<< አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ካስፈለገ በውሸት ላይ የተመሰረቱና የተመረጡ የታሪክ ንባቦችን ማረም ያስፈልጋል !!! >>
(ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ)
.
አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የታሪክን አረዳድ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ተገለፀ፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት እንደሌለ፤ በታሪክ አረዳድ፣ በትርክቶች፣ በብሔራዊ ጀግኖችና በምልክቶች መግባባት ላይ እንዳልተደረሰ፤ ለዚህ ትልቁ ችግርም ያልተስተካከለ የታሪክ ምልከታና ብያኔ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ደሳለኝ ማብራሪያ፤ ሕዝቦች ለዘመናት አብረው አንፀባራቂ ድሎችን አስመዝግባዋል። በግንኙነታቸው ውስጥም መልካምም መጥፎም ገጠመኞችም ነበሯቸው። ከ1960ዎቹ ወዲህ የተፈጠሩ ብሔረተኞች የችግሮቹ መንስዔና በዳይ አድርገው ጨቋኝ ተጨቋኝ በማለት የተሳሳተ የታሪክ ብያኔ ይሰጣሉ። ይህ በስህተት ላይ የተመሰረት ብያኔ አገራዊ መግባባት እንዳይፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ዶክተር ደሳለኝ ‹‹አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር የታሪክን አረዳድ ማስተካከል። በአገሪቱ የተፈጠረው ልማትም ሆነ ጥፋት የሁሉም ሕዝቦች የጋራ አድርጎ መውሰድ ይገባል። በውሸት ላይ የተመሰረቱና የተመረጡ የታሪክ ንባቦችን ማረም። ፖለቲከኞች ባለፈ ታሪክ ከመነታረክ ወጥተን ለልጆቻችን መልካም አገር ለማውረስ የቀጣይ የ50 ዓመታት የጋራ ርዕይ በማስቀመጥ ወደ ሥራ መግባት አለብን፤ ታሪክን ለፖለቲካ መሣሪያና ትርፍ ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል›› ብለዋል።
ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ባለድርሻዎች አሉ። የፖለቲካ ኃይሎች ግን ያለፈ ታሪክ ላይ ከመነታረክ ወጥተን የኢትዮጵያ መጽዒ ዕድል ላይ በጋራ መፍትሄ መፈለግ አለብን ያሉት ዶክተር ደሳለኝ፤ መንግሥት፣ የታሪክ ምሁራንና የማህበረሰብ አንቂዎች የተሳሳቱትን አካሄዶች ማስተካከል ላይ መስራት እንዳለባቸው ዶክተር ደሳለኝ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀዋል።