Breaking News
Home / Amharic / የአቢይ አህመድ አገዛዝ ፋኖን አልቻለውም!

የአቢይ አህመድ አገዛዝ ፋኖን አልቻለውም!

ሶስት ሳምንት ብለው 9 ወር ሆነ፣ አገዛዙ አልቻለም #ግርማካሳ

አገዛዙ በአማራ ክልል ጦርነት በይፋ የጀመረው ሚያዚያ 20 ቀን 2015 ዓ/ም ነበር፡፡ በሶስት ሳምንታት ውስጥ ፋኖዎችን ትጥቅ እናስፈታለን ብለው ዝተውና ተማምለው ነበር በጥጋብና በጀብደኝነት ጦራቸውን በጎንደር፣ በሸዋ፣ በወሎና በጎጃም ያሰማሩት፡፡ ያኔ የነበሩ የፋኖ አደረጃጀቶች የተወሰኑ ነበር፡፡ እንኳን እነዚህ የተወሰኑትን ሊያጠፉ፣ እንደዉም በየቦታው ህዝቡ፣ ገበሬው፣ ከተሜው ነፍጡን አንስቶ ተነሳባቸው፡፡ በፊት ከነበሩት በብዙ እጥፍ አዳዲስ የፋኖ አደረጃጀቶች ተፈጠሩ፡፡ የአገዛዙ ጦር በተሰማራበት ቦታ ሁሉ ሽንፈቶችን መከናነብ ጀመረ፡፡

ከሚያዚያ 20 እስከ ሐምሌ 20 ቀን ፋኖዎች በአስደማሚ ሁኔታ ራሳቸውን መከቱ፡፡ ከሐምሌ 20 እስከ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ/ም የማጥቃት ዘመቻዎችን አድርገው ምን ማድረግ እንደሚችሉ በተግባር አሳዩ፡፡ ከደሴና ኮምቦልቻ በቀር በክልሉ ያሉ ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ፣ ከ46 በላይ ከተሞችን፣ ከ120 በላይ ወረዳዎችን ተቆጣጠሩ፡፡ የክልሉ የብልጽግና መዋቅርን፣ የአማራ ብልጽግና ወይንም ብአዴንን አፈራረሱ፡፡ እነ ይልቃል ከፍያለና ሰማ ጥሩነህ የመሳሰሉ የአገዛዙ ጉጅሌዎች ወደ አዲስ አበባና ናዝሬት ኮበለሉ፡፡

አገዛዙ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ/ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ፡፡ እንደ ሱዳን ወይንም ግብጽ ካሉ የዉጭ አገራት ጋር የሚደረግ ጦርነት ይመስል፣ የአገሪቷን የመከላከያ ጦር በስፋት በአማራ ክልል አንቀሳቀሰ፡፡ የተለያዩ ኦፕሬሽኖችን በተለያዩ ጊዜያት አደረገ፡፡ አገሪቷ ካላት አምስት እዞች ( ስሜን ያው ፈርሷል)፣ ትላልቆቹ በጀነራል ብርሃኑ በቀለ የሚመራው የሰሜን ምዕራብ ዕዝና በጀነራል መሃመድ ተሰማ የሚመራው የምስራቅ ዕዝ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁለቱም እዞች በጎንደር፣ ወሎና ጎጃም በስፋት ተንቀሳቅሱ፡፡ በጀነራል ሹማ አብደታ የሚመራው የአየር ወለድ ጦርና የሪፓብሊካን ጋርዶች በስፋት በሸዋ ተሰማሩ፡፡ የተወሰነም ኃይል ከደቡብ እዝ ሳይቀር እንዲሰለፍ ተደረገ፡፡ አየር ኃይል ያለውን አቅሙን በሙሉ ተጠቀመ፡፡ የአገዛዙ ጀነራሎች በእጃቸው ያለ ያልተጠቀሙት መሳሪያ የለም፡፡ የጦር ጀቶች፣ ድሮኖች፣ ታንኮች፣ መድፎች ኧረ ስንቱ ይዘረዘራል፡፡

ሆኖም አገዛዙ አልቻለም፡፡ በበርካታ አውደ ውጊያዎች በሽንፈት ላይ ሽንፈት ተከናነበ፡፡ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ወታደሮቹ አንዋጋም ብለው እጆቻቸውን ለፋኖ ሰጡ፡፡ ብዙዎችም ፋኖን ተቀላቀሉ፡፡ ፋኖዎች እንኳን ሊሸነፉ የበለጠ እየተደራጁ ፣ እየተሰባሰቡ ከመንደር አደረጃጀት ወደ ሻለቃ፣ ከሻለቃ ወደ ብርጌድ፣ ከብርጌድ ወደ ክፍለ ጦር፣ ከከፍለ ጦር ወደ ዕዝ እየተሸጋገሩ ነው፡፡ የጎጃም እዝና የጎንደር ዕዝ በይፋ ተቋቁሟል፡፡ የጎጃም እዝ አዛዥ ሻለቃ ዝናቡ፣ የጎንደር እዝ አዛዥ ሻለቃ ሃብቴ እንዲሆኑ ተድርጎ በጎጃምና በጎንደር የፋኖ እንቅስቃሴ በወታደራዊ አደረጃጀትና ዲሲፕሊን አንጻር ትልቅ እርምጃ ወደፊት እንዲሄድ የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡

በሸዋና በወሎ ዕዝ በመመስረቱ ጉዳይ አንዳንድ መንገጫገጮች አሉ፡፡ ቢሆን ንግግሮች እየተደረጉ ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አውጀው፣ እዚያ በፊትም ለሶስት ወራት፣ ለውጥና ድሎች ያስገኙ ይመስል፣ የኦሮሞ ብልጽግናዎች፣ ጥር 24 ቀን 2016 ዓ/ም፣ “በእቅድ ያላጠናቀቅነው ስራ አለ” በሚል፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጃቸውን ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም አድርገዋል፡፡ ይህን ማድረጋቸው፣ መሸነፋቸውን፣ የዛቱትንና እናደርገዋለን ብለው ደረታቸውን የነፉበትን ማድረግ አለመቻላቸውን እንዳመኑ የሚያሳይ ነው፡፡

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.