Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ !

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰጠ መግለጫ !

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን ከሚታገልላቸውና ትግሉ የሚጠይቀውን መስዕዋትነት ሁሉ ለመክፈል ከዝግጁም በላይ ከሆነባቸው የአማራ ሕዝብ የኅልውና ጥያቄዎች ውስጥ የመጀመሪያው የአማራን ሕዝብና ግዛት አንድነትና ኢተነጣጣይነት ተፈጥሯዊ መብቱን ማስከበር ነው። አማራ ጠል ኃይሎች ወደ ትግል ሲገቡ ጀምረው የአማራውን ሕዝብ በጠላትነት ፈርጀው የተነሱ፥ ይህንን የአማራ ጥላቻቸውን በትግል ሰነዳቸው ሳይቀር አካተው ሲታገሉ ኖረው በለስ ቀንቷቸው አገራዊ ሥልጣን ሲቆናጠጡ፥ አስቀድሞ የነበራቸውን የአማራ ጥላቻ መንግስታዊና ተቋማዊ ቅርፅ በመስጠት ሥርዓትና ሥሪት እንዲሆን አድርገዋል። አማራ ጠል ብሔርተኛ የፖለቲካ ኃይሎች አማራውን በነጠለና ባገለለ መልኩ፥ የአማራ ሕዝብ እንደሕዝብ ሳይሳተፍ፣ ሳይፈቅድና ይሁንታውንም ሳይሰጥ፤ ለበርካታ ሺህ ዓመታት የኖረባቸው ታሪካዊ ርስቶቹ በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች እንዲካለሉ ተደርጓል። የአማራ ታሪካዊ ርስቶች ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች ከተካለሉ በኋላም ልዩ ልዩ የሰፈራ ፕሮግራሞችን በመንደፍ ዴሞግራፊያዊ አለመመጣጠን እንዲፈጠር በማድረግ ነባር አማራዋችን የመዋጥ እና መሰልቀጥ ሁኔታዎች ከመኖራቸውም በላይ የየግዛቶች ታሪካዊ ባለቤት የሆኑትን አማራዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ቁጥራቸውን በመቀነስ የዘር ማሳሳት፣ ያለፈቃዳቸውና በተፅዕኖ ወደ ተካለሉባቸው አስተዳደሮች ማንነታቸውን የማስቀየር የማንነት ገፈፋ፣ የማንነት መገለጫዎቻቸውን እንዳያዳብሩና እንዳይጠቀሙ አፈናና ጫና በማሳደር የማንነት ቅየራ፣ አፋኝ ቢሮክራሲ በመፍጠር ተማረው እንዲሳደዱ ማድረግ፣ ማንነታችን ይከበርልን ጥያቄ ለምን አነሳችሁ የሚል ጅምላ እስር፣ ድብደባ፣ ዘር ማጥራት፣ በአማራነታቸው የማሸማቀቅና የመነጠል ኢሰብአዊ ድርጊቶች ተፈፅሞባቸዋል፤ አሁንም ድረስ ቀጥሏል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በወልቃይት፣ ራያና መተከል ታሪካዊ ርስቶችና በእነዚህ ርስቶች በሚኖሩ አማራ ወገኖች ላለፉት 27 ዓመታት የታየው ዘር ማጥፋትና ፍጅት መቆም አለበት ብሎ ያምናል። መፍትሔውም በፖለቲካ ውሳኔ የተወሰዱ የአማራ ርስቶችና አማራ ወገኖች ወደ ነባራዊ የአማራ አስተዳደር በተወሰዱበት አግባብ በፖለቲካ ውሳኔ መመለስ ብቻ መሆኑን በአንክሮ ይገነዘባል። ከዚህ በተቃራኒ ትናንት ጥቅምት 23/2011 ዓ/ም የኢፌዴሪ መንግስት ከወሰንና ማንነት ጋር ተያያዥ ጥያቄዎችን ለመመለስ ገለልተኛ አጥኚ ኮሚቴ ማቋቋሙን በፌዴሬሽን ምክርቤት በኩል ይፋ አድርጓል። አብን የኢፌዴሪ መንግስትን አካሄድ አምርሮ ያወግዛል። ከማውገዝም ባለፈ መላውን የአማራ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ በማነቃነቅ በጽናት የሚታገለው መሆኑንም ይገልፃል። 

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን የኢፌዴሪ መንግስት ከወሰንና ማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በገለልተኛ አጥኚ ኮሚቴ ለመፍታት ያስቀመጠውን አቅጣጫ የሚቃወምባቸው ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።
1) የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ርስቶች ባለቤት የአማራ ሕዝብ ነው። ይህ ኃቅ ተገርስሶ የአማራ ሕዝብ ሳይጠየቅ፣ ሳይሳተፍና ይሁንታውንም ሳይሰጥ በኃይልና በፖለቲካ ውሳኔ ወልቃይት፣ ራያና መተከልን ጨምሮ የተለያዩ የአማራ ሕዝብ ርስቶች ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች ተካለዋል። የተወሰዱ ርስቶች በኃይልና በፖለቲካ ውሳኔ የተደረጉ እንጂ በሕግና ኮሚቴ በማዋቀር በጥናት ስላልሆነ የተወሰዱ ርስቶችና ወገኖቻችን በተመሳሳይ መልኩ በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ነባራዊ የአማራ አስተዳደር እንዲመለሱ ከማድረግ ውጭ ያለውን አካሄድ ሁሉ አብንም ሆነ መላው የአማራ ሕዝብ አይቀበለውም።

2) የፌዴሬሽን ምክርቤት የተቋቋመው ጥያቄ የሚቀርብባቸው የአማራ ርስቶችና ወገኖች በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች ከተካለሉ በኋላ ነው። ይኸው መንግስታዊ ተቋም ለበዳይ ወገን ባደላ መልኩ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ሲያቀርቡ በነበሩ ወገኖች መከራና ሲቃይ ሲያላግጥ የኖረ ነው። ይባስ ብሎም ፌዴሬሽኑን በአፈጉባዔነት የሚመሩት ግለሰብ ሕገወጡን የአማራ ርስቶች ቅርምትና በአማራ ወገኖች ላይ የደረሰውን የዘር ማጥፋት በጠንሳሽነት ያስፈፀመው ሕወኃት የሥራ አስፈፃሚ አባል በመሆናቸውና በቅርቡም ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ ለአንድ ወገን ባደላ መልኩ «ራያም ሆነ ወልቃይት መሬቱም ሆነ ሕዝቡ የትግራይ ነው» የሚል መግለጫ የሰጡ በመሆናቸው፥ በተለይ ከዚህ ጋር የተያያዙ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን በገለልተኝነት ይመራሉ ብለን አናምንም። ስለሆነም ከሕገመንግስት መጽደቅና መሰል ጥያቄዎችን ለመፍታትም መንግስታዊ ተቋም ከመደራጀቱ በፊት የፖለቲካ ውሳኔ ተወስኖ በኃይል ወደ ተለያዩ የአስተዳደር ክልሎች የተካለሉ አማራ ወገኖቻችንም ሆኑ ርስቶቻችን በኮሚቴ ይመለሳሉ ብለን ስለማናምን የመንግስትን ውሳኔ አንቀበለውም።

3) የኢፌዴሪ መንግስት አማራው የሕዝብና ግዛት አንድነትና ኢተነጣጣይነት ተፈጥሯዊ መብቱ እንዲከበርለት ያነሳውን የኅልውና ጥያቄ ለመፍታት ዳተኝነት ከማሳየቱም በላይ ጉዳዩን እልባት ለመስጠት እየሄደበት ያለው መንገድ ለጨቋኝና ጭቆና ውግንና የመቆም ያህል ነው። መንግስት የወልቃይት፣ ራያና መተከል ጉዳይ የመላው የአማራ ሕዝብ ጉዳይ መሆኑን ሆነ ብሎ በመርሳት በገለልተኛ አጥኚ ኮሚቴ ሽፋን ዛሬም የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን የአማራ ሕዝብ ባላሳተፈና ባገለለ መልኩ እያደረገ ያለው አካሄድ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም። አብን ለዚህን ዓይነት መንግስታዊ አካሄድ ፈፅሞ እውቅና አይሰጥም። የተሳሳተውን የመንግስት አካሄድም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን አምርረን በጽናት የምንታገለው ይሆናል። የመንግስት አካሄድ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን የአማራ ሕዝብ ያገለለ ስለሆነ አንቀበለውም።

በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት እየሄደበት ያለው መንገድ ከአገራዊ አንድነትና የሕዝብ ለሕዝብ መተማመን ይልቅ አገርን የሚያፈርስና ጥርጣሬን የሚያነግስ፣ ላንድ ወገን ያደላና አማራውን ነጣይነ አግላይ በመሆኑ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን እንደማይቀበለው ያሳውቃል። ንቅናቄያችን የአማራ ሕዝብ የሕዝብና ግዛት አንድነትና ኢተነጣጣይነት ተፈጥሯዊ መብቱን ለማስከበር ባለፉት 27 ዓመታት ካደረገው ትግል የከፋና መራር ትግልም ከፊቱ እንደተደቀነ ይገነዘባል። ስለሆነም ሁሉም አማራ የኅልውና አደጋውን ለመቀልበስና የአማራን ሕዝብ ኅልውና ለማስቀጠል ትግሉን በባለቤትነት ጭምር ይዞ እንዲመራ ከአብን ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል!

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን

ጥቅምት 24/2011 ዓ/ም 

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.