Breaking News
Home / Amharic / የአብን ፅህፈት ቤት ኃላፊ በለጠ ካሳ መኮነን ከቂሊንጦ እስር ቤት ለልጁ ህፃን ምኒልክ በለጠ የላከው ደብዳቤ

የአብን ፅህፈት ቤት ኃላፊ በለጠ ካሳ መኮነን ከቂሊንጦ እስር ቤት ለልጁ ህፃን ምኒልክ በለጠ የላከው ደብዳቤ

ቀን 22/04/2012 ዓ.ም

ለልጄ ምኒልክ በለጠ
~~~~~~~~~~~

በባርነት ውስጥ ብትወለድም በነፃነት መኖርህ አይቀርም፡፡ ቂሊንጦ እስር ቤት መጥተህ በፍርግርግ ሽቦና ቆርቆሮ አጥር እኔን ለመጠየቅ ስትንጠለጠል በደረሰብህ እጅህን የመቀርደድ አደጋ በእጅጉ ልቤ ተነክቶ አዝኛለሁ፡፡ አንተም የፈሰሰውን ደም እያዬህ ያለቀስከው ለቅሶ ሁሉንም እስረኛና የእስረኛ ጠያቂ ቤተሰብ ከልብ አሳዝኗል፡፡ የጥበቃ ፖሊሶች ሳይቀር ህሊናቸው ተነክቶ የሚችሉትን የድጋፍ ሙከራ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡

አሁን አንተ አምስት አመት ሊሞላህ የቀረህ ትንሽ ጊዜ ነው፡፡
ጊዜው የአንተ የመጫወቻ የመቦረቂያ ስለነገው የነፃነት ዋስትና በምከፍለው ስቃይ አባትክን ፍለጋ እስር ቤት እየተመላለስክ ነው፡፡ መመላለስህ ሳይበቃ ይሄው የማትቸለውን ስቃይ እያየህ ነው፡፡ በቁስል እንድትንሰፈሰፍም ሆነሃል፡፡ ከህፃን ገላህ ላይ የፈሰሰው ደምህ ስለነፃነት በሚደረግ ጉዞ የፈሰሰች ጠብታ እንደሆነች ዛሬ ባትረዳም ወደፊት ነፍስ ስታውቅ ኩራት እንደሚሆንህ አልጠራጠርም፡፡

እኔ ከታሰርኩ ጀምሮ ብዙ ነገር እንደጎደለብህ አውቃለሁ ፡፡
ማታ ማታ የማወራህ ተረት የለም ፤ ትምህርት ቤት አልሸኝህም፤ የአባት ፍቅር ጎድሎብሃል አውቃለሁ፡፡

ልጄ ምኒልክ አይዞህ ! አሁን እያጋጠመህ ያለው ናፍቆትና የአባት ስስት ነገ ከሚያጋጥምህ ዘላለማዊ ባርነት አይበልጥም፡፡ ዛሬ እኔ አባትህ ይሄንን ዋጋ ከፍዬ ወደ ነፃነት ማማ ካላወጣሁህ በምትኮራበት የአባቶችህ ታሪክ እንድትሸማቀቅ ትገደዳለህ ፤ በስምህም ምኒልክ በለጠ ተብለህ አትጠራም፡፡ ዘላለማዊ ባርነት ውስጥ መኖር ስለሌለብህ ይህን ትግል ማድረግና ለረጅሙ የነፃነት ጉዞ ራስን መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡
ልጄ አንተ ህፃን ስለሆንክ ሁሉም ነገር አይገባህም ፡፡ ነገር ግን ቆርቆሮ የቆረጠው እጅህ ምንም በቢሆን ጠባሳው ይኖራል ይሄም የእስር ቤቱ ማስታወሻ ይሆናል፡፡

ልጄ ምኒልክ የሚል ስም ያወጣሁልህ የነፃነትን ዋጋ አብዝቼ ስለምረዳ ነው፡፡ ምክንያቱም በምድር ላይ ለግማሹ ህዝብ (ለጥቁር የሰው ለልጆች) ነፃነትን ያቀዳጀው የአድዋው ዘመች ጥቁሩ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ነውና፡፡

