Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ –አብን ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ::

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ –አብን ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ::

ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ –አብን ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ
***
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ –አብን መላው የአማራ ሕዝብ ከተደቀነበት የኅልውና ስጋት ተላቆ በወርዱና በቁመናው ልክ ፍትኃዊ ድርሻውን ፤ ዘላቂ መብትና ጥቅሙን እንዲያስከብር የተደራጀ ትግል ለማድረግ ዓላማው አድርጎ የተመሰረተ አማራዊ አደረጃጀት ነው፡፡

አብን ከተመሰረተበት ከሰኔ 3/2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የአማራ ሕዝብን ትግል ወደፊት የሚያራምዱ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከል በበርካታ ቦታዎች የአማራን ሕዝብ የማንቃት እና የማደራጀት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች ሕዝባዊ ውይይቶችን እና የአደባባይ ስብሰባዎችን አከናውኗል፡፡
ከአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ካሉ ድርጅቶች ጋር ለመስራት በጎ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ አማራዎችን በማንቃትና በማደራጀት ትግሉን ለመደገፍ የበኩላቸውን ን ሚና እንዲወጡ ጥረቶች ተደርገዋል፤ በመደረግም ላይ ናቸው፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን ብሔራዊ ምክር ቤት ንቅናቄው ካሉት 3 ዋና ዋና ሥልጣን ተቋማት አንዱ ሲሆን ተቀዳሚ ተግባሩም የንቅናቄውን የሕግ አውጭነት ሚና በመያዝ ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ በማስቀመጥ እንዲሁም የሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የበጀት እና ዕቅድ አፈፃፀም ክንውን መገምገም እና ማፅደቅ ነው፡፡

በዚህ ስልጣኑ አግባብ ከጥቅምት 3/2011 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 4/2011 ዓ.ም ድረስ ሁለተኛውን መደበኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ጉባኤው፡-

ሀ) የሥራ አስፈፃሚውን የ4 ወራት የሥራ ክንውን ሪፖርት በማድመጥ ተወያይቶና ገምግሞ አፅድቋል።

ለ) የንቅናቄውን ያለፉትን የ4 ወራት የፋይናንስ ሪፖርት በማድመጥ ተወያይቶና ገምግሞ አፅድቋል።

ሐ) የ2011 በጀትና ዕቅድ ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ አፅድቋል፡፡

መ) የንቅናቄውን የውስጥ ተቋማት ግንኙነትና መዋቅራዊ አሰራር በተመለከተ በዝርዝር ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪ በወቅታዊ አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በዝርዝርና በጥልቅ በመወያየት ጉባዔው አቋም ይዟል፡፡ ጉባዔው አፅዕኖት ሰጥቶ ከገመገማቸውና ተወያይቶ አቋም ከያዘባቸው አገራዊና አካባቢያዊ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡-

ሀ) የአዲስ አበባ ወጣቶች በህገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች መጋዝ፣

ለ) የራያ አማራ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ትምህርት የመማር ጉዳይ፣

ሐ) በማንነታቸው ምክንያት ከወልቃይት (ከርስታቸው) የተፈናቀሉ አማሮች ጉዳይ

መ) በጣና ኃይቅ እና በላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሕንፃዎች ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች በተመለከተ እንዲሁም

ሠ) ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጋር ተያይዞ የተጋረጠውን የፀጥታና ደኅንነት እጦት በነዋሪዎች ላይ የደቀነውን ስጋት በተመለከተ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በዝርዝር ተወያይቷል።

በመሆኑም ከላይ በተመለከቱት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመመርኮዝ የአብን ብሔራዊ ምክር ቤት የሚከተሉትን አቋሞች ይዟል:-

1) የአዲስ አበባን ወጣቶች በሕገወጥ መልኩ መታሰርና ግዞት በሚመስል መልኩ ወደ እስር ቤቶች እና ማሰልጠኛ ካምፖች መጋዝን ብሔራዊ ምክር ቤቱ በፅኑ ያወግዛል፡፡ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ/ውሳኔና የሕግ ሥርዓት (Due process of Law) የትኛውም የፖሊስ ተቋም ዜጎችን ያለፍላጎታቸው በግዞት መልኩ ወደ ሥልጠና ካምፖች በማስገደድ ማስገባት አይቻልም፡፡ ይህ ድርጊት በኢትዮጵያም ሆነ አገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለማቀፍ ስምምነቶችና ሕግጋቶች የማይደገፍ ሕገወጥ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባ ፖሊስ በግዞት መልክ ያሰራቸውን ዜጎች በፍጥነት እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡ የፌዴራል መንግስትም ይህንን ሕገወጥ ድርጊት በመኮነን ዜጎች ነፃነታቸውን እንዲያገኙ በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡

2) ያለሕዝብ ፍላጎት ከወሎ አማራ ግዛት ተቆርሶ ወደ ትግራይ ክልል በተጠቃለለው የራያ አማራ ግዛት የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የዜጎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ፍላጎት እና መብት በመገደብ የሚያደርገውን ሕገወጥ ድርጊት እናወግዛለን፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ አገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለማቀፍ ስምምነቶችና ሕግጋት ሕፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር ሙሉ መብት እንዳላቸው በግልፅ ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ የራያ አማራ ተማሪዎች ተገደው ያለፍላጎታቸው በትግርኛ ቋንቋ እንዲማሩ የትግራይ ክልል መንግስት የሚያደርገውን ያልተገባ ድርጊት በፍጥነት እንዲያቆም እንጠይቃለን፡፡ ፌዴራል መንግስቱም ጣልቃ በመግባት በራያ አማራዎች ላይ የሚደርሰውን በደልና ግፍ በፍጥነት እንዲያስቆም እንጠይቃለን፡፡

3) በማንነታቸው ምክንያት አማሮች ከገዛ ርስታቸው ከወልቃይትና ጠገዴ በትግራይ ክልላዊ መንግስት ባለሥልጣናት ግፊት በሕገወጥ መንገድ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ –አብን ብሔራዊ ምክር ቤት ይህንን ድርጊት በፅኑ ያወግዛል፡፡ በአስቸኳይ እንዲቆምም ይጠይቃል፡፡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡ የፌዴራል መንግስቱና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት አማሮች ከገዛ ርስታቸው የሚፈናቀሉበት ሕገወጥ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

4) በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እና በጣና ኃይቅ ኃብቶቻችን ላይ እየደረሱ ያሉ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ውድመቶች በእጅጉ ያሳስበናል፡፡ የፌዴራሉ መንግስትና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ በመውሰድ ኃብቶቻችንን እንዲታደጉ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

5) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከሰሞኑ በተፈጠረው የሰላም እና ፀጥታ መደፍረስ የተነሳ ዜጎቻችን ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ–አብን ብሔራዊ ምክር ቤት የፌዴራል መንግስቱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልል መንግስታት በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ እና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ የተለመደውን በሰላም የመኖር መብታቸውን እንዲያስከብሩ በጥብቅ ይጠይቃል፡፡

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ኝቅናቄ–አብን ብሔራዊ ምክርቤት

ጥቅምት 4/2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ፥ሸዋ፣ኢትዮጵያ

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.