Breaking News
Home / Amharic / አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ …

አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ …

“አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ሊከሰት ለሚችል የከፋ ሁኔታ ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው” – ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም
**********************

አፍሪካውያን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ሊከሰት ለሚችል የከፋ ሁኔታ ራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም አሳሰቡ።

የዓለም ጤና ድርጅት በ33 የአፍሪካ አገራት ውስጥ 633 የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች መገኘታቸውንና እስካሁን 17 ሰዎች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል።

ቫይረሱ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በፍጥነት የመዛመት ባህርይ እንዳለው የገለጹት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ አፍሪካውያንን ሊያዘናጋ አይገባም ብለዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገራት 633 የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች መመዝገባቸውን፣ ሆኖም ግን አሁንም ያልተደረሰባቸው እና ሪፖርት ያልተደረጉ ታማሚዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ማናቸውም ዓይነት የሰዎች መሰባሰብ ሊቆም ይገባል፣ አፍሪካ ልትነቃ ይገባል በማለት በአጽንኦት አሳስቧል።

ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ ጋምቢያ፣ ሞሪሽየስ እና ዛምቢያ የመጀመሪያ ታማሚዎች ማግኘታቸውን ይፋ አድርገዋል ብሏል።

ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ መድረሱን እና ከስምንት ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ገልጸዋል።

በሽታውን ይበልጥ ለመከላከል አገራት የበሽታው ምልክት ያለባቸውን ሰዎች መለየት፣ መመርመር፣ ማስታመም እና ሌሎች ታማሚዎች መኖር አለመኖራቸውን መከታተል መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በርካታ አገራት ከድርጅታቸው የሚወጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑንም አመልክተዋል።

ምንጭ:- የዓለም ጤና ድርጅት

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.