Breaking News
Home / Amharic / የጀኔራል አሳምነው ጽጌ አስከሬን ወደ ቤተሰባቸው ተሸኝቷል፡፡

የጀኔራል አሳምነው ጽጌ አስከሬን ወደ ቤተሰባቸው ተሸኝቷል፡፡

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 19/2011ዓ.ም (አብመድ) በአማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተጠርጥረው የነበሩት ብርጋዲዬር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ትናንት ሕይወታቸው ማለፉ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 አካባቢ በአማራ ክልል ‹የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ› መደረጉን መንግሥት መግለጹ እና የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እና የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩት ጀኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው የሚታወስ ነው፡፡ ለድርጊቱ ተጠርጣሪ ሆነው ሲፈለጉ የነበሩት የአማራ ክልል የሠላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዲዬር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ሰኔ 17 ቀን 2011ዓ.ም ከባሕር ዳር ከተማ ቅርብ ርቀት ዘንዘልማ አካባቢ በተኩስ ልውውጥ ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል፡፡ አስከሬናቸውም ወደ ቤተሰቦቻቸው ትናንት መላኩ ታውቋል፡፡
ብርጋዲዬር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ በ1970ዎቹ አጋማሽ ኢህዴን (ብአዴን/አዴፓ) በትጥቅ ትግል እያለ ወደ ትግሉ ተቀላቅለዋል፡፡ ከትጥቅ ትግሉም በኋላ በተለይ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጅ በ2001ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወንጀል ተከስሰው የዕድሜ ልክ እስር ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ በተለይ ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ በነበሩት ተከታታይ የሕዝብ ጥያቄዎችና በተፈጠረው ለውጥ ከእስር ከተፈቱ እስረኞች መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡

ከእስር እንደተፈቱም በሀገሪቱ በተጀመረው የለውጥ ሙሉ ማዕረጋቸውና ጥቅማቸው የተመለሰላቸው ብርጋዲዬር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የአማራ ክልል የሠላምና ሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነውም ሲያገለግሉ ነበር፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማቀነባበር የተጠረጠሩት ግለሰቡ በመጨረሻም ለሕግ ሳይቀርቡ ሕይወታቸው ማለፉ ተነግሯል፡:

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.