የአማራ ባንክን ሥራ ለማስጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን አቶ መላኩ ፋንታ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 08/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ መላኩ ፋንታ በተለይ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ በምስረታ ላይ ያለውን አማራ ባንክ ሥራ ለማስጀመር እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ መላኩ ማብራሪያ ባንኩን ፈቃድ የማሰጠትና ሥራ የማስጀመር ሂደት ሦስት ምዕራፎች አሉት፡፡ የመጀመሪያው የቅድመ-ምስረታ ምዕራፍ ሲኾን የንግድ ስያሜ ማውጣት፣ ከብሔራዊ ባንክ አክሲዮን የመሸጥ ፈቃድ የማግኘትና አካውንት የማስከፈት ተግባራት ይከናወኑበታል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ጠቅላላ ጉባዔ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ አክሲዮን በስኬት የተሸጠበት፣ ጠቅላላ ጉባዔ የተደረገበት፣ ከጉባዔተኛው ጋር የመመስረቻና መተዳደሪያ ደንቦች እንዲሁም ሌሎች ሰነዶች በተሳካ ሁኔታ የጸደቁበት ነው፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ፈቃድ ለማግኘት ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ የሚቀርብበት ነው፤ ለዚህም ቃለ ጉባዔዎችን፣ መመሥረቻና መተዳደሪያ ሰነዶችን፣ የተመረጡ ዕጩ የዳይሬክተሮች ቦርድ እንዲሁም የባለአክሲዮኖች መረጃ ተሟልተው መቅረብ አለባቸው፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግም በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ እንዲመዘገብ ተደርጎ የባንክነት ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡
የሁለተኛው ምዕራፍ ሂደቶች በተሳካ ሁኔታ መተግበራቸውን የገለጹት አቶ መላኩ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ በቀረቡት ሰነዶች ላይ ዝርዝር አስተያዬት እንደሰጠባቸው አብራርተዋል፡፡ በተሰጡ አስተያዬቶች ላይ እየተሠራ ሲኾን ተግባሩ እንደተጠናቀቀ ፈቃድ በማግኘት ሁለተኛው ምዕራፍ የሚጠናቀቅ ይኾናል ብለዋል፡፡
በሦስተኛውና የመጨረሻው ምዕራፍ የባንኩን ዋና መሥሪያ ቤት መቀመጫ መወሰን፣ የሰው ኀይል፣ የብራንድ ጉዳይ፣ ስትራቴጂና የቢዝነስ ፕላን ምን መኾን እንዳለበት፣ የፖሊሲ ጉዳይ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ባንኩ አገልግሎት ለመስጠት ብቁ መኾኑ ተገምግሞ የባንክ ሥራ እንዲጀምር ፈቃድ የሚሰጥበት ነው፡፡ ለሦስተኛው ምዕራፍ የሚረዱ አብዛኛዎቹ ተግባራት መጠናቀቃቸውንም አንስተዋል፡፡ ሂደቶቹ በታሰቡት ልክ ከተሳኩም በመጪው መስከረም ሥራ ለመጀመር መታሰቡን ነው ያስታወቁት፡፡ አቶ መላኩ እንዳሉት ባንኩን ሥራ ለማስጀመር የሚከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ናቸው፡፡
አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከ191 ሺህ በላይ ባለአክስዮኖች አሉት፡፡ ከ6 ቢሊየን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል እና ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ቃል የተገባ የገንዘብ መጠንም አከማችቷል፡፡ አሁን ያለው የካፒታል መጠን በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ የሚባል ሲኾን በሀገሪቱ ከሚገኙ የግል ባንኮችም ቀዳሚውን ስፍራ እንዲይዝ አድርጎታል፡፡
ተከፋይ የኾነው የካፒታል መጠኑ 12 አዳዲስ ባንኮችን የማቋቋም አቅም አለው፤ ቃል የተገባው ደግሞ 16 አዳዲስ የግል ባንኮችን የማቋቋም አቅም እንዳለው ተነግሮለታል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
Amhara Bank Registration
Amhara Bank Registration