Breaking News
Home / Amharic / አብን በፓርላማ ተወክሎ ለአማራ ሕዝብ ምን ለውጥ አመጣ? አማራ ለምን በድርድሩ አልተወከለም? ደሳለኝ ጫኔ (Dr.)

አብን በፓርላማ ተወክሎ ለአማራ ሕዝብ ምን ለውጥ አመጣ? አማራ ለምን በድርድሩ አልተወከለም? ደሳለኝ ጫኔ (Dr.)

ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መሥራችና ከፍተኛ አመራር፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡ በአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርት በሰላማዊ ሁኔታ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት፣ እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያላቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ከሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡– የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በምርጫ ተወዳድሮ አባላቱ ፓርላማ በመግባታቸው ለሚወክለው የአማራ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ለውጥ አመጣ ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- በ2013 ዓ.ም. የተካሄደው ምርጫ በርካታ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ በበርካታ አካባቢዎች በምርጫ ሒደቱ ላይ በነበሩ ችግሮች፣ በመንግሥት ካድሬዎች አፈናና የድምፅ ማጭበርበር ምክንያት በርካታ ልናገኛቸው የምንችላቸው ድምፆችና መቀመጫዎች ነበሩ የሚል ግምገማ ነው የነበረን፡፡ ያም ሆኖ ግን ቢያንስ በፌዴራል ፓርላማና በአማራ ክልል ምክር ቤት ከገዥው ፓርቲ ቀጥሎ ከፍተኛ  መቀመጫዎችን አብን አግኝቷል፡፡ አብን በአማራ ክልል ምክር ቤት ውስጥ 15 መቀመጫዎችን፣ በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደግሞ አምስት መቀመጫዎችን ማግኘት ችሏል፡፡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፎካካሪ ፓርቲዎች የተያዙት በአጠቃላይ  12 መቀመጫዎች ናቸው፡፡ እንግዲህ በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዚህ የተሻለ መቀመጫዎችን ያገኙባቸው ጊዜያት የሚታወሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በምርጫ 97  በአማራ ክልልም ሆነ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከምርጫ 2013 የተሻለ ድምፅና መቀመጫዎች አግኝተው ነበር። ስለዚህ አሁን የዴሞክራሲ ግንባታ ሒደታችን መሻሻል ላይ ነው ወይም እያደገ ነው የሚያስብል ሳይሆን፣ ከዓመት ዓመት እየቀጨጨ መሄዱን የሚያሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ፓርላማ የገባነው የአብንም ሆነ የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ለወከልነው ሕዝብም ለአገራችን ኢትዮጵያም፣ በቻልነው መጠን ድምፅ ለመሆን ሞክረናል፡፡ በተለይ ወደ ፓርላማ በገባንበት ወቅት ወይም ፓርላማው ሥራ ሊጀምር አካባቢ ለአገራችን ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገናል ብዬ አስባለሁ።  መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ የአገሪቱ ሁሉም አቅሞች የአገር ሉዓላዊነትና ህልውና መከላከል ላይ እንዲያተኩር ለመጠየቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲጠሩልን አድርገናል፡፡ ማብራሪያዎችን ጠይቀናል፡፡ በመንግሥት ላይም የቻልነውን ጫና በማድረግ ጠንካራ የሆነ ሥራ እንዲሠራ ተከታታይ ግፊት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በአጠቃላይ እንግዲህ ካሰማናቸው የሕዝብ ድምፆች በላይ ትልቁ ስኬታችን ብዬ የማስበው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ሕወሓት እስከ ደብረ ሲና ገፍቶ እስኪደርስ ድረስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቶሎ ማወጅ ሲገባው ዘግይቶ ነበር። ነገር ግን ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ከአማራ ክልል የገዥው ፓርቲ ተወካዮች ጋር በመሆን ያነሳናቸውን ጥያቄዎች መንግሥት በትኩረት ዓይቶ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ አድርገናል ብለን እናስባለን፡፡ እነዚህንና በርካታ የመንግሥት አሠራር ድክመቶችንና ስህተቶችን ለመተቸት ሞክረናል። መልካም ናቸው ያልናቸውን ሥራዎች በግልጽ ለማበረታታት፣ መስተካከል ለሚገባቸው ትችት በማቅረብ  የሚጠበቅብንን ነገር ለማድረግ ሞክረናል፡፡  

ሪፖርተር፡– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማካሪ ኮሚቴ አባል ነዎት፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ካገኘ ፓርቲ ጋር በዚህ ደረጃ አብሮ መሥራት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- አንተ እንደገለጽከው በምክር ቤቱ የአማካሪ ኮሚቴ ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ ምክትል አፈ ጉባዔ፣ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትርና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች አለንበት፡፡ የዚህ ኮሚቴ ዋነኛ ኃላፊነት አንደኛው የምክር ቤቱን አስተዳደራዊ ሥራዎች መምራት ሲሆን፣ ሁለተኛው ምክር ቤቱ የሚወያይባቸውን አጀንዳዎች መቅረፅና አዘጋጅቶ በአሠራርና በአባላት ሥነ ምግባር ደንቡ መሠረት ለምክር ቤቱ ለመወያያነት ማቅረብ ነው፡፡ በዚህ በአማካሪ ምክር ቤቱ ውስጥ ከእነ ውስንነቱም ቢሆን ድምፃችን በደንብ ይሰማ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በተለይ አጀንዳ ማቅረብንና አጀንዳ ማሻሻልን በተመለከተ ቀድመው እንዲታዩ የምንላቸውን ነገሮች፣ በአፈ ጉባዔውም ሆነ በሌሎች አመራሮች በትኩረት ይታዩ ነበር። የምንሰጣቸውንም ሐሳቦች ገምግሞ ከምክር ቤቱ አስተዳደራዊ ሥራዎችም ሆነ ከአጀንዳ ቀረፃ ጋር ድምፃችን በበቂ ሁኔታ ይሰማ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ያ ማለት ግን ችግር አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቀን በወር አንድ ጊዜ እንዲኖር የአባላት ሥነ ምግባርና አሠራር ደንቡ ይፈቅዳል፡፡ እንዲሁም የተቃውሞ ድምፃችንን አዘጋጅተን እንድናቀርብም ይጠበቃል፡፡ በእኛ በኩልም በሕግ ማመንጨት ሒደት ውስጥም አጀንዳዎች ቀርፀን እንድናቀርብ ይፈቅዳል፡፡ ነገር ግን ያን የምንሳተፍበትን ሒደት በከፍተኛ ሁኔታ የተገደበ ወይም በገዥው ፓርቲ በበላይነት የተያዘ ነበር፡፡ በዓመቱ መጨረሻም ላይ እነዚህን ጉዳዮች ገምግመናል፡፡ በዚህ ዓመት በእርግጠኝነት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ቀን በወር አንድ ጊዜ እንዲከበር፣ እኛ አጀንዳ እያቀረብን የምንወያይበትና መንግሥት ደግሞ በተደጋጋሚ የውሳኔ ሐሳቦች ሲቀርቡ እንደ ልማዳዊ አሠራሩ የድጋፍ የውሳኔ ሐሳቦችን ብቻ ያቀርባል፡፡ በዚያ ላይ ተወያይተን በድምፅ ይወሰናል ማለት ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን አብን ብቻ ሳይሆን የሌሎች የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጭምር በጋራ እየተወያየንበት ያለው፣ መንግሥት ለሚያቀርበው እያንዳንዱ የድጋፍ የውሳኔ ሐሳብ የተፎካካሪ ፓርቲው የፓርላማ ቡድን ከዚያ የተለየ የውሳኔ ሐሳብና ድምፆችን የምናቀርብበት አሠራር መዘርጋት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ እነዚህ ጥያቄዎችም ተቀባይነት ይኖራቸዋል ብለንም እንገምታለን፡፡ የአባላት ሥነ ምግባርና አሠራር ደንቡም በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ይመለከተኛል የሚል ዜጋ፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የፓርላማ አባላት ረቂቅ ሕጎችን የማመንጨትና