አዎ ! ምኒልክ ያላወረሰኝን ባርነት አላወርስህም፡፡ የተከሰስኩበት ጉዳይ ለአንተ በባይገባህም ወደፊት እስከምትረዳው መጠበቅ አልፈለኩም፡፡ ምክንያቱም አንተም አብረህ ታስረሃልና ነው፡፡ የአባትህ መታሰር ያንተም ሆኖ ይሄው የቂሊንጦ እስር በቤት አጥር አንተንም የልጅ ገላህን በመተልተል ደምህን አፍስሶታል፡፡

እኔ

“ወልቃይት የአማራ ነው ወልቃይትም በኮሚቴ ልመና አይመለስም ፤ በብአዴንን ህዝብ እንዳያምነው ፤ የአባቶቻችን ዳር ድንበር የመተማ መሬት መጠበቅ አለበት”

የሚል ቅስቀሳ አድርገሃል የሚል ክስ ቀርቦብኝ ለጊዜው እኔን ከአንተ ለይተው አጎብዳጅ የአማራ ወኪል ነን ባዮች ቢያስሩኝም የታሰርኩበት አላማ አንተን የሚያኮራ ፤ ነገ አንገትክን የማትደፋበት ፤ የአሳሪዎቼ ልጆች የሚያፍሩበት ታሪክ እየተሰራ ነው፡፡

በመጨረሻው ጊዜ የድል ዋንጫ ስንጨብጥ አንተም እድሜህ ታሪክ መመርመር ሲጀምር ሁሉንም ትረዳዋለህ፡፡ እስከዚያው አንተም በርታልኝ ጠንክርልኝ ፤ ቀቁስሉም ቶሎ ይሽርልሃል፡፡ አእርግጥ ነው አሁን ወጥቼ አላሳከምኩህም ሆኖም ግን ካሉት ፈተናዎች መጨረሻ ነፃነት ሲመጣ ደጋግመህ የምትመካበት ታሪክ እየሰራሁልህ መሆኑን ትረዳለህ፡፡

ሁሉንም ክስተቶች በማስታወሻ በማስታወሻ እየፃፍኩ ለአንተና ለሌሎች የታሪክ ሰነድ ሆኖ እንድቀመጥ የማድረጉን ስራም አላቋረጥኩትም፡፡ ታሪክ መስራትም ታሪክ መመዝገብም ዕለታዊ ተግባሬ ሆኗል፡፡

በመጨረሻም በአማራ ህዝብ ጠንካራ ትግል ከቂሊንጦ እስር ቤት እስከ ዛሬ የተቋረጠብህን የአባትነት ፍቅር በእጥፍ እንደምከፍልህ አልጠራጠርም፡፡

ልጄ ይሄንን የምልህ ታህሳስ 21/2012 ዓ.ም የፍርድ ቤት ቀጠሮ የህዝባችን ዕልህና ቁጭት ከእምባ ጋር እየታገልኩ ፣ ከዕልህና ሲቃ ጋር እየተናነኩ የማየት እድል ስለነበረኝ ነው፡፡

ልጄ ምኒልክ ፤ ስለታላቁ የአማራ ህዝብ የምችለውን ዋጋ መክፈሌ ከላይ እንደነገርኩህ የነፃነት ብቻ ሳይሆን በግልህም የኩራት ካባህ ነው፡፡

ይሄንን ደብዳቤ ስፅፍልህ በህፃን እድሜህ አንተም ለአማራ ህዝብ እየከፈልክ ያለኸውን የነፃነት ትግል አለም እንድያውቀው ለማድረግ ነው፡፡

አንተም በትምህርትህ በርትተህ ለአገር አለኝታ ለታናሽ ወንድምህ #ለአስከብር_በለጠም አርዓያ እንደምትሆን እተማመናለሁ፡፡

የዛሬ አሳሪዎቼ የአጎብዳጆቹ ነገ በአባቶቻቸው ታሪክ ያፍራሉ፤ ይሸማቀቃሉ፡፡

አንተ ግን ትኮራለህ !!

ተጻፈ፡ ከአባትህ በለጠ ካሳ

ቂሊንጦ !!

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.