት ቀናት ባደረገው ጉባኤ፣ጉባኤተኛው የሃገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ፓለቲካዊ አሰላለፍ ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርጓል።ገምግሟል።በውይይቱም የአማራ ህዝብ በአማራነቱ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ባለመደራጀቱ ምክንያት ባሳለፍናቸው 27 የአገዛዝ አመታት ከሌላው ኢትዮጵያዊ በባሰ መልኩ ከፍተኛ ግፍና በደል እንዲፈጸምበት አንዱ ምክንያት መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊ አርበኞች ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር ከጥር 25-26/2011 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ ለሁት ቀናት ያክል ባደረገው ጉባኤ 49 የምክርቤት አባለትን እና 9 የስራ አስፈጻሚ አባላትን መርጧል።በተጨመሪም አርበኛ ወርቁ በለጠን የድርጅቱ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል።በዚህ በስኬት በተጀመረው ጉባኤ ባለ ሰባት (7) ነጥብ የአቋም መግለጫዎችን በማውጣት ጉባኤው በድል ተጠናቋል።
1ኛ) የኢ.ህ.አ.ግ አባል ከ95% በላይ የአማራ ተወላጅ በመሆኑና ወቅቱ በፈጠረው ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምክንያት፤ በቅድሚያ ለአማራ ህዝብ ህልውና፣ አማራው በወርዱና በመቁመቱ ልክ በመሰረታት ኢትዮጵያ አገሩ ላይ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እኩል የጥቅም ተቋዳሽነት እንዲኖረው መታገል እንዳለበት ጉባኤተኛው በሙሉ ድምጽ ወስኗል።በተጨማሪም የአማራን ህዝብ ህልውና መታደግ ማለት ኢትዮጵያን ማዳን መሆኑን በጎባኤው የጋራ አቋም መያዝ ተችሏል።
2ኛ) ለአማራ ህዝብ ጥቅምና ህልውና ከሚታገሉ አማራ አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኢ.ህ.አ.ግ አብሮ ይታገላል።በአምባ ገነኑ ህወሃት የተዘረፉ የአማራ ርስቶችንና የአማራ ማንነቶችን ለማስመለስ በሚደረገው ማንኛውንም አይነት ትግል አርበኞች ግንባር፣ ከተወለደበት ማህጸን ከአማራ ህዝብ ጎን ተሰልፎ ይታገላል!! ያታግላል። ዛሬም እንደትላንቱ መስዋእትነት ይከፍላል።
3ኛ) የአማራን ህዝብ ሰላም የሚያውኩ እና በአማራው ህዝብ ደም ለስልጣን ለመብቃት የሚቋምጡ እንዲሁም የአማራው ህዝብ መደራጀትና መጠናከር ሲያዩ አይናቸው የሚቀላባቸው እኩይ አካላት ከእኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አርበኞች ግንባር በዚህ አጋጣሚ በጥብቅ ማሳሰብ ይወዳል።
4ኛ) ኢ.ህ.አ.ግ ከግንቦት 7 ጋር የነበረውን ያልተቀደሰ ጋብቻ በይፋ ሰማኒያውን ከቀደደ ስንብቶ እያለ፤ነገር ግን መንግስትም ሆነ ሚዲያዎች ከግንቦት 7 ጋር በግድም ቢሆን ተጣብቃችሁ ትኖራታላችሁ በሚመስል አይነት፣የእነ ዶ/ር ብርሃኑን ድርጅት “ግንቦት 7” ማለት ሲገባቸው “አርበኞች ግንቦት 7” እያሉ በመጥራትም ሆነ በመዘገብ፣በስል
ጣን ወልፍ ናውዞ ሳይሆን ለአገሩና ለህዝቡ ብቻ የአርበኝነት ትግል ያደረገውን አርበኛ እያሳዘኑትና ሆድ እያስባሱት ይገኛሉ።በመሆኑም ከዚህ በኋላ “ግንቦት 7” እንጂ “አርበኞች ግንቦት 7” ተብሎ ሚዲያው ዘገባ እንዳይሰራ፣መንግስም “አርበኞች ግንቦት 7” ብሎ እንዳይጠራ በአጽንኦት እናሳስባለን።
5ኛ)ሰራዊቱ ላቡን ጠብ አድርጎ የገዛቸውንና ለድርጅቱ ግልጋሎት ይሰጡ የነበሩትን ሰባት መኪናዎች እንዲሁም ሌሎች ንብረቶች ግንቦት 7 ዘረፋ በሚባል ሁኔታ ሽጧል።ገንዘቡንም ለፓርቲ መመስረቻ፣ለስልጣን ማሳለጫ አውሎታል።በመሆኑም የአርበኛውን የንብረት ግምት፣ድርጅቱ ግንቦት 7 በአስቸኳይ ለድርጅታችን እንዲያስረክብ እንጠይቃለን።በተጨማሪም ግንቦት 7 በድርጅታችን ስም የሰበሰበውን ገንዘብ መውደቂያ አጥቶ በችጋር ለሚቆራመደው ታጋይ እንዲያከፋፍል እንጠይቃለን።
6ኛ )የለውጡ ፋና ወጊ የሆነውን አርበኛ በአስቸኳይ የመልሶ ማቋም እንዲደረግለት አርበኞች ግንባር አበክሮ ይሰራል።ይህ በወታደራዊ ስነ-ምግባር ደንብ የታነጸው ሰራዊት ለአማራ ህዝብ ሰላም መጠበቅ የብረት አጥር እንዲሆን እና የተጀመረው ለውጥ ከዳር እንዲደርስ፣ ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገርና በመወያየት አርበኛው ትጥቅ እንዲታጠቅ ኢ.ህ.አ.ግ ይሰራል።
7ኛ) በየዱር ገደሉ የወደቁትን የጀግኖች አርበኞቻችን አጽም፣ ተሰብስቦ በክብር እንዲያርፍ እና መታሰቢያ እንዲቆምላቸው ለቤተሰቦቻቸውም በጀግንነት መስዋትነት መክፈላቸውን በስነ- ስርአቱና በወጉ በማርዳት እንዲሁም የሚቻለውን ድጋፍ በማድረግ አብሮነቱንም በተግባር የሚያረጋግጥ ሲሆን ይሄንና በዚህ ያልተጠቀሱትን ዝርዝር የአርበኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር አርበኞች ግንባር የተለመደውን መስዋትነት ይከፍላል።
ውርሳችን አርበኝነት ትርፋችን ታሪካዊነት ነው!!
ትክክለኛ አቋም ነው በርቱ