ይዘው ቀርበው ሕግ እንዲሆኑ ፓርላማውን መጠየቅ ይችላሉ። ምንም እንኳን አሁን አንድ ፓርቲ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ አብላጫ ድምፅ መቀመጫውን የያዘ ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎች እንዲህ ዓይነት ረቂቅ ሕጎችን ወደ ፓርላማ የማቅረብ መብት አላቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዓመት አንድ፣ ሁለትና ሦስት ረቂቆችን አቅርበን ፓርላማው እንዴት እንደሚያየው ለመፈተሽ እናስባለን፡፡ በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን በዚህ ዓመት አስተካክለን የእኛንም ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ከተያዙት አጀንዳዎች የወጡ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል፡፡ በአፈ ጉባዔውም እንዲቆሙ ሲደረጉ ይታያል፡፡ ይህ አሠራር እንዴት ይታያል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- በምክር ቤት ውስጥ ውይይት ለማድረግ በመጀመርያ አጀንዳው በአማካሪ ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ከፀደቀ በኋላ ነው ውይይት የሚደረገው፡፡ ነገር ግን ከምክር ቤቱ አባላት ውስጥ ቀድሞ ያልተወያየንበትና በአማካሪ ኮሚቴ ያልተያዘ አጀንዳ ከሆነ፣ በልዩ ሁኔታ ታይቶ አጀንዳው እንዲያዝ የመጠየቅ መብት አለ፡፡ አፈ ጉባዔው አጀንዳው አስፈላጊ ነው ብለው ከፈቀዱ ምክር ቤቱ በአጀንዳነት ይዞ ሊወያይበት ይችላል፡፡ በወለጋ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ብሔርንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ከፍተኛ ጥቃትና የጅምላ ጭፍጨፋ በተፈጸመበት ወቅት፣ በዕለቱ ተይዘው ከነበሩ አጀንዳዎች በተለየ የአብን የፓርላማ አባላት ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ በመወያያየትና መነጋገርና የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለብን፣ ከዚህ የበለጠ ለአገራችን አስቸኳይ አጀንዳ ሊኖር አይገባም ብለን ጥያቄ ለማቅረብ ሞክረን በአፈ ጉባዔው በበጎ አልታየም፡፡ አፈ ጉባዔው ሐሳባችንን ለመግለጽ እንኳ ዕድል ባለመስጠታቸው፣ ያንን የተቀረፀ ቪዲዮ እንዲወጣ አድርገን በርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መወያያ እንዲሆን ያደረግንበት ሁኔታ የሚታወስ ነው፡፡ በሌላ በኩል የአፈ ጉባዔውን ሥጋትና በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በተተበተበ ፓርቲ  ውስጥ ያለባቸውን ተግዳሮት እንረዳለን። በገዥው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ከኢሕአዴግ የተወረሰ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ባህል አለ ብለን ስለምናስብ፣ አፈ ጉባዔው ያንን ጉዳይ ፈቅደው እንድንወያይ ቢያደርጉ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን በመጣሰ ችግር ውስጥ ሊያስገባቸው የሚችልበት ዕድል አይኖርም ብለን አናስብም፡፡ ስለዚህ አፈ ጉባዔው ያንን ሠግተው የእኛን ድምፅ ሲያፍኑ እኛ ችግሩ ከዚያ እንደሚመነጭ እንረዳለን፡፡ ግን ደግሞ በምክር ቤት አሠራር በጣም አንገብጋቢና አስቸኳይ ጉዳዮች ካሉ አማካሪ ኮሚቴ ሳያያቸው እንዲቀርቡ ተደርጎ በምክር ቤቱ አባላት ውስጥ አንድ ሦስተኛ ድምፅ ድጋፍ ካገኙ፣ በምክር ቤቱ የአሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንቡ መሠረት ውይይት በማድረግ የተፈቀደ ነው፡፡ በቀጣይ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ከተነሱ በአፈ ጉባዔው አማካይነት የሚደረጉ የማፈን ሙከራዎች ይታረማሉ ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡– አብን እንደ ፓርቲ በርካታ አስተያየቶች እየቀረቡበት ነው፡፡ በአንድ በኩል የክፍፍል መፈጠር፣ በሌላ በኩል ደግሞ የውስጥ ሽኩቻ ስለ መኖሩ ይነሳል፡፡ ፓርቲያችሁ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ግልጽ ቢያደርጉልኝ?