“የተፈፀመብን በደልና ህገ ወጥ ተግባር ይታወቅልን!” እነ ክርስቲያን ታደለ
“ክርስቲያን ታደለ፣ በለጠ ካሳ እና ሌሎች አብረዋቸው በእስር የሚገኙት ህዳር 17 ለ18/2012 ከሌሊቱ 10:30 በአንድ ሻለቃ የፌደራል ፖሊስና አንድ ሻለቃ አድማ በታኝ በመጠቀም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሬት ለመሬት በመጎተትና ድብደባ በመፈፀም ወደ ቂሊንጦ እስር ቤት ያወረዷቸው ሲሆን፣ በየትኛውም ጊዜ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚችልም ዛቻ ደርሶባቸዋል። በድባደባውም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን እስካሁንም ምንም አይነት ህክምና አላገኙም። በተለይ በፈንታሁን ሞላ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
ይህን ህገወጥና ኢሰባዊ እርምጃ የተቃወመ የአንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል (ሙሉቀን ወንድምነህ) የታሰረ ሲሆን፣ በሽብር ተጠርጥረሃል ተብሎ ሰሜን ማዘጋጃ ላዛሪስት ት/ት ቤት ፊትለፊት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ መሆኑ ተረጋግጧል።
እነ ክርስቲያን እና በለጠ ካሳ ቂልንጦ ዞን 4 ማግለያ ወይንም ሳጥን ቤት በመባል በሚታወቀውና ጣራውም ግድግዳውም ኮንክሪት በሆነ ክፍል ውስጥ የታሰሩ ሲሆን የሽንት ቤቱ ሽታና ፍሳሽ ወደ ማግለያ ክፍሉ የሚገባ በመሆኑም ለጤና ጉዳት ተጋልጠዋል።የታሳሪዎቹ ንብረቶች በፖሊስ እጅ ናቸው። ለምሳሌ የክርስቲያን ታደለ መነፅር፣ እንዲሁም የሌሎችን ታሳሪዎችም የተለያዬ አልባሳትና እቃወች ተወስደውባቸዋል። ለታሳሪዎችም ምንም ዓይነት የህትመት ውጤቶች ሊገቡላቸው እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል።
ወደ ቂሊንጦ ሲገቡም የተጠረጠሩበት የወንጀል አይነት “ሽብር” በሚል ካርድ ተሰጥቷቸዋል። መ/አ መሳፍንት ጥጋቡም አብሯቸው ታስሮ ይገኛል።”
(የመረጃው ምንጮች ቤተሰቦቻቸው ናቸው)