Breaking News
Home / Amharic / ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ስላለው ጥቅምና ጉዳት. Is BRICS good or bad for Ethiopia?

ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ስላለው ጥቅምና ጉዳት. Is BRICS good or bad for Ethiopia?

ታምሩ ጽጌ

December 24, 2023

ባለፈው ዓመት መጠናቀቂያ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ብሪክስን በይፋ መቀላቀሏ ከተነገረ ጀምሮ ከ330 በላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ኢትዮጵያ መቀላቀሏ ስላለው ጥቅምና ጉዳት የተደረገውን ጥናት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ታኅሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አደረገ፡፡

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱትን ብሪክስ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ላይ በይፋ የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ማኅበሩ ‹‹ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ምን ትጠቀማለች? ምንስ ትጎዳለች?›› የሚለውን ለመለየት ጥናት ማካሄዱን፣ በማኅበሩ የጥናትና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ በሠራው የባለሙያዎች ዳሰሳ ጥናት (Expert Survey)፣ ብሪክስን ወይም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለማሳተፍ የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ ግምገማ መደረጉን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ማኅበሩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዓላማዎቹን ማሳካት አለማሳካቱን በሚመለከት ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን በመጠቀም መገምገሙን አስታውቋል፡፡ ብሪክስ ሰባት ዓላማዎች ያሉት ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) ያቋቋመ ሲሆን፣ ዓላማዎቹን የሚያሳካ ከሆነ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ማሳካት ትችላለች ወይ?›› የሚልና ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ አባል መሆኗ (መቀላቀሏ) ሲታወቅ የሚወሰድባት ዕርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ሌሎችንም መለኪያዎች ተጠቅሞ፣ ማኅበሩ ጥናቱን ማካሄዱን ደግዬ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከብሔራዊ ጠቅላላ ምርት አኳያ (GDP Per Capita) ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ነው? ወይስ እየሰፋ ነው?፣ ወደ ውጭ የሚልኩት የንግድ ምጣኔያቸው (FDI) በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት መሻሻል አምጥቷል? የሚሉትን ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን በመጠቀም በተደረገው ጥናት፣ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት የገንዘብ ተቋማትን ሪፎርም እንደሚያደርግ ማስታወቁን ጥናቱ ጠቁሞ፣ ነገር ግን የፋይናንስ ጥያቄ በታዳጊ አገሮች ቢቀርብም፣ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደማይኖረው ጠቁሟል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ባንክም ሆነ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከፍተኛ ድምፅ (Voting Power) ያላቸው አገሮችን ይሁንታ ስለሚያስፈልግ መሆኑን ማኅበሩ በጥናቱ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ለመጠቆም ያህል 37 በመቶ የሚሆነውን ካፒታል ስቶክ የተቆጣጠሩት አምስት አገሮች፣ 52 በመቶውን አሥር አገሮችና 70 በመቶውን 20 አገሮች ድምፅ ያላቸው ሲሆን፣ 162 አገሮች ያላቸው ድምፅ 30 በመቶ ብቻ መሆኑን ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ እነዚህ 30 በመቶ ድምፅ ያላቸው አገሮች ለእያንዳንዳቸው ቢካፈል ያላቸው ድምፅ ከአንድ በመቶ በታች ከመሆኑ አንፃር፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ የሚለው፣ ዓላማ የተዘነጋና ምንም ዓይነት መሻሻል ያልታየበት መሆኑ በጥናቱ መረጋገጡንም አክለዋል፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች (HIC) እና ዝቅተኛ ልማት ያላቸው አገሮች (LDC) መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ የሄደ መሆኑንና በንግድ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎች እንደሚያሻሽል የገለጸ ቢሆንም፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የታየው ልዩነት ግን እየሰፋ በመሆኑ፣ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ሥርዓት ዓላማ አለመሳካቱንም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ማረጋገጣቸውን ማኅበሩ አስረድቷል፡፡

የውጭ ንግድ ሚዛንም ቢሆን በአገሮቹ መካከል ሰፊ ልዩነት ያለው ከመሆኑ አንፃር፣ በዓለም አቀፍ ወጪ ንግድ ከፍተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች ያደላ መሆኑን በጥናቱ ማረጋገጥ መቻሉን ደግዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ በኤክስፖርትና ከላይ በተገለጹት ሁሉም መሥፈርቶች ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት፣ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ሥርዓት የተሳካ ነገር እንደሌለ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ባደረጉት ጥናታዊ ግምገማ ማረጋገጣቸውንም ደግዬ (ዶ/ር) አክለዋል፡፡

ከላይ ከተብራራው አንፃር ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ለምንድነው? ለሚለውን ጥያቄ 233 የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን መስጠታቸውን ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ ጫና ስለበዛባት መሆኑን 49 በመቶ የሚሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲገልጹ፣ 47 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አዲስ የኢኮኖሚ ተቋም በመሆኑ እንደሆነ መግለጻቸው ተጠቅሷል፡፡ 41 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የተቀላቀለችው የውጭ ግንኙነቷ በጣም እየወረደ (እየወደቀ) ስለመጣ በመሆኑ እንደሆነ ሲገልጹ፣ 46 በመቶ የሚሆኑት ባለችበት የጂኦግራፊ አቀማመጥ ምክንያት መሆኑን እንደተናገሩ ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ 41 በመቶ ሚሆኑት ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብነት ስለበዛባት መሆኑን እንደገለጹና በአጠቃላይ 11 የሚደርሱ ምክያቶችን መስጠታቸውን አክለዋል፡፡

መንግሥት ግን በብቃትና በበጎ ሥራው መሆኑን እንደገለጸ ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የምጣኔ ባለሙያዎቹም ሆኑ መንግሥት የየራሳቸውን ትንታኔ ከመስጠት ባለፈ፣ ብሪክስን የተቀላቀሉ አገሮች ምንም ዓይነት ግልጽ የሆነ መሥፈርት እንዳልተቀመጠላቸውና ሁሉም የየራሱን መሥፈርት እንደሚያስቀምጥ አስረድተዋል፡፡

ብሪክስ የተቋቋመበት ዓላማ በዋናነት የዶላርን የበላይነት ለማስወገድ፣ አባል አገሮች በራሳቸው ገንዘብ ዓለም አቀፍ ንግድን እንዲገበያዩና እንዲጠቀሙ ለማስቻል መሆኑን የገለጹት ደግዬ (ዶ/ር)፣ 61 በመቶ የሚሆኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዶላርን ማስወገድ እንደሚቻል መናገራቸውን አስረድተዋል፡፡ 23 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ለማስወገድ አምስት ዓመታትን እንደሚወስድ ሲገልጹ፣ 53 በመቶ የሚሆኑት ግን አሥር ዓመታት፣ 67 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ 15 ዓመታትን እንደሚወስድና ከዚያም በላይ ዕድሜ እንደሚፈልግ 18 በመቶ የሚሆኑት መግለጻቸውን ደግዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ከእነ አሜሪካ ጋር ተነፃፃሪ ባይሆንም ቻይና፣ ህንድና ሩሲያ ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ውስጥ ያላቸው ካፒታል ኢንቨስትመንት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ዶላርን በአጭር ጊዜ ማስወገድ ስለማይቻል፣ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ጥቅም በአጭር ጊዜ ሊታወቅ እንደማይችልም ተነግሯል፡፡

የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ሊሳካ ስላልቻል ብሪክስን መቀላቀሉ ሊጠቅም ይችላል ያሉት 70 በመቶ የሚሆኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ 59 በመቶዎቹ የፖለቲካ ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል ሲያስረዱ፣ 67 በመቶዎቹ ግን ፖለቲካዊ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል የሚል ፍራቻ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ጥቅሙ ከጉዳቱ እንደሚበልጥ 51 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ሲናገሩ፣ 25 በመቶዎቹ ግን ጉዳቱ ከጥቅሙ ይበልጣል ማለታቸውን ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆኗ የሚያጋጥማት ጉዳት ወይም የሚያስከፍላት ዋጋ ብድር መከልከል መሆኑን 56 በመቶ የሚሆኑ የጥናቱ ተሳታፊ ባለሙያዎች ተናግረዋል ተብሏል፡፡ ከዓለም ባንክና ሌሎች አበዳሪ ተቋማት ያገኘችው ብድርም ሊቋረጥ እንደሚችል 43 በመቶ የሚሆኑት ተሳታፊ ባለሙያዎች መተንበያቸው ተገልጿል፡፡ ሌሎች 40 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ደግሞ የገንዘብ (ብር) መገሸብ (ዲቫሊዩ) ሊያጋጥም ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ማብራራታቸውን ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ችግር ሊገጥም እንደሚችል፣ የብድር ቅድመ ሁኔታዎች በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምሩ እንደሚችሉና ሌሎችም ትንታኔዎች በባለሙያዎቹ መቅረቡ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ሰፋ ያለ ጥናት አድርጎ ትንታኔ ከሠራ በኋላ በሰጠው ምክረ ሐሳብ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ መናገር የቻሉት፣ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው መንግሥት እንደሚለው በሜሪት ወይም ተመራጭ ስለሆነች ሳይሆን ባጋጠማት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን ነው፡፡ ብሪክስ ግን ለምን እንደተቀበላት ማንም የሚያውቅ እንደሌለ የገለጹት ደግዬ (ዶ/ር)፣ መሥፈርታቸው ህቡዕ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ሁሉንም ምክንያቶች እንድታውቅ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዓላማ ስላልተሳካ፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም ጠቃሚነቱን በደንብ ተገምግሞ መታወቅ እንዳለበት፣ የኢትዮጵያ መቀላቀልም ከጥቅሙና ከጉዳቱ አንፃር ተጠንቶ መረጋገጥ እንዳለበት አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

ለምሳሌ ያህል ማሌዥያ አመልክታ የነበረ ቢሆንም፣ የአገሯ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጥናት አድርገውና ገምግመው ባገኙት ውጤት ‹‹መቀላቀሏ ጥቅም የለውም›› በማለታቸው፣ ሳትቀላቀል መቅረቷን በመጠቆም፣ ኢትዮጵያም ያንን ማድረግ እንዳለባት ምክረ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

ምርመራው (ግምገማው) ከአባል አገሮች ጋር ተነፃፃሪ መሆን ስላለበት፣ ልዩነቱና አንድነቱን መርምሮ፣ የጋራ አጀንዳ ተገምግሞ መሆን እንዳለበት አክለዋል፡፡

ፈርጀ ብዙ አደጋ ስላለው ኢትዮጵያ እስካሁን ከምዕራቡ ዓለም የምታገኘውን ጥቅም የሚያካክስ ጥቅም መገኘት አለመገኘቱ መረጋገጥ እንዳለበትም በምክረ ሐሳቸው አሳውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር የገባቻቸው ብዙ ስምምነቶች (Engagements) ስላሉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከብሪክስ ጋር መሥራት የሚያስችላት አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዋናው የብሪክስ ዓላማና ኢትዮጵያም የተቀላቀለችበት ምክንያት በአገር ውስጥ ገንዘብ ለመጠቀምና የዶላርን የበላይነት ለመጣል በመሆኑ፣ ይህንን ለማድረግ አዳዲስ አጋር የማግኘት ተግዳሮት ሊገጥማት እንደሚችል ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከብሪክስ ጋር በብር መሥራት ከተቻለ፣ ከምዕራባውያን ጋር መሥራት ስለማይቻል ከሁለቱም ተቋማት ጋር መሥራት ግድ ስለሚል፣ በሁለቱም አባል አገሮች ተቀባይነትን ማግኘት ግድ ይላል ብለዋል፡፡

እንደ ህንድ ሩፒ፣ እንደ ቻይና የንና እንደ ሩሲያ ሩብል የኢትዮጵያ ብር ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? በሚል የሚጠይቁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ፣ ይህ ሁሉ መፈተሽ ስላለበት ጥልቅ ግምገማና ጥናት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ አዳዲስ አጋሮች ካላገኘት የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ስለሚያባብሰው አዲሱን ተቋም ከመቀላቀሏ በፊት በደንብ መገምገም አስፈላጊ መሆኑን አክለዋል፡፡ ለሚፈጠሩት አዳዲስ ብሎኮች ምን ዓይነት የልማት ዕድሎችን ማግኘት እንደሚቻል ማወቅና ጥቅምን ማሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ከመሆኑ ባሻገር፣ የፖለቲካ ውሳኔ ብቻ መፍትሔ ማግኘት እንደማይቻልም አሳስበዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ በሰጡት ትንታኔ፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ቴክኖሎጂና ሲስተም በጣም የወረደ በመሆኑ፣ በሚገባ ቴክኖሎጂና የፋይናንስ ሲስተም የታጠቀና ከመንግሥት ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ባንክ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ መረጋገጡንም ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን በብሪክስ ውስጥም ቢሆን ጭራ ሆኖ መቅረት እንደሚኖር አስታውቀዋል፡፡ የተፈለገውን ማግኘት እንደማይቻልና ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት የፋይናንስና ማርኬቲንግ ሁኔታ ህንድ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ብራዚል ሆኑ አዲስ ገቢዋ ግብፅም ብትሆን አብረው ለመሥራት እንደማይችሉ ጥናቱ ማመላከቱን ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ገለልተኛና ነፃ ብሔራዊ ባንክ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ካለበት ግን የትኛውም አገር አብሮ ለመሥራት ፍላጎት እንደማይኖረውም አሳስበዋል፡፡

በአጠቃላይ በጥናቱ ማወቅ የተቻለው ከብሪክስ አባል አገሮች ጋር ተነፃፃሪ የሆነ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የአስተዳደር ሥርዓት፣ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ ባንክ ከሌላት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ጥቅም ልታገኝ እንደማትችል በጥናቱ አመላካች ነገር መገኘቱን ደግዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

 

ethiopian reporter

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.