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይመሠረታሉ፣ የሆነ ወቅት ላይ ጠንካራ እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፡፡ ከዚያም በሒደት ተግዳሮቶች ሲገጥማቸው አንዳንዶች  የመከፋፈል ወይም የመዳከም ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ አብን ውስጥ በመሠረታዊነት የነበረው ችግር ምንድነው? ባለፈው መጋቢት 2014 ዓ.ም. አካባቢ በባህር ዳር  የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚያ ጠቅላላ ጉባዔ በተለይ ሦስተኛውን አጀንዳ የድርጅት ሪፎርምና መዋቅራዊ ማሻሻያ ጉዳዮች አጀንዳ ተይዞ ስለነበር፣ እሱን በሚገባ ተወያይቶ ጉዳዩን ዘግቶ የመሄድ ችግር ነበር። ከዚያ ችግር ጋር ተያይዞ ያ አጀንዳ መቋጨት አለበት? ወይስ የለበትም? የሚሉ ክርክሮች ተነስተው የተወሰነው ከፍተኛ አመራር ያን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎችን በአንጃነት የመፈረጅ፣ እንዲሁም እኛ ብቻ የምንለው መንገድ ትክክል ነው የሚል አዝማሚያዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የአብን ጠቅላላ ጉባዔ እንደገና ተሰብስቦ ያደሩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳረፍ ሲችል ነበር። ምርጫ ቦርድ ጉባዔው እንዲካሄድ ውሳኔ ያስተላልፋል ብለን እናስባለን፡፡ ጉባዔው በዚህ ዙሪያ ከተወያየና ከመከረ በኋላ የጉባዔው ውሳኔ የድርጅቱ ገዥ የወደፊት አቅጣጫ ሆኖ ይወጣል ብለን እናስባለን። አብን ውስጥ አሁን ያለው ሁኔታ በአጠቃላይ በተወሰነው አመራርና በአባላት መካከል ከሪፎርም ጥያቄ ጋር የተያያዘ ችግር ነው። አብን የአማራ ድምፅነትና ተስፋነት፣ እንዲሁም አብን ትክክለኛ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን የያዘ መሪ ድርጅት መሆኑን ምንም ጥያቄ የሚነሳበት ንቅናቄ እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡– አብን አሁን ካለበት ሁኔታ ውስጥ ወጥቶ በቀጣይ ዓመታት ምን የተሻለ ነገር ይዞ ይመጣል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- የእኔ ተስፋ ምንድነው? በአጭር ጊዜ ውስጥ ጉባዔው እንዲደረግ ምርጫ ቦርድ መመርያ ይሰጣል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ እንግዲህ 580 ሰዎች ከሁሉም አካባቢ በአካል መጥተው የሚሳተፉበት በመሆኑ፣ በዚህ ጉባዔ አብን ራሱን ለውጦና አሻሽሎ እንደ አዲስ ጠንካራ የአማራ ሕዝብ ወኪልነቱን አረጋግጦ ከጉባዔው ይወጣል፡፡ በቀጣይ በሚካሄዱ አገራዊ ፖለቲካ ጉዳዮች የድርሻውን የሚወጣ፣ የአማራን ሕዝብን የሚያነቃና የሚያታግል፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ ከዚህ በፊት የወሰዳቸውን ጠንካራና ለአገር መከታ የሚሆኑ ዕሳቤዎችን የሚያረጋግጥና አገራችን አደጋ ውስጥ በገባችበት ወቅት ከአገራችን በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ አለመኖሩን በተከታታይ እንዳደረገው አጠናክሮ የሚያስቀጥል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶቻችን በፖለቲካ ትግል ይፈታሉ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ትግል ማድረግ የምንችለው አገራችን ውስጥ ሆነን ነው፡፡ አገርን የሚያተርፉ በርካታ ውሳኔዎችን እየወሰነና ከምሥረታው ጀምሮ እያራመደ የመጣ ድርጅት ነው፣ በቀጣይም እነዚህን በጎ አገራዊ አበርክቶዎች አጠናክሮ የሚቀጥልበት፣ በአካባቢያዊና በአገራዊ ምርጫዎች የተሻለ ዝግጅትና ተሳትፎ እያደረገ የተሻሉ ዕጩዎችን ይዞ የሚቀርብበት፣ በሒደት በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ የሚያደርግበትና የተሻለ አሻራ የሚያሳርፍበት ጊዜ ይዞ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡– ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ ምንድነው እየጠበቃችሁት ያለው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ጠቅላላ ጉባዔው የሚደረገው የሪፎርምና እንደገና ድርጅቱን የማጠናከር ሥራ ለማጠናቀቅ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ሒደት ውስጥ ያኔም በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ሲነሳ የነበረው ነባሩ አመራር በተለይ የመንግሥት ኃላፊነት የወሰደው ከፍተኛ አመራሩ፣ የመንግሥት ኃላፊነትና የፓርቲ ሥራዎችን አጣጥሞ መሥራት አልቻለም፡፡ በመንግሥት ሥራዎች ውስጥ በመጠመዱ የፓርቲ ሥራችን ተቀዛቅዟል፣ ተዳክሟል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት የተሰጣቸው ኃላፊነት ላይ እንዲቀጥሉ የያዙትን የአብን ወይም የድርጅት ኃላፊነት ደግሞ ለሌሎች እንዲያስረክቡ የሚል የጎላ ድምፅ ነበርና እንግዲህ በዚህ ዙሪያ ተወያይቶ አንድ ውሳኔ ያስፈልጋል ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔው ምናልባት በአንድ ወይም በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ቦርድም አስገድዶ ወይም በሌሎች መንገዶች አብን ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሂዳል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡– የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በመሠረተው መንግሥት ውስጥ በሥራ አስፈጻሚነት በመሳተፋቸው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አቅም እንዳነሳቸውና እንዳዳከማቸው በፓርቲዎቹ በሕዝቡም የሚነሳ ዕሳቤ አለ ይባላል፡፡ አብን በመንግሥት የሥራ አስፈጻሚ አካላት ውስጥ በመካተቱ ምን ፈጠረባችሁ?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- በቀጥታ ከዚያ ጋር አላያይዘውም ማለት የገዥው ፓርቲ ያን አስልቶና መከፋፈል ሊፈጥሩ ይችላሉ ብሎ አስቦ አድርጎት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል እንዲህ ዓይነት ድምዳሜዎች በጥንቃቄ መታየት አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡ አንድ ግልጽ የፈጠረው ነገር ምንድነው? በሚኒስትርነትና በቢሮ ኃላፊነት ደረጃ የተሾሙ ሰዎች የፓርቲ ሥራ በሥራቸው ላይ እንዳይነሳ መደረጉን ዓይተናል፡፡ እኛም አብን ውስጥ ሊቀመንበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ናቸው፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዘርፍን ካየኸው አገራችን ዋነኛ የልማት ምሰሶ ብላ ከለየቻቸው አምስት ዘርፎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ተቋም የሚመራ አንድ ሚኒስትርና የአብን ሊቀመንበር መሆን በጣም ውስብስብና ሰፊ የሆኑ ኃላፊነቶች ከአባላት፣ ከደጋፊዎች፣ ከአመራሩ፣ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ ከውጭ ደጋፊዎቻችንና ከሌሎች የሚመነጩ በርካታ ኃላፊነቶች ያሉበት ነው፡፡ የሚኒስትርነት የፓርቲ ኃላፊነትን እንዲሁ ማስኬድ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በመንግሥት ውስጥ ካየህ በገዥው ፓርቲ መዋቅሮች ሰፊ ናቸው፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲ መዋቅር ግን ጥቂት ሰዎች በጥቂት ገንዘብ ፓርቲውን እየመሩ ወደፊት እንደሄዱና የፓርቲውን ዓላማ እንዲያሳኩ ከመጠበቁ አንፃር፣ ቀላል ተግዳሮት እንዳልሆነባቸው የአብንን ብቻ ሳይሆን የኢዜማም ሆነ የሌሎች ፓርቲዎች ውስጠ አዋቂዎች ከገለጹልን ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እነዚህ ነገሮች ቀላል አይደሉም፡፡ ግን ደግሞ በመንግሥት ፖሊሲ ሐሳብ መስጠትና ተፅዕኖ ለማሳደር፣ መንግሥት የሚንቀሳቀስባቸውን ጉዳዮች ለመረዳትና መረጃዎችን ