Breaking News
Home / Amharic / የሕልውና ትግል ወይስ የሥልጣን ሽኩቻ?

የሕልውና ትግል ወይስ የሥልጣን ሽኩቻ?

የሕልውና ትግል ወይስ የሥልጣን ሽኩቻ?

በዚያ ታላቅ የአማራ ሕዝብ የሕልውና ትግል ሥም ጥቂት የሥልጣን ጥመኞች ራሳቸው መንገሥና ዘውድ መጫን መፈለጋቸው በእጅጉ ያሳዝናል። መጀመሪያውኑ አንድ ሕዝባዊ ትግል በፌስቡክና በቲክቶክ እንዲሁም በዩቱበር ሳንቲም ለቃሚ አውታሮች ሊመራ እስከተሞከረ ድረስ ዓላማውንና ግቡን መምታቱ በጣሙኑ አጠራጣሪ ነው። ይችን ጦማር እየከተብኩ ባለሁበት ሰዓት አንዲት በቲክቶክና በፌስቡክ የሚታወቁ ወ/ሮ በቲክቶክ መስኮታቸው ብቅ አሉና “…እስኪ እዩት እጁን የእስክንድርን አማራ እኮ አይመስልም…: ብለው ሲናገሩ ስሰማ ሰው ከነ-ልብሱ ማበዱን ነው የተረዳሁት። በሴትዮዋ ግንዛቤ አማራ መሆን በእጅና በእግር የሰውነት አካሉ ተለይቶ ይታወቃል ማለት ነው። አጃኢብ ያሰኛል። አሁንም ሕዝበኝነትን ባለማስቀደምና በቲፎዞ ባለመከበብ ከእውነታ ጋር በመወገን ወደ ቀልብ መመለስ ያስፈልጋል።

በእኔ እምነት በትግሉ ዙሪያ ተቋምም እየተመሠረተ፣ መዋቅርም እየተዘረጋ አይመስልም። በተቧደኑ ግለሰቦች ዙሪያ የሥልጣን መያዝ ሽኩቻ ነው እየተካሄደ ያለው። አንድ አማራ፣ አንድ ፋኖ … ወዘተ የመሳሰሉት ይህን ኅብረተሰብ አንድ የመሆን መግለጫነት በፕሮፓጋንዳ መልክ ቢስተጋቡም መሬት ላይ አማራው አንድ አይደለም። አንዲት ቲክቶከር :…ሸዋዎች የተሸወዱት እስክንድር ሸዌ መስሏቸው ነው። እስክንድር በአንድ በኩል ጎጃሜ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ጎንደሬ ነው…” ብላ ስትበጠርቅ መስማት “አማራው አንገቱ አንድ ነው” ከሚለው ስብከትና መፈክር ጋር ይፃረራል። በትግሉ ዙሪያ ተቋም ወይም ድርጅት እየተገነባ ቢሆን ኖሮ የድርጅቱ የትግል መርሆዎች ላይ ወደ አንድነት ሳይመጣ ሁለት ዓይነት የአማራ ትግል የአካሄድ መርሆች ሳይታረቁ ለሁለት የተለያዩ የመታገያ መርሆች ሊያገለግል የሚችል አንድ አመራር መሰየም አግባብነት አይታይበትም። ሁለቱን ዓይነት የትግል መርሆዎች እየተከተሉ እስከ ተጓዙ ድረስ ወደ አንድ መምጣት ባልቻሉበት ሁኔታ አንድ ዓይነት አመራርም ሊኖራቸው አይችልም።

በመሆኑም ፋኖዎች ምርጫ ከማካሄዳቸው በፊት ማድረግ የነበረባቸው፣ በየትኛው የመታገያ መርህ እንደሚመሩ መወሰን ማለትም፣

ሀ/ መነሻችን አማራ፣ መዳረሻችንም አማራ

ለ/ መነሻችን አማራ-መዳረሻችን ኢትዮጵያ

በሚሉ የተለያዩ የፓለቲካ መርሆዎች እየተመሩ አንድ ዓይነት አመራርም ሊኖራቸው አይችልም። ግራ ያጋባል? አንድ ዓይነት አመራር ይኑራቸውም ተብሎ ግራ-ቀኙ ተስማምተው ምርጫም ከተካሄደ፣ በምርጫና በዲሞክራሲ የአሰራር መርሆ መሠረት አብላጫ ድምፅ ያገኘውን አመራር አለበት ከተባለው ከነ ችግሩ መቀበል አስፈላጊ ነበር። ለምርጫ መሥፈርት ካዋጧቸው መመዘኞዎች በአንደኛው የማይፈልጓቸውን ሰዎችና አካባቢ ከጨዋታ ውጭ ማድረግ ተችሏል። በእዚህ የተደሰተ አካልም አለ። መጀመሪያውኑም የመጀመሪያው መመዘኛ ለማንሳፈፍ የተፈለጉ ግለሰቦችና አካባቢም ስለነበር በዚያ ግባቸውን የመቱ ሤረኞች አሉ። ተሳክቶላቸዋል። ሁለተኛው መመዘኛ ያጣላው ግን የምርጫው ውጤት ሲታወቅ “…እኔ ካልተመረጥኩ..” ሁሉም ገደል ይግባ ዓይነት የእልህ ውሳኔ ይመስላል። በጣምም አሳፋሪ ነው። ወደ ምርጫ ሲገባ፣ ምንም ይሁን ምን ውጤቱን መቀበል የምርጫ ጨዋታ ሕግ ይነግረናል። ውስጣዊ የሥልጣን ፍላጎታቸውን ደብቀው ማስቀረት ከማይችሉበት ደረጃ ሲደርሱ ወደ ተለመደው የሥም መጠፋፋትና የመፈራረጅ ጥንብ የፓለቲካ አካሄድ መከተል ተጀመረ።

አሁንም የራስን አካሄድ ደካማ ጎን በውጫዊ ምክንያት ለመሸፋፈን ከመሯሯጥ ራስን ወደ ውስጥ ማየት የግድ ያስፈልጋል። አንዳርጋቸው ነው፣ ግንቦት ሰባት፣ መሳይ፣ ወዘተ እያሉ ሰበቦችን ከመደርደር ራሱን እስክንድርንም አማራ አይደለም፣ እጁም አማራ አይመስልም እያሉ ከማለቃቀስ በተጨባጭ የአማራው የሕልውና ትግል ሲባል ምን ማለት ነው? ትግሉ እየተካሄደ ያለውስ በትክክል የአማራ ሕልውናን ለማስከበር በተቀየሰ የትግል ስትራቴጅና ታክቲክ ላይ ተመሥርቶ ነወይ? ወዘተ… የመሳሰሉትን ጥያቄዎች እያነሱ አደብ ገዝቶ መነጋገር ያስፈልጋል። በፉከራና በስሜት የሚገኝ ነፃነት የለም። ይህ አካሄድ እርምት ሳይደረግበት በስሜትና በፉከራ መነዳቱ ከቀጠለ አትራፊው አሁንም አገዛዙ ነው። እንዲያውም ማሾፍ ጀምሯል። የጠላቶቹ አካሄድ እርስ በእርስ ገመድ ጉተታ ላይ ተመሥርቶ እየተጠላለፉ የሚገኙ ከሆነ ሊያሾፍም ይገባዋል።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የአማራ ብሔር ተወላጅ እና ለሀገሩም እንደሚቆረቆር ሀገር-ወዳድ ዜጋ ለእኔ የአማራ “የሕልውና ትግል” ባጭሩ የሚገባኝ በትናንቱ ዘመንም ሆነ በአሁናዊው የኢትዮጵያ ፓለቲካ ቅኝት አማራው፣ ሳይሳደድ፣ ሳይፈናቀል፣ ሳይገደል፣ ብቻ በተፈበረከ የፈጠራ ትርክት በሁሉም ዓይነቶች የጠላትነት መግለጫ መንገዶች ተፈርጆ “ነፍጠኛ” የሚል ታርጋ ተለጥፎበት ከመኖር ወደ አለመኖር እንዲወርድ ስለተደረገ አይ! ይህ ግፍስ በቃኝ ብሎ፣ በሀገሩ ተፈጥሯዊ የመኖር መብቱን አስከብሮ ለመኖር መነሳቱን ማንም ይገነዘበዋል። ነፍጥ ከማንሳቱም አስቀድሞ ተው፣ አትግደሉን፣ አታሳዱን ወደ ጋራ ሀገራችን ዋና ከተማም እንድንገባ አታግዱን …እያለ ድምጹን ቢያሰማም ሰሚ ጆሮ አላገኘም። ኢትዮጵያዊነቱን አስበልጦ ለብዙ ዓመታት ለሞቱት ነፍስ ይማር እያለ፣ ሻማ እያበራ፣ የኅሊና ጸሎት እያደረገ በተማፅኖ ሕይወቱን ቢገፋም ሁኔታዎች እየተባባሱ መጡ እንጅ መሻሻል አልታየባቸውም። ከዚያ እየሆነ ያለውን ሁላችንም እያየን ነው ስለሆነ ዝርዝሩ አስፈላጊ አይሆንም።

የአገዛዙ የፓለቲካ በትር በአማራው ላይ ማነጣጠሩ ቢበራትም ሌሎች ብሔር-ብሔረሰቦችም ኦሮሞውን ጨምሮ ተመችቷቸዋል ማለት አይደለም። የሕልውና ትግሉ የአገዛዙ ጥቃት እየደረሰባቸው የሚገኙትን ሁሉ ከጎኑ ከማሳለፍ ይልቅ “አባቶቻችን መንግሥት ልንገባ ነው!” ወዘተ እየተባለ ጭራሽ ቤተ-መንግሥትንም የግል አፅመ-ርስት ያስመሰለ ፕሮፓጋንዳ እየተረጨ ጠላት ማብዛት ተጀመረ። ፓለቲካው የሚመራው በስሜት ነው። ከስህተትና ከችግር ትምሕርት በማግኘት ትግሉ ወደ ተሻለ ደረጃ ይሸጋገራል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ብሶበት በሁለት ግለሰቦች ሰብዕና ዙሪያ ወደ ማጠንጠን ተሸጋግሮ አረፈ። አንድን ሰው “ታላቁ” እስክንድር እያሉ ከፍተኛ ማማይ ላይ ሲሰቅሉ ኖሮ፣ ከነ ችግሩ በምርጫ ማግሥት “እጁም አማራ አይመስልም፣ አማራም አይደለም፣ ሙ0ስቱም ትግሬ ናት፣ ኦሮሞ ነው … ወዘተ እያሉ በሰውዬው ሰብዕና ላይ ሳይቀር መዝመት በሽተኛ መሆን እንጅ የጤነኛ ሰው መሆን ምልክት አይደለም። በመርህ የሚመራ፣ ዓላማና ግብ ያለው ድርጅት ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ እስክንድርም ሆነ ዘመነ የመወያያ አጀንዳ መሆን አልነበረባቸውም።

በአንድ ወቅት አንድ ስብሰባ ላይ አሁን ዝምባብዌ ያሉት ሰው “………ጓዶች! ያለችው አንድ ወንበር ነች፣ እሷንም እኔ ተቀምጬባታለሁ…” ብለው መናገራቸውን በቀጥታ ተላልፎ በነበረ የቲቪ መስኮት በጆሯችን አዳምጠናል። ሥልጣን ቤተ-መንግሥትም፣ ጫካም ላይ እያፋጀ ነው። ዴሞክራሲ ሁሉም ቦታ ላይ አደጋ ላይ ነው። ቃሉን እንደ ውዳሴ ማርያም እንደግመዋለን እንጅ በተግባር ለመተርጎም ግን ሁሉም አይፈልግም። ማንም ዝግጁ አይደለም።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ግን የሚታገሉት ኃይል በእነሱ መከፋፈል ከፍተኛ የፓለቲካ ትርፍ እንዲያጋብስ እያደረጉት ናቸው። አሁንም አልመሸምና ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። እስኪ ከመጨረሴ በፊት አሁን ባለው ትርምስ ከመንግሥት ጋር ለመደራደር ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተው ፋኖ ተደራዳሪዎችህን አቅርብ ቢባል እንኳ በእነማን የሚመራው ፋኖ ነው የአማራን የሕልውና ትግል ወክሎ መቅረብ የሚችለው አካል? ወደ ታንዛንያ-አሩሻ ወይም ወደ ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ አማራን ወክሎ ማን ይሂድ? ይህን ድክመት የተገነዘቡት ጠቅላዩ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ባሕርዳር ላይ ተገንተው ባሰሙት ንግግር “የምን ቴዎድሮስ ነው! አማራ እንደ አረጋ ከበደ ያለ መሪ አግኝቷል፣ ችግራችሁን ተነጋግራችሁ ፍቱ…” ሲሉ ተመጻድቀዋል።

ስለዚህ መሳለቂያም-መመጻደቂያም ከመሆን በስሜት መነዳት ይቁም። ፓለቲካው የጨረባ ተስካር አይሁን። ከእንቅልፍ እንደተነሳን ፊታችንን እንኳ በአግባቡ ሳንታጠብ በቲክቶክና በዩቱብ መስኮት ብቅ እያልን አፋችን እንዳመጣልን ከመትፋት እንቆጠብ። ይህን ማድረግ ለአማራውም፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝባችንም ምንም አይጠቅመውም። አንዳንድ ጊዜ ትንፋሽ እየሳቡ፣ ጊዜ የሚፈታቸውም እንቆቅልሾች መኖራቸውን በመገንዘብ የጽሞና ወቅትም ያስፈልጋል።

Hohetebirhan Getu
Germany

 

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.