አማራ ባንክ
አማራ ባንክ ሰኔ 11 ሥራውን በይፋ እንደሚጀምር አስታወቀ።
በባንኩ የምረቃ ዕለትም 70 የተሟሉ ቅርጫፎች የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ይኾናል ተብሏል።እሰከ ሰኔ 30 ባሉት ቀናቶች ባንኩ ቅርንጫፎቹን ወደ ከ100 በላይ የሚያሳድግ መኾኑንም ገልጿል።
የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ መላኩ ፋንታ እንዳሉት ባንኩ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የተከፈተ ነው፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ የተጀመረ ባንክ ነው ብለዋል።
ባንኩ የሕዝብ ባንክ መኾኑን አንስተው እሰካሁን በብሔራዊ ባንክ ደንብ መሠረት የአክሲዮን ሸያጭ መከናወኑን አንስተዉ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች አክሲዮኖች ተሽጠዋል ብለዋል።
የካቲት 2/2014 ዓ.ም ዋና እና ምክትል ሥራ አስፈጻሚዎችን ማስመረጡንም አንስተዋል።
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ከበደ በበኩላቸዉ እስከ ሰኔ 30 አጠቃላይ 100 ቅርጫፎች ሥራ እንደሚጀምሩ ጠቅሰዉ ሰኔ 11 ላይ በመክፈቻዉ 70 ቅርጫፎች ሥራ ይጀምራሉ ብለዋል።
የሠራተኛ እና የሥራ ቁሳቁስ ግብዓት የማሟላት ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።ዋና መሪ ቃሉን “ከባንክ ባሻገር “ብሎ የጀመረዉ አማራ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን በሥራዎቹ እንደሚወጣ አስታውቋል።
እስከ ሰኔ 11 ባሉት ቀኖችም ባንኩ የፓናል ዉይይት፣ የደም ልገሳ እና ሌሎችም መርኃግብሮች እንደሚኖሩት አመላክቷል።
ባንኩ የማኅበራዊ አገልግሎቱን ለመወጣት እንዲያስችለው ሥራ በሚጀምርበት ሰኔ 11 ቀን ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 3 ሰዓት ድረስ የአምበሳ አውቶቡስ ተጠቃሚዎችን ወጭ መሸፈኑን አስታውቀዋል።