Breaking News
Home / Amharic / የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የታሰሩ አመራሮቹንና አባላቱን ለማስፈታት የተለያዩ የትግል ስልቶች መንደፉን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶር ደሳለኝ ጫኔ ተናገሩ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የታሰሩ አመራሮቹንና አባላቱን ለማስፈታት የተለያዩ የትግል ስልቶች መንደፉን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶር ደሳለኝ ጫኔ ተናገሩ

***
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአመራሮቹና በአባላቱ ላይ እየተፈፀመ ያለው እስርና ወከባ የፓርቲዎች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መርህን የጣሰ መሆኑን በመጥቀስ፣ በቀጣይ ራሱን ከስምምነቱ ሊያገል እንደሚችል ያስታወቀ ሲሆን የታሰሩትን አባላቱን ለማስፈታት የተለያዩ የትግል ስልቶች መንደፉን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

ንቅናቄው በአባላቱ፣ በአማራ የመብት ጥያቄ አራማጆችና አንቂዎች ላይ መጠነ ሰፊ እስራት መፈፀሙን ጠቁሞ የታሰሩትን ለማስፈታት በቅድሚያ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የተደራጀ አቤቱታ ለማቅረብ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ለሚመለከታቸው የመንግስትና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ጥያቄ እናቀርባለን ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ ይህ አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ የታሰሩ የማይፈቱ ከሆነ ንቅናቄው ሰላማዊ ሰልፎችን ጨምሮ ሌሎች የሰላማዊ ትግል አይነቶችን በሙሉ ተጠቅሞ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር መወሰኑን አስታውቀዋል።

የአመራሮቹንና አባላቱን እስር አስመልክቶ ሊወስድ ባሰባቸው ፖለቲካዊ እርምጃዎች ዙሪያ ምክክር መደረጉንና በቅድሚያ እንዲፈቱ ለመንግስት ይፋዊ ጥያቄ ማቅረብን እንደሚያስቀድም የጠቆሙት ሊቀመንበሩ ጥያቄው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ግን ወደ መጠነ ሰፊ ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንደሚገባ አስረድቷል፡፡

የአባላቱን እስር በተደጋጋሚ ለጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤትና ለፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቢያቀርብም እስካሁን ቀና ምላሽ አለማግኘቱን በመጠቆም ፓርቲዎች የሚተዳደሩበት የቃል ኪዳን ስምምነት በኢህአዲግ የማይከበር ከሆነ ንቅናቄያቸው ከስምምነቱ ራሱን እንደሚያገልም አስታውቀዋል፡፡“አሁን እየተፈፀመ ያለው የጅምላ እስርና እንግልት የጋራ የቃል ኪዳን ሠነድ ሥምምነቱን ባልተከተለ መንገድ ነው” ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ “ድርጊቱም የዜጎችን የፖለቲካ ጥያቄ በኃይል የማፈንና የመድፈቅ ተግባር ነው” ብለዋል፡፡

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለታሰሩት የንቅናቄው አባላት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባው ያስገነዘቡት ሊቀመንበሩ በአማራ ተወላጅ የመንግስት ተቋማት ሠራተኞች፣ በመላ አገሪቱ በሚገኙ አብን አባላትና አመራሮች፣ በሕግ ባለሙያዎች፣ በጋዜጠኞችና ጦማሪያን ላይ በጅምላ እየተወሰደ ያለው እርምጃ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው አስታውቀዋል፡

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.