Breaking News
Home / Amharic / # የአዲስ አበባ ወጣቶች የዋስትና መብት ዛሬም ሳይከበር ቀርቷል ! ታምራት ነገራ በ50,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ተወሰነ !

# የአዲስ አበባ ወጣቶች የዋስትና መብት ዛሬም ሳይከበር ቀርቷል ! ታምራት ነገራ በ50,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ተወሰነ !

# የአዲስ አበባ ወጣቶች የዋስትና መብት ዛሬም ሳይከበር ቀርቷል !
# ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50,000 ብር ዋስ እንዲፈታ ተወሰነ !
/
ዛሬ ቀጠሮ የነበራቸው የአዲስ አበባ ወጣቶች እና የባልደራስ አባላት በዋስትና ጉዳይ ላይ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ለአርብ መጋቢት 30/2014 ዓ.ም ተቀጠሩ፡፡ የዛሬው ችሎት ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት የጀመረ ሲሆን፣ ወጣቶቹ በ3 የተለያዩ መዝገቦች ተለያይተው ቀርበዋል፡፡
# የአድዋ ቲሸርት ጉዳይ
የችሎቱ ሂደት የጀመረው በአድዋ ቲሸርት ጉዳይ ሲሆን፣ ፖሊስ ለምን ቲሸርቱን እንደሚከለክል ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ፣ በቲሸርቱ ሳቢያ ሁከትና ብጥብጥ ይፈጠራል የሚል ስጋት እንዳለው፣በእስር ቤቱ ውስጥ አምባጓሮ እየተፈጠረ መቸገሩን፣በዚህም ሳቢያ ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል ወደ እስር ቤት መላኩን ገልጿል፡፡
# የጠበቆቹ ምላሽ
የተከሳሽ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ፣ ፖሊስ ቲሸርቱን የሚከለክለው ፍርድ ቤት ከሰጠው ትዕዛዝ በተቃራኒ መሆኑን፣ ዛሬም ቢሆን ከተከሳሾቹ አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ቲሸርቱን ለብሶ አላወልቅም በማለቱ ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ መደረጉን፣ሁከትና ብጥብጥ እስር ቤት ውስጥ እየተፈጠረ ነው የሚባለው ሀሰት መሆኑን፣ ኃላፊዎቹ ችሎት እንዲቀርቡ እየታዘዙ አሻፈረኝ ማለታቸው ፖሊስ ለህግ ተገዥ አለመሆኑን አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
# የሰለሞን አላምኔ አቤቱታ
ከእስረኞቹ አንዱ የሆነው ፋርማሲስቱ ሰለሞን አላምኔ በበኩሉ ለፍርድ ቤቱ ባሰማው አቤቱታ፣ ቲሸርቱን ለብሰው አምባጓሮ ፈጥረው እንደማያውቁ፣ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የቀሩት ችግር በመፍጠራቸው ሳይሆን የአጼ ምኒልክን ምስል ስላደረጉ ብቻ መሆኑን፣ ቅዳሜ ዕለት ቲሸርቱን በማድረጋቸው ከአባ ሳሙኤል ልብሶቻቸውን በፌስታል ጠቅልለው እንዲወጡ ከታዘዙ በኋላ፣ አራዳ ጊዮርጊስ የሚገኘው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መጥተው እንደነበር፣ በር ላይ እንደደረሱም በቀጠሯቸው መሠረት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ዳግም ወደ አባ ሳሙኤል እንዲመለሱ መደረጉን ተናግሯል፡፡ በተጨማሪም፣ እሁድ ዕለት ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ልዩ የፖሊስ ኃይል ከተኙበት ቀስቅሶ የአድዋ ቲሸርትን በሙሉ እንደቀማቸው ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡
# ምርመራው ስላለበት ደረጃ
በቀጣይነት፣ ፖሊስ ምርመራውን ከምን እንዳደረሰው ተጠይቆ፣ እንደወትሮው የሚፈልጋቸው ተጨማሪ ሰነዶች እንዳሉ፣ የሚያዙ ቀሪ የወንጀሉ አባሪዎች እንዳሉ በመግለጽ ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
# ዋስትና ስለመጠየቁ
ጠበቆቹም ለፖሊስ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ፖሊስ በየቀጠሮው የሚሰጠው ምክንያት አለመለዋወጡን፣ እስካሁን ባለው ሂደት የ87 ሰዎችን የምስክርነት ቃል እንደተቀበለ በመናገሩ ከዚህ በላይ ምስክር ያስፈልገዋል ተብሎ እንደማይገመት፣የፖሊስ ዓላማ በምርመራ ስም ተከሳሾቹን በእስር ማንገላታት መሆኑን፣ በተመሳሳይ ጉዳይ የተያዙ 4 ሴት እስረኞች ቅዳሜ ዕለት በዋስ እንዲፈቱ ታዞ የተለቀቁ በመሆኑ፣ በቀሪዎቹም እስረኞች ላይ ተመሳሳይ ውሳኔ ተሰጥቶ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል፡፡
# የፍርድ ቤቱ ምላሽ
ፍርድ ቤቱ በመጨረሻ በሰጠው ብይን፣ በቲሸርቱ ጉዳይ ፖሊስ በፈፀመው ተደጋጋሚ ህገወጥ እርምጃ ላይ ተግሳጽ ሳይሰጥ እንኳን በሽፍንፍን አልፎታል፡፡ የዋስትና ጥያቄውንም ቢሆን፣ በተመሳሳይ ጉዳይ ተይዘው የነበሩት 4ቱ የሴት እስረኞች በዋስ የተለቀቁ ቢሆንም፣ “ምርመራው በምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማየት አለብኝ” በሚል ለአርብ መጋቢት 30/2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በ50,000 ብር ዋስ እንዲፈታ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስኗል። ከ100 ቀናት በላይ ያለ አግባብ የታሰረው ታምራት፣ ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ የሀገሪቷ የባለፉት 4 ዓመታት ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንደሆነ ያመላክታል።
/
Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.