ከባሮ ቱምሳ እስከ ሐጫሉ ሁንዴሳ፤ ከ”ደረጀ አማረ ተስፋ” እስከ በቲ ኡርጌሳ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ርስ በርስ በተገዳደሉ ቁጥር በአማራ እየተመካኘ በአማራ ላይ ሲካሄድ የኖረው የዘር ፍጅት! [ክፍል ፩]
የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝ በሚቆጣጠረው በሸዋ ምድር በደራ ወረዳ ከሁለት ወራት በፊት ደረጀ አማረ ተስፋ የሚል ስም የሰጠውን እና የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደሆነ የነገረንን የድኃ ልጅ በግፍ አርዶ በፋኖ ስም በማላከክ በአማራ ሕዝብ ላይ የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት የሚያስንቅ ሌላ ዙር የዘር ፍጅት እንዲካሄድ በሁሉም ልሳኖቹ ዘግናኝ የዘር ፍጅት ቅስቀሳ እንደ አዲስ ከፍቷል።
አረመኔው የዐቢይ አሕመድ የፍጅት አገዛዝ ደረጀ አማረ የተባለውን የድኃ ልጅ [በሚያርዱት ቪዲዮ ላይ የሚታየው ደረጀ አማረ ሳይሆን ሌላ ትልቅ ሰው እንደሆነ ልብ ይሏል] የኦሮምኛ ቅላጼ ባላቸው አራጆቹ ሲያርድ የሚያሳየውን ቪዲዮ ከሰሞኑ የለቀቀው ሌላው ሕዝብ ባያምነኝ ኦሮሞ የነገርሁትን ሁሉ ስለሚያምነኝ የምፈልገውን አላማ አሳካበታለሁ ብሎ በማሰብ በአማራ ሕዝብ ላይ የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት የሚያስንቅ ሌላ ዙር የዘር ፍጅት ለመፈጸም ነው።
ከዚህ ውጭ ሰው ሁሉ ለማሰብ ፍቃደኛ እንዳልኾነው ተከታዩ ሁሉ ያለውን ሁሉ ሳይጠራጠርና ሳይመረምር እውነት ነው ብሎ የሚወስድ፤ ሳጣራትና ሳያረጋግጥ እንደወረደ የሚቀበል ስላልሆነ፣ በምርኮ የያዛቸውን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጅ የመከላከያቸውን አባላት ወደቤተሰባቸው ሲመልስ የሚውለውን ፋኖ አንድን የደራ የድኃ ልጅ በኦሮሞነቱ ይገድለዋል ብሎ የሚያስብ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ አንጎሉን ያደነዘዘ ሕዝብ የለም።
አረመኔው ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የኦሮሞ ብሔርተኞች በሙሉ ያነገቡትን ጸረ ሰው አላማቸውን ለማሳካት የራሳቸውን ሰው እየገደሉ በአማራ ላይ ማላከክና ኦሮሞን ቀስቅሰው በአማራ ሕዝብ ላይ ዘግናኝ የዘር ፍጅት የመፈጸመ የኀምሳ አመታት የዳበረ ልምድ አላቸው። ይህን በማስረጃ እንደሚከተለው ማየት ይቻላል።
የዐቢይ አሕመድ የአፓርታይድ አገዛዝ ሐጫሉ ሁንዴሳን የገደሉት በኦነግ ታጣቂ ቡድን ተልዕኮ የተሰጣቸው የኦሮሞ ተወላጆች መኾናቸውን በወቅቱ “ዐቃቤ ሕግ” በነበረችው በአዳነች አበቤ አማካኝነት ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ በሰበር ዜና ነግሮናል። ሆኖም ግን ሐጫሉን ራሳቸው ገድለው ሲያበቁ ግድያውን በአማራ ስም በማላከክ ኦሮምያ በሚባለው የአማራ መታረጃ ቄራ ውስጥ በሚኖረው አማራ ላይ የሩዋንዳውን የዘር ፍጅት የሚያስንቅ ፍጅት ፈጸሙበት፤ ንብረቱን አቀደሙበት፤ ከዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር እስከ ዘጠና አመት አዛውንት በጅምላ አማራ የተባለን ሁሉ በጭካኔ ጨፈጨፉት። ጅፍቱን የፈጸሙት ላለፉት አራት አስርታት ሲተረክላቸውን የኖረውን ጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ለማጣራት ፍቃደኛ ያልሆኑ በአማራ ጥላቻ የሰከሩ ገዳዮች አልያም የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው።
ኦነጋውያን የትግል አባት አድርገው የሚቆጥሩትን ባሮ ቱምሳን የገደለው አብዱል ከሪም ኢብራሂም አሚድ ወይም በጫካ ስሙ ጃራ አባገዳ በመባል የሚታወቀው የእስላማዊ ኦሮሚያ ነጻ አውጪ ግንባር መሪ የነበረው የኦሮሞ ሸማቂ ነው። «ኦሮሞ ከፖለቲካ ሥልጣን ተገልሏል» ብሎ ኢስላማዊ ኦሮሚያን ለመፍጠር ጫካ የገባው ጃራ አባገዳ ወይም አብዱል ከሪም ኢብራሂም አሚድ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛና በሐረርጌ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የአውራጃ ገዢ የነበሩት የፊታውራሪ ኢብራሂም ሀሚድ ልጅ ነው።
ባሮ ቱምሳን ጃራ አባገዳ እንደገደለው ታሪኩን የነገረን የኦሮሞ ብሔርተኛው መረራ ጉዲና ነው። መረራ ጉዲና ይህን ታሪክ የነገረን በጦብያ መጽሔት በጥር 1988 ዓ.ም. «በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር በሌሎች ላይ የመጀመሪያውን ድንጋይ ወርዋሪ አይኾንም» በሚል ርእስ ባሳተመው ባለሁለት ክፍል ጽሑፉ ነው።
ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን የኦሮሞ ብሔርተኛት አባት የሚለው ዳኛ አሰፋ ዱላ ኢትዮጵያ ሆቴል ውስጥ የተገደለው ከኦሮሞው ጃራ መስፍን ጋር በጥይት ተጠዛጥዘው ሲኾን ርስ በርሳቸው ተገዳደሉበት የጠባቸው ምክንያትም በመካከላቸው የተፈጠረው ቁርሾ ነው። ኦነጋውያን ግን ለኦሮሞ ወጣቶች ያስተማሩት ዳኛ አሰፋ ዱላን አማራ እንደገደለው አድርገው ነው።
ኦነግ የኦሮሞ ትግል ምልክት ያደረገውን ጀኔራል ታደሰ ብሩን የመሬት ላራሹን አዋጅ ተቃወመ ብለው ከነ ጭሰኞቹ የገደሉትም ኦሮሞዎች ናቸው። መጋቢት 5 ቀን 1967 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ጋዜጣ ካወጣው ሪፖርት ማንበብ እንደሚቻለው ጄነራል ታደሰ ብሩ ከነጭስኞቻቸውና ከኮሎኔል ኃይሉ ረጋሳ ጋር ከሸፈቱበት አስሶ የያዛቸው የኦሮሞ ነገድ ተወላጁ ሻለቃ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ነው። ሻለቃ ተስፋዬ (ኋላ ሌተናት ጀኔራል) የኢትዮጵያ 11ኛው መከላከያ ሚንስትር ሲኾን ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ነበር።
ስለ ሻለቃ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ሲከነክነኝ የኖረውን አንድ ነገር ዛሬ ልተንፍሰው። ሻለቃ ተስፋዬ ታኅሣሥ 20 ቀን 1971 ዓ.ም. የብርጋዴር ጄነራልነት ሹመት ያገኘው ከሌተናት ኮሎኔልነት ተነስቶ ሁለት ማዕረግ በመዝለል ነው። የሻለቃ ተስፋዬ ማዕረግ መዝለል በዚህ አላበቃም። የመከላከያ ሚኒስቴር በኾነ ባመቱ በአንድም የጦር ሜዳ ሳይውል አንደኛ ደረጃ የጦር ሜዳ ሜዳይ ተሸላሚ ኾነ። ሁለት ዓመት ቆይቶ ደግሞ በየካቲት ወር 1974 ዓ.ም. ማዕረግ የመዝለል ታሪኩን በመድገም ከብርጋዴር ጄነራል ማዕረግ በቀጥታ የሌተናት ጄነራል ማዕረግ ተሰጠው። ይህ ሁሉ ሲኾን ሰጪውም አላፈረም ተሸካሚው ሻለቃ ተስፋዬም ከሻለቃነት ተነስቶ የሌተናት ጄነራልነት ማዕረግ ሲሰጠው ሳይከብደው ተቀበለው።
በኢትዮጵያ ሠራዊት ታሪክ (የወያኔን ጦር እንደ ኢትዮጵያ ሠራዊት አልቆጥረውም) እንዲህ ዓይነት የማዕረግ እድገት ያገኘው ብቸኛው የኢትዮጵያ ጄነራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ብቻ ነው። ማዕረግና እድገት ዋጋው ከፍ ያለ በነበረበት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቢኾን ኖሮ ግን ከሌተናት ኮሎኔልነት ወደ ብርጋዴር ጀኔራልነት ለማደግ ቢያንስ የ15 ዓመታት፤ ከብርጋዴር ጄነራልነት ወደ ሌፍተናት ጄነራልነት ለማደግ ደግሞ ቢያንስ 10 ተጨማሪ የአገልግሎት ዘመን ይጠይቅ ነበር። ሻለቃ ተስፋዬ ሌፍተናት ጄነራል የኾነው በእርሱ የሞያ አግባብ ቢያንስ 25 ዓመታት ተጨማሪ የአገልግሎትና የትምህርት ጊዜ የሚጠበቅበትን በመዝለል ነው። ወያኔዎች የሳንሲየርና የሳንድረስት ምሩቃን ጄነራሎች የነበሩትን (ደርግ የገደላቸውን) የኢትዮጵያ ጦር አሸነፍን የሚሉት እንደዚህ ዓይነት ከሻለቃ በላይ ጦር መርተው የማያውቁ የመንግሥቱ ኃይለ ማርያም መደዴዎችን ማሸነፋቸውን እንደ ድል እየቆጠሩ ነው።
ወደ ጄነራል ታደሰ ብሩ ታሪክ ስንመለስ ጄነራሉ እንደሸፈቱ እጃቸው እንዲያዝ አልያም እምቢ ካሉ እንዲደመሰሱ ትእዛዝ የሰጡት የደርጉ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት የወለጋው ኦሮሞ ኮሎኔል ተካ ቱሉ ናቸው። ጄነራል ታደሰ ተይዘው ልዩ የጦር ፍርድ በቀረቡ ጊዜ የልዩ የጦር ፍርድ ቤቱ ዐቃቢ ሕግ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ የነበሩ ሲኾኑ ዳኛው ደግሞ ኦሮሞው ሻለቃ በቀለ ነዲ ነበሩ። መረራ ጉዲናም ቀደም ሲል በጠቀስኩት ጽሑፉ ጄነራል ታደሰ ብሩ በኦሮሞ እንደተገደሉና ጄነራል እንዲገደሉ ሴራውን ያቀነባበረው ባሮ ቱምሳ እንደኾነ ጽፏል። ኃይሌ ፊዳ የሚመራው መ.ኢ.ሶ.ንም ጄነራል ታደሰ ብሩ ሲገደሉ “ፊውዳሉ” ታደሰ ብሩ እንደተገደለና የተወሰደውን ዐቢዮታዊ ርምጃም እንደሚደግፍ በልሳኑ መግለጫ አውጥቷል።
በሌላ አነጋገር ጄነራል ታደሰ ብሩ የተረሸኑት ከሸፈቱበት እንዲያዙ ወይም ካልኾነ እንዲረሸኑ ኦሮሞው ኮሎኔል ተካ ቱሉ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ኦሮሞው ጄነራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን ባካሄዱት ኦፕሬሽን ሲኾን፣ ጦር ፍርድ ቤት የቀረቡትና የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ደግሞ ኦሮሞው ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ዐቃቤ ሕግ በነበሩበትና ኦሮሞው ሻለቃ በቀለ ዳኛ ኾነው በተሠየሙበት የልዩ ጦር ፍርድ ቤት ውሳኔ መሠረት ነው። ይህ በጄነራል ታደሰ ብሩ ላይ የተላለፈው የግፍ ፍርድ በኦሮሞው በኃይሌ ፊዳ ድርጅት በመ.ኢ.ሶ.ን ተደግፎ ነበር። ኦነጋውያን እንደ ትግል ጀማሪያቸው የሚያዩትን የመኢሶኑን ኃይሌ ፊዳንም ዐቢዮታዊ ርምጃ እንዲወሰድበት የወሰኑትም (የወሰኑበት ሰነድ በእጄ ገብቷል) ኦሮሞዎቹ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ተስፋዬ ገብረ ኪዳን፣ ደበላ ዲንሳ እና ተካ ቱሉ ናቸው።
ይህ ብቻ ሳይኾን ሐውልት የቆመለትን የጡት ቆረጣ ታሪክ ሳይቀር በኦሮሞ ላይ የፈጸመው ኦነግ እንጂ አማራ አይደለም። ይህን ታሪክ ኦሕዴዶችም፣ ኦነጎችም፣ ወያኔዎችም ያውቃሉ። የኦሮሞን ጡት የቆረጠው ኦነግ መኾኑን የማይሞተውን የታሪክ ምስክርነት የሰጠን የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት የነበረው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ነው። ነጋሶ ጊዳዳ ‹‹ዳንዲ የነጋሶ መንገድ›› በሚል በተረከውና የሕይዎት ታሪኩን ባቀረበበት መጽሐፉ ገጽ 50፣ ኦ.ነ.ግ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሴት ወታደሮችን ማለትም ሴት የኦሮሞ ወታደሮችን ጡት ይቆርጥ እንደነበር ባይኑ ያየውን ታሪክ ነግሮናል። ነጋሶ ኦ.ነ.ግ የኦሮሞ ሴቶችን ጡት የቆረጠበትን ታሪክ የኦ.ነ.ግ አምበል የነበረው አባ ቢያ አባ ጆቢር አባ ጅፋር ሳይቀር በሽግግር መንግሥት ተብዬው ምክር ቤት ፊት ቀርቦ እንዳረጋገጠና የሰጠውም ምስክርነት በምክር ቤቱ ላይብረሪ ውስጥ በምስልና በድምጽ ተሰንዶ እንደሚገኝ ነግሮናል።
ለኦሮሞ ወጣቶች ግን እየተነገራቸው ያደጉት ቀደም ሲል የቀረቡትን ኦሮሞዎች ሁሉ የገደላቸውና የኦሮሞን ጡት የቆረጠው አማራ እንደኾነ ተደርጎ ነው። ይህም በመኾኑ ኦነጋውያን ለፖለቲካቸው መሳካት ኦሮሞን የመስዋዕት በግ እያደረጉ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲፈጽሙ የኖሩትን ግፍ ግን በአማራ የተፈጸመ እያስመሰሉ ያስተማሩትና አማራን እንዲያጠቃ እያሰለጠኑ ያሳደጉት አንድ ትውልድ፣ ፖለቲካውን አማራን መፍጀትንና የአማራ የመሰለውን ሁሉ ማውደም አድርጎታል።
ታዋቂ ኦሮሞዎች የሚባሉትን ሁሉ የገደላቸውና የኦሮሞን ጡት የቆረጠው አማራ እንደኾነ ሲነገረው ያደገው የኦሮሞ ወጣት ባለፉት ሳምንታት በኦሮሞዎቹ በጥላሁን ያሚ፣ አብዲ ዓለማየሁ እና ከበደ ገመቹ የተገደለውን የሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ለመበቀል የዘር ፍጅት ሲያካሄድ የሰነበተው ምንም በማያውቁ ምስኪን አማራዎች ላይ ነው። የዘር ፍጅቱ የተካሄደው ኦሮሚያ በሚባለው ክልል ልዩ ኃይል የሚደገፉ፣ በሁለተኛ መንግሥት (ማለትም በጃዋር መሐመድ በሚመራው መንግሥት) የዘር ፍጅት እንዲያካሂዱ የተደራጁ ቄሮዎች ቢኾኑም የዘር ፍጅት ለማካሄድ የሰለጠኑት የጃዋር መሐመድ ቄሮዎች ፍጅቱን በአማራዎች ላይ እንዲጀምሩ ኦሮሞዎች የገደሉትን ሐጫሉን አማራ እንደገደለው አድርገው የቀሰቀሱት ዋና ዋናዎቹ ግን ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ፣ ፀጋዬ አራርሳ፣ ሕዝቅኤል ጋቢሳ፣ ሄኖክ ጋቢሳ፣ ኢታና ሀብቴና የኦ.ኤም.ኤን ቴሌቪዥን ናቸው።
ከነዚህ ሁሉ የፍጅት ጠማቂዎች መካከል የሚገርመኝ ብርሃነመስቀል የሚባለው ጉድ ነው። አሜሪካን ሀገር ሲሠራ የኖረበትን የጥብቅና ፈቃድ ከተቀማ በኋላ ለአገዛዙ አድሮ አምባሳደር ለመኾን የበቃው ብርሃነመስቀል አበበ ‹‹ፊንፊኔ ለሁለት ሺህ ዓመታት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነበረች››፤ ‹‹ዐፄ ምኒልክ የኦሮሞን ሕዝብ በባዮሎጂካል ኬሚካል ፈጀተዋል ወዘተ›› እያለ ሲቀሰቅስ ይውል የነበረ ፕሮፓጋንዲስት ነው።
ብርሃነመስቀል አበበ አምባሳደርነት ለመሾም ጭራውን ይቆላ በነበረበት ወቅት የዐቢይ አሕመድ አገዛዝ በኦ.ነ.ግ ታጣቂ ቡድን ላይ ርምጃ እንዲወስድ ይመክር ነበር። በመካከላቸው በተፈጠረ የጥቅም ግጭት በተባረረበት ወቅትና አምነስቲ ከአንድ ዓመት በፊት በወለጋ በአግዛዙ ኃይሎች ተወሰደ ያለውን የኃይል ርምጃ ይፋ ባደረገበት ወቅት ዐይኑን በጨው አጥቦ አምነስቲ ያወጣውን ሪፖርት ‹‹በካፒታልዝም ስም የጭሰኛውን ሥርዓት መልሰው በሕዝባችን ላይ ሊጭኑ የሚቋምጡት አሃዳዊያን›› የፈጠሩት አድርጎ አቀረበው።
ብርሃነመስቀል ከተባረረ በኋላ ወለጋ የኾነውን ‹‹በካፒታልዝም ስም የጭሰኛውን ሥርዓት መልሰው በሕዝባችን ላይ ሊጭኑ የሚቋምጡት አሃዳዊያን›› ሲል ያቀረበውን፣ ከዐቢይ አሕመድ ጋር ተደምሮ ሽር ብትን ይል በነበረበት ጊዜ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል በተለይም ወለጋ ውስጥ ይካሄድ የነበረውን ግድያ ‹‹ጌታቸው አሰፋ በኦሮሞ ስም ያደራጃቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የከፈቱት የውክልና ጦርነት››፣ ‹‹በሕወሓት የሚታገዝ የኦሮሞ ካባ የለበሱ ጸረ ኦሮሞ አጀንዳ [አራማጆች]››፣ ‹‹[የኦሮሞ ካባ የለበሱ] ጃንጃዊዶች ሽብር›› በማለት ይገልጸው የነበረውንና ‹‹ጌታቸው አሰፋ በኦሮሞ ስም ያደራጃቸው ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳዮች››፣ ‹‹በሕወሓት የሚታገዝ የኦሮሞ ካባ የለበሰ ጸረ ኦሮሞ. . . ››፣ ‹‹ጃንጃዊድ›› ሲል በገለጻቸውና ወለጋ ውስጥ ኦሮሞን አሸበሩ ባላቸው ሸኔዎች ላይ መንግሥት ትዕግስቱ አብቅቶ ርምጃ ሊወስድባቸው ይገባል እያለ በመከረው መሠረት የተወሰደውን የኃይል ርምጃ ነው። ብርሃነመስቀል ከውስጥ አዋቂዎቹ የሐጫሉን መገደል እንደሰማ ‹‹ኢትዮጵያ ኦሮሞን ገደለች›› ብሎ ጻፈ። ቀጠለና ሐጫሉን ነፍጠኞች (አማሮች ማለቱ ነው) እንደገደሉት ጻፈ። በአማሮች ላይ ያ ሁሉ ፍጅት የተካሄደው ይህን መሰሉን የጥላቻ ዘመቻ ተከትሎ ነው።
የፍጅት ጠማቂዎቹ ወደፊት ለሚመጣው የኦሮሞ ትውልድም ርስ በርሳቸው እየተገዳደሉ አማራ ኦሮሞን ገደለው እያሉ ማመካኘታቸውን ይቀጥላሉ። ነገ በሚጽፉት ታሪክም ዛሬ በኦሮሞዎቹ በጥላሁን ያሚ፣ አብዲ ዓለማየሁና ከበደ ገመቹ እንደተገደለ የተነገረውን ሐጫሉ ሁንዴሳን አማራ እንደገደለው አድርገው ማስተማራቸውን አይተዉትም። ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በነበራቸው የማኅበራዊ ሜዲያ ተሳትፎ ለማሰብ ፍቃደኛ ላልኾነው ወጣት ሲነግሩ የቆዩት ይህንን ዓይነት በፈጠራ ታሪክ ላይ የተመሠረተ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳቸውን ነው።
ባጭሩ እነዚህ የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እያመረቱ የኦሮሞን ወጣት አማራ የኦሮሞን መሬት ቀምቶ እንደሰፈረ፣ አማራ ኦሮሞን እንደጨፈጨፈና ጡት እንደቆረጠ ሲያስተምሩ የከረሙ፣ ለበቀልና ለዘር ፍጅት ሲያሰለጥኑ የከረሙ የኢትዮጵያ ጁቪናል ሃቢያሪማናዎች ናቸው። በጃዋር መሐመድ የሚመራውና የዘር ፍጅቱን ያካሄደው ቄሮም የተደራጀው ሩዋንዳ የተካሄደውን የዘር ፍጅት ያካሄዱትና በቱትሲዎች ጥላቻ የሰከሩ ወጣቶች ኅብረት የነበረውን የኢንተርሐሞይ ትጥቅና ዝግጅት እንዲኖረው ተደርጎ ነው።
በቴ ኡርጌሳን በድቅድቅ ጨለማ ካረፈበት ሆቴል አውጥተው በራሱ ቀበቶ የፍጥኝ ካሰሩ በኋላ በጥይት ደብድበው የገደሉት የኦሮምያቸው ልዩ ኃይል አባላት ናቸው። ይህንን የራሳቸውን ግድያ ግን ለኦሮሞ ሕዝብ የነገሩት ግድያውን “ኢትዮጵያ መንግሥት” እንደፈጸመው አድርገው ነው። ግድያውን የኦሮምያቸው መንግሥት ተብዮው ፈጽሞት ሳለ እነሱ “የኢትዮጵያ መንግሥት” በሚሉት የሚያላክኩት ኢትዮጵያዊ አይደለህም ብለው ሲያሳስቱትና “የኢትዮጵያ መንግሥት” ማለት “የአማራ መንግሥት” ነው እያሉ ሁለት ትውልድ ያደረጉት ተከታያቸው ግድያውን “የኢትዮጵያ መንግሥት” ፈጸመ ሲባል አማራ እንደፈጸመው እንደሚቆጠርላቸው ስለሚያምኑ ነው። እነዚህ የኦሮሞ ብሔርተኞች ወርቅ ወይም አልማን በሩጫ ያገኘን አንድ የኦሮሞ አትሌት ሲያስተዋውቁ “የኦሮምያ” ወይም የኦሮሞ አትሌት ብለው እንጂ የኢትዮጵያ አትሌት ብለው አይደለም። የኦሮምያቸው ልዩ ኃይል የፈጸመውን የበቲ ኡርጌሳን ግድያ ግን “የኢትዮጵያ መንግሥት” የፈጸመው አድርገው በውስጠ ታዋቂ ራሳቸው የኦሮሞ መንግሥት ሆነው የፈጸሙትን ወንጀል ሌላ አካል ፈልገው በማላከክ ጸረ አማራ አረመኔ አላማቸውን ለማሳካት ተጠቅመውበታል።
አረመኔዎቹ የኦሮሞ ብሔርተኞች ከሰሞኑ የኦሮምኛ ቅላጼ ባልተላቀቀው አንደበታቸው በአማርኛ “በሲማም” እያሉ ድኃ በማረድና በቪዲዮ በመቅረጽ ፍቃደኛ ያልሆነውን ተከታያቸውን ለመቀስቀስ እያሰራጩት የሚገኙት ሰቅጣች ድርጊታቸው ለኀምሳ አመታት ሙሉ የተካኑበትን ትራጄዲያዊ ድራማ መስራት ላቅ ወዳለ ደረጃ ያሸጋገሩበትና የራሳቸውን የአረመኔነት ክብረ ወሰን የሰበሩበት ሆኖ ተመዝግቧል።
ይቀጥላል…
አቻምየለህ ታምሩ