Breaking News
Home / Amharic / አብን እንዴት ተጀመረ? በስዩም ተሾመ

አብን እንዴት ተጀመረ? በስዩም ተሾመ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከየትና እንዴት መጣ?

ሰሞኑን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰኘው አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረቱን ተከትሎ በአንዳንድ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን፣ እንዲሁም የአንድነት አቀንቃኝ በሆኑ ወገኖች መካከል አላስፈላጊ እሰጣ-ገባ እየተካሄደ ነው። ራሴን ማጋነን አይሁንብኝና፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሚባል ፓርቲን ስለማቋቋም ሳይነሳ፣ ኦቦ ለማ መገርሳ ወደ ባህር ዳር መሄድ ሳያሰብ፣ የኦሮማራ ጥምረትና ትብብር ሳይጀመር፣… ከሁለት አመት በፊት ከታች በምስሉ ላይ በተገለፀው መልኩ የአማራ ልሂቃን ከቀኝ ወደ ግራ ዘመም፣ የኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ዘመም ፖለቲካ በሚያደርጉት ሽግግር በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ጥምረት እንደሚመሰርቱ ገልጩ ነበር።

በዚህ መልኩ በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የተጀመረው የኦሮማራ ጥምረት ብአዴንና ኦህዴድ እርስ-በእርስ እንዲተባበሩ በማድረግ የህወሓት የስልጣን የበላይነት ለማስወገድ አስችሏቸዋል። አብዛኞቹ የኦሮሞ ልሂቃን ሲያራምዱት የነበረውን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ወደ በመተው ኢትዮጲያዊ አንድነትን ማቀንቀን ጀምረዋል። በተቃራኒው ብዛት ያላቸው የአማራ ልሂቃን ሲያራምዱት የነበረውን ኢትዮጲያዊ አንድነት ወደ ጎን በመተው የአማራ ብሔርተኝነትን ማቀንቀን ጀምረዋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መመስረት የዚሁ የሽግግር ሂደት ውጤት ነው። ስለዚህ የራሱን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የመጣ ስለሆነ እንደ ልዩ ፖለቲካዊ ክስተት መታየት የለበትም። በመሆኑም “እንዴት የአማራ ብሔርተኛ ቡድን ሊፈጠር ይችላል?” ብሎ መረባረብ አያስፈልግም፣ ወይም “የአማራ ብሔርተኛ ቡድን ስለተቋቋመ የተለየ ነገር ይሰራል” ብሎ መጠበቅ አግባብ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን የፖለቲካ ንቅናቄ ከቅኝ ወደ ግራ እና ከግራ ወደ ቀኝ የተሸጋገረበትን ምክንያት መዝርዝር መረዳት ያስፈልጋል።

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ኢትዮጲያ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ሽኩቻ የነበረው በኦሮሞ፥ አማራና ትግራይ ልሂቃን መካከል እንደነበር ይታወቃል። ለዚህ ዋናው ምክንያት ሦስቱ የፖለቲካ ቡድኖች የሚያራምዱት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው የስልጣን ልዩነት ነው። እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የትግራይና ኦሮሞ ልሂቃን በአብዛኛው ከሀገራዊ አንድነት (ኢትዮጵያዊነት) ይልቅ በዘወግ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የሚያራምዱ ናቸው። በተቃራኒው አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአብዛኛው ከዘወግ ብሔርተኝነት ይልቅ በሀገራዊ አንድነት (ኢትዮጵያዊነት) እሳቤ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ነበራቸው።

ይህ በተቃዋሚ ጎራ ብቻ ሳይሆን ሦስቱን ክልሎች በሚወክሉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ ጭምር ልዩነቱ በግልፅ ይታያል። ለምሳሌ ቀንደኛ የሚባሉት የህወሓትና ኦህዴድ አመራሮች የዘወግ ብሔርተኝነት አራማኞች መሆናቸው ይታወቃል። በአንፃሩ አብዛኞቹ የብአዴን ነባር አመራሮች የቀድሞ የኢህአፓ አባላት የነበሩ ሲሆን በአብዛኛው የአንድነት አቀንቃኞች ነበሩ። ከዚህ በተረፈ፣ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የዘውግ ብሔርተኝነት የሚያራምዱ የብአዴን አመራሮች ፀረ-አማራ የሆነውን የህወሓት አስተምህሮት የሚያቀነቅኑ ነበሩ።

ምንም እንኳን የሚያራምዱት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት አንድ ዓይነት ቢሆንም ከፖለቲካና ኢኮኖሚ አንፃር መሰረታዊ ልዩነት አላቸው። የትግራይ ልሂቃን በሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣንና ኢኮኖሚ ላይ የበላይነት ነበራቸው። በአንፃሩ የኦሮሞ ልሂቃን ያላቸው የፖለቲካ ስልጣን የህወሓት መጠቀሚያ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም። በመሆኑም የኦሮሞ ልሂቃን ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር የነበራቸው ሚና በጣም ውስን ነበር። የአማራ ልሂቃን በፖለቲካና ኢኮኖሚው ረገድ የክልሉን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር የነበራቸው አቅምና ስልጣን ልክ እንደ ኦሮሞ ልሂቃን ውስንና አነስተኛ ነበር።

በመንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥና ውጪ የነበሩት የኦሮሞና አማራ ልሂቃን የትግራይ ልሂቃንን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማስወገድ የሚያስችል ፖለቲካዊ አቅም አልነበራቸውም። የኦሮሞ ልሂቃን ከትግራይ ልሂቃን ጋር ተመሳሳይ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም የህወሓቶች መጠቀሚያ ከመሆን አልዘለሉም። የአማራ ልሂቃን ከህወሓቶች የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት የነበራቸው ቢሆንም የአማራን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አልቻሉም።

ህወሓት የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማስቀጠል የሚከተለው ስልት፤ የአማራ ልሂቃንን አቋምና አመለካከት በትምክህት፣ የኦሮሞ ልሂቃንን ደግሞ በጠባብነት በመፈረጅ በኃይል ማፈን ነበር። ተቃዋሚዎች ከሆኑ ደግሞ ትምክህትና ጠባብነት የሚሉት ወደ ግንቦት7 እና ኦነግ አባልነት ቀይሮ በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጁ ይከስሳል፣ ያስራል፣¸ያሰቃያል።

በመሰረቱ “ጠባብ ብሔርተኛ” (ጠባብነት) – “ለጎሳው ብቻ የሚያስብና የሚያደላ፣ በሌላው ላይ ጥላቻ የሚያሳይ” ማለት ነው። “ትምክህት” (ትምክህተኛ) – “ከመጠን በላይ በራስ መመካት፥ መተማመን፣ ራስን ከፍ አድርጎ የሚያይ” ማለት ነው። በዚህ መሰረት፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” ከሌሎች ብሔሮች ይልቅ የራሱን ብሔር ወይም ጎሳ ጥቅምና ፍላጎት የሚያስቀድም ሲሆን “ትምክህተኛ” ደግሞ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን የሚሞክር ነው።

ህወሓት በብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳለው ይታወቃል። ሆኖም ግን፣ ባለፉት 25 አመታት በተግባር እንደተመለከትነው ይህ የፖለቲካ ቡድን በአንድነት ሆነ በብሔርተኝነት ጎራ ከተሰለፉ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር አብሮ የመስራት ፍላጎት ሆነ ዓላማ የለውም። ይህ የሆነበት መሰረታዊ ምክንያት ህወሓት ብሔርተኛ ብቻ ሳይሆን ትምክህተኛ ጭምር ስለሆነ ነው።

እንደ “ጠባብ ብሔርተኛ” ህወሓት ከሌሎች ብሔሮች ይልቅ የራሱን ብሔር ጥቅምና ፍላጎት ያስቀድማል፣ እንደ “ትምክህተኛ” ደግሞ የራሱን ጥቅምና ፍላጎት በሌሎች ብሔሮችና የፖለቲካ ቡድኖች ላይ ይጭናል። ስለዚህ ህወሓት “ጠባብ ብሔርተኝነት” የሚለውን አፍራሽ አገላለፅ የሚጠቀመው በዋናነት የኦሮሞ ልሂቃን የሚያነሷቸውን የመብትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በኃይል ለማዳፈን ነው። በተመሳሳይ “የትምህክት አንድነት” የሚለውን የሚጠቀመው ደግሞ በዋናነት የአማራ ልሂቃን የሚያነሷቸውን የመብትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በጉልበት ለማፈን ነው።

በዚህ መልኩ ህወሓት በአማራና ኦሮሞ ልሂቃን ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ የሚከተለውን ለውጥ አስከትሏል፡- አንደኛ፡- የአማራ ልሂቃን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ከአንድነት ወደ ብሔርተኝነት እንዲሸጋገር፣ ሁለተኛ፡- የኦሮሞ ልሂቃን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ከብሔርተኝነት ወደ አንድነት እንዲሸጋገር፣ ሦስተኛ፡- በዚህ የሽግግር ሂደት ውስጥ የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ጥምረት እንደሚመሰርቱ ያስችላል። ይህን የለውጥ ሂደት በ2008 ዓ.ም ባወጣሁት ፅሁፍ ላይ እንደሚከተው ገለጬ ነበር፡-

“ትምክህተኛ” የሚለው እሳቤ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በባህላቸውና በታሪካቸው ላይ ያላቸውን የራስ መተማመን ስሜት የሚሸረሽር ነው። በዚህ መልኩ የሚደረገው ተፅዕኖ በአማራ ልሂቃን ላይ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ይፈጥራል። አንድ ሰው በአማራነቱ ብቻ “ትምክህተኛ” እየተባለ ታሪኩና ማንነቱ እንደ ጥፋት ሲቆጠር በውስጡ የብሔርተኝነት ስሜት ያቆጠቁጣል። በመሆኑም አማራን “የትምክህት አንድነት” በሚል እንደ ብሔር የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከአንድነት ወደ ብሔርተኝነት እየቀየረ መጥቷል። በተመሣሣይ፣ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው እሳቤ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ያለውን ድርሻ የሚያንኳስስ፤ በሀገሪቱ አንድነት ላይ ያለውን ሚና ከምሶሶነት ወደ ቅርጫፍነት የሚያሳንስ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚገባውን መጠየቁ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ “በጠባብነት” ሲፈረጅ በኃይል ሚዛኑን ውስጥ የሚገባውን ድርሻ ለመያዝ በራሱ መንቀሳቀስ ይጀምራል። በመሆኑም ኦሮሞን “ጠባብ ብሔርተኛ” በሚል በሀገሪቱ አንድነት ውስጥ የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለነበር፣ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከብሔርተኝነት ወደ አንድነት እየቀየረ መጥቷል። የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ በዚህ የሽግግር ሂደት መሰረት ከሁለት ተቃራኒ ጫፎች ወደ መሃል በመምጣት ያልተጠበቀ ጥምረት ተፈጥሯል። ይህ አንደ ቀድሞው በሁለት ተቃራኒ ፅንፈኞች መካከል የተፈጠረ ጥምረት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁለቱም ሕዝቦች በማንነታቸውና በሆኑት ልክ የሚገባቸውን ጥቅምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴው የተፈጠረ የጋራ ጥምረት ነው። በመሆኑም የኦሮሞና አማራ ጥምረት በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ጥምረት ነው።

በአጠቃላይ የአማራና ኦሮሞ ልሂቃን በሚከተሉት የፖለቲካ አመለካከት ረገድ ያሳዩት ለውጥ አንደኛና ሁለተኛ ላይ በተገለፀው መሰረት የመጣ ነው። ሦስተኛ ላይ የተገለፀው የለውጥ ሂደት ደግሞ የዶ/ር አብይ አመራር ወደ ስልጣን እንዲመጣና ህወሓት የነበረውን የስልጣን የበላይነት እንዲያጣ አድርጎታል። “ይህ የለውጥ ሂደት በአማራና ኦሮሞ ልሂቃን መካከል ያለውን ግንኙነት ወደዬት ይወስደዋል? በቀጣይ የህወሓት ሚና ምን ይሆናል? እነዚህ ለውጦች የሚፈጥሩት ተፅዕኖ የሀገራችንን ፖለቲካ ወደዬት ሊወስደው ይችላል?” የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በቀጣይ ፅሁፍ በዝርዝር ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ለአሁኑ ግን በኦቦ ለማ መገርሳ የተቀጣጠለው ኢትዮጵያዊነት ሆነ በአብን የተጀመረው ብሔርተኝነት የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ በሚደረግ ትግል የተቀየሱ የትግል ስልቶች ናቸው። ስለዚህ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መምጣት እንደ ልዩ ፖለቲካዊ ክስተት ተወስዶ ላለመግባባትና እሰጣ-ገባ መንስዔ ሊሆን አይገባም።

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.