ዘረኛ ዝማሬን አንዘምርም! ገለታው ዘለቀ
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የኦሮምያ የብሄር መዝሙር አዲስ አበባ ውስጥ ቢዘመር ቅር አይበላችሁ፣ ይልቁን ሊበረታታ ይገባል የሚል ነገር ሲናገሩ እኒህ ሰው ከዚህ ከብሄር ፖለቲካና ከዘር መዝሙር የማይላቀቁ ሰው እንደሆኑ በግልጽ ያሳያል። እነዚያ ህጻናት የዘር መዝሙር በመዲናችን አንዘምርም በማለታቸው ከእኚህ መሪ በእጅጉ የተሻሉ ሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል።
በመሰረቱ በመላው አለም ውስጥ የዘር ወይም የብሄር መዝሙር የሚባል የለም። የነጮች ብሄራዊ መዝሙር፣ የጥቁሮች ብሄራዊ መዝሙር፣ የስፓኒሾች ብሄራዊ መዝሙር የሚባል ነገር የለም። አለም የዘር ዝማሬዎችን ታወግዛለች። አዲስ ኣበባ ውስጥ አማራው፣ ትግሬው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣ ሁሉም ዜጋ ተከባብሮ ነው የሚኖረው። ለዚህ ህዝብ መቀባበልንና መከባበርን የሚሰብከው የለም። ትልቁ ችግር ያለው ከነ ዶክተር አብይ አካባቢ ነው። የዘር መዝሙር ደርሰው፣ ሁሉም በየብሄሩ መዝሙር አውጥቶ ስለ ጋራው ቤታችን የሚያስብ እንዲጠፋ ያደረጉት የብሄሩ ለሂቃን ናቸው።
ዶክተር አብይ አዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሚያ መዝሙር ይዘመር ቅር አይበላችሁ ያሉትን መዝሙር ከታች ተመልከቱት። ይህ መዝሙር አንዲት ቦታ የኢትዮጵያ ስም አልተጠቀሰበትም። ኢትዮጵያን ስሟን አያነሳም። ህብረትን አንድነትን፣ ፍቅርን፣ መከባበርን የማያሳይ መዝሙር ነው። የዚህ መዝሙር ደራሲም ራሳቸው ናቸው። የኦሮሞ ህዝብ መዝሙር አይደለም። ታዲያ ይህንን መዝሙር አንዘምርም ቢሉ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ከቶ ምን አጠፉ?…….
በነገራችን ላይ አዲስ አበቤው የዘር መዝሙር የተባለን ነገር ነፍሱ ትጸየፋለች። ነገ የአማራ ክልል መዝሙር በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ይዘመር ቢባል ተማሪዎች የዘር መዝሙር አንዘምርም ማለታቸውን ይቀጥላሉ። የዚህ ህዝብ ጥያቄ እኮ መዝሙራችን ይለወጥ ህብረትን አንድነትን ኢትዮጵያን በመዝሙራችን ውስጥ እንክተት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ቢዘመር የሚጠላ ማን አለ። ከተቻለ አንድ ኢትዮጵያዊ ሁሉንም የሃገሩን ቋንቋዎች ቢያውቅ ደስተኛ ነበር።
ዋናው ጉዳይ ህዝቡ ነፍሱ የጠላው ነገር የዚህን የብሄርና የዘር ዝማሬ ነው። ዶክተር አብይ ገና ዘፈናቸውን አልለወጡም። ዛሬም የብሄርና የዘር መዝሙር ይዘምራሉ። ህዝቡ ግን የዘር ዝማሬን አንዘምርም እያለ ነው። የዘር መዝሙር እንኳን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በራሱ በብሄሩ ውስጥም መዘመር የለበትም። መዝሙሮቻችን ሃገራችንን ኢትዮጵያን የረሳና ብሄርተኝነትን የሚያጎላ መሆን የለበትም። ፍቅርን አብሮነትን ማካፈልን የሚያራምድ መሆን አለበት።
ዶክተር አብይ ስለ አንዳንድ ሃገራትን መዝሙሮች ጠቅሰዋል። ተሳስተዋል። ሁሉም የአለም ህዝብ ዝማሬው አብሮነት እንጂ የዘር ዘፈን የሚያዜም የለም። ከፍ ሲል እንዳልኩት አዲስ አበባ የተጣላው ከዘረኛ ዝማሬ ጋር እንጂ ስለ ህብረትና አንድነት የሚዘመር መዝሙርን ከነፍሱ እየተደሰተ ይዘምራል። የሃገሬ ልጅ በየትኛውም ቋንቋ ይሁን ግድ የለውም አብሮነትንና ኢትዮጵያዊነትን በደስታ ይወድሳል። ስለዚህ ዶክተር አብይ የአዲስ አበባን ተማሪዎች ዘረኛ ዝማሬ ካልዘመራችሁ የሚለውን ሰበካ ያቁም። መዝሙሩ በትግርኛ ይሁን፣ በአማርኛ፣ ወይም በኦሮምኛ የዘርና የክልል መዝሙር በመዲናችን ብቻ ሳይሆን በምድራችን መዘመር የለበትም። ነውር ነው። በአውነት ነውር ነው። እኔ የራሴን ብሄር መዝሙር ደርሼ ሌላውን ብሄር ለእኔ ዘምርልኝ ማለት በጣም ቀፋፊ ነገር ነው።
በአጠቃላይ ይህ ጉዳይ የሚያሳየው ነገር ዶክተር አብይ ከዚህ ከብሄር ዝማሬ ያልወጡ ግራ ተጋብተው ግራ ያጋቡ መሪ መሆናቸውን ነው። ሃገራችን በተራበችው ለውጥ ልክ የሚራመድ መሪ ያስፈልገናል። ወደ ሽግግር እንለፍ የምንለው ለዚህ ነው። አሁንም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ የዘርና የብሄር ብሄራዊ መዝሙር እናቁም። ባህልና ቋንቋ ይከበር፣ ነገር ግን ኢትዮጵያን የረሳና የብሄር ስም የተለጠፈበትን ብሄራዊ መዝሙር እንለውጥ። መዝሙሮቻችን ወንድማማችነትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ህብረትን የሚያጠናክሩ ይሁኑ።
ለትዝብት ይሆን ዘንድ የኦሮምያን መዝሙር ከታች አያይዤዋለሁ። ለትምህርት ይሆን ዘንድ የካናዳንና የአውስትሬሊያን መዝሙር አያይዤላችሁዋለሁ። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ ይጠብቅ።