Breaking News
Home / Amharic / ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የተሰጠ መግለጫ!

ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የተሰጠ መግለጫ!

ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ) የተሰጠ መግለጫ!

እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እጅግ አደገኛ ምስቅልቅል ውስጥ ትገኛለች፤ እንደ ህዝብ አማራ የእልቂት አዋጅ ታውጆበት ራሱን ከፈጽሞ ጥፋት ለማዳን በእያንዳንዷ ሰከንድ በእልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ውስጥ ነው። በዚህ ምክንያት ወቅቱን በዋጀ የጠላትን እንቅስቃሴ በሚመጥን አኳኋን፣ ጠላትን ለመመከትና ለመደምሰስ ህዝባዊ ትግል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአማራ ህዝባዊ ሃይልን ፈጥረን ላለፉት ሶስት ወራት በሞት ጫካ ውስጥ እየተሽሎከሎክን ህዝቡን ስናነቃ፣ ስናደራጅና ስናሰለጥን ቆይተናል። በአጭር ጊዜም ሽዎችን ማንቃት ማደራጀትና ማሰልጠን ተችሏል። 

በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ እያለን የሰሞኑን መንግስት የክተት ጥሪ ተከትሎ ለውጊያ ቅድመ-ዝግጅት እንዲያግዘን የመርጡለማርያም ግብርና ኮሌጅን እንደ ጊዚያዊ መሰባሰቢያ ካምፕ እንድንጠቀም ተነገረን። ከዚህም በተጨማሪ የመንግስት ሰራተኛ አባሎቻችንን ጭምር ማዝመት እንደምንችል እና ደሞዛቸው ለቤተሰብ እንደሚደርስ፣ የቡድን መሳሪያና ተተኳሽ በበቂ እንደሚቀርብልን፣ ምግብ በአንድ ትልቅ ተቋም በኩል እንደሚቀርብ… ወዘተ ተስማማን።

በኛም በኩል የመንግስትን ውሳኔ አድንቀን መላው የአማራ ሕዝባዊ ኃይል አባላት (ፋኖ) ወደ ጊዜያዊ ካምፑ እንዲከት ጥሪ አስተላለፍን፤ በሰባ ሁለት ሰአት ውስጥ አንድ ሽህ አንድ መቶ አስራ ስምንት (1118) የሰለጠነ ፋኖ ወደ ካምፕ ከተተ። ከዚህ ውስጥ ከ ሰላሳ በላይ የኮማንዶ አሰልጣኞች፣ ከአስራ አምስት በላይ ሃኪሞች፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና መሪዎች የነበሩ፣ የልዩ ሃይል መሪዎችና አባላት የነበሩ የሚገኙበት ሲሆን ብዙ ሺወች ከየቀያቸው ተነቃንቀው ህዝባዊ ሃይሉን ለመቀላቀል መጠራራት ጀመሩ። 

ይሁንና ሰባ ሁለት ሰአቱ በቅጡ ሳይጠናቀቅ የመንግስት የተለመደ አመል ማገርሸት ጀመረ። ምግብ ያቀርባል የተባለው ተቋም አንድ ረፋድ ላይ ደረቅ እንጀራ፣ ሽሮና በርበሬ አድርሶ ጠፋ፤ ካምፑን ለቀን እንድንሄድ እዚህም እዚያም ጫናዎች መታየት ጀመሩ፤ “ደመወዛቸው አይቋረጥም ችግር የለም ይዝመቱ” የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ አባሎቻችን ላይ ባልተለመደ ሁኔታ ላንድ ቀን እንኳን ካምፑ ውስጥ ውለው ሳያድሩ መስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ እንዲጽፍ ማድረግ ተጀመረ፤ ፋኖዎች ከአካባቢያቸው እንዳይንቀሳቀሱ መኪና መከልከልና ማስከልከል ተጀመረ፤ “ከሰላሳ እስከ አምሳ ሰው ብቻ ነው ማዝመት የምትችሉት ከዛ ውጭ አትችሉም” ይሉን ገቡ፤ “በመከላከያ እዝ ስር ከተው ሊያስጨርሷችሁ ነው ተመለሱና ልዩ ሃይሉንና መከላከያን ብቻ ተቀላቀላችሁ ሰልጥኑ”…ወዘተ የሚሉ የውስጥ ለውስጥ ቅስቀሳዎች ጦፉ። 

ከጉዟችን ላለመናጠብ ሲባል ብቻ ችግሮችን ባላየ እያለፍን በትዕግስት ይዘን ትኩረታችንን ዋናው ጠላት ላይ ለማድረግ አቅደን ፋኖውን ለቀጣይ ግዳጅ ማዘጋጀቱ ላይ ብቻ አተኩረን ነበር። ይህ ትዕግስት ግን የረባ ውጤት ሳያመጣ የተገባልን ቃል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ከመታጠፉ በተጨማሪ ሰኞ እኩለ ቀን የገባንበትን ካምፕ ረቡዕ እለት ለቀነው እንድንወጣ፤ ኃይላችንም እንድንበተን ግፊት መደረግ ተጀመረ። አልፎም “ሁኔታዎች እየተካረሩ ከሄዱ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደምንገባ” ‘ይመክሩን’ ገቡ። 

በእኛ በኩልም መንግስት በገባው ቃል መሰረት ተገቢዉን ይፈፅማል በሚል እምነት ወደ አንድ ካምፕ የተሰባሰበ በርካታ የአማራ ፋኖ ህይወት አደጋ ውስጥ ላለመጣል እና የውስጥ ችግር ላለመፍጠር ስንል ከህዝባዊ ኃይሉ አባላት ጋር መክረን የህዝባዊ ኃይሉን ህልውናና ቀጣይ እንቅስቃሴ በማይነካ አኳኋን ፋኖው ወደ ቀየው ተመልሶ ከነ ሙሉ መዋቅሩ ትግሉን እንዲቀጥል አቅጣጫ በማስቀመጥ ከካምፕ ወጥተን በቁጭት እምባ እየታጠብን ወደየቀያችን ተመልሰናል። ፍርዱን ለአማራ ህዝብ፣ ለኢትዮጲያ ህዝብ እና ለታሪክ ትተነዋል። 

 

በመሆኑም:-

1/ አባሎቻችን ቀጣይ ተልዕኮ እስኪሰጥ ድረስ በየመጣችሁበት ወረዳ ተመልሳችሁ ህዝብ የማንቃት እና የማደራጀት ስራችሁን እንድትቀጥሉ እናሳስባለን።

 

2/ የመንግስት አመራሮች ቃላችሁን ለማክበር ፈቃዱ ካላችሁ እኛም ማንኛውንም ስምሪት ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በህዝብ ፊት ቃል እንገባለን።

3/ መላው የአማራ ህዝብ እና የገባንበት የህልውና አደጋ ያሳሰባችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ህዝባዊ ኃይሉ ለትግል ዝግጁ መሆኑን አውቃችሁ እንድትደግፉት እና በየሚመቻችሁ አደረጃጀት ትግሉ ላይ አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪ እናስተላልፋለን።

 

4/ ጥሪያችንን ባለመቀበል፤ አንድም የአማራ ጉልበት እንዳይባክን አበክረን የገለፅነውን ወርቃማ ሃሳብ በመግፋት ለሚደርሰው ታሪካዊ ኪሳራ ገዥወች ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ እናሳውቃለን።

 

 No 

 አማራ ሕዝባዊ ኃይል (ፋኖ)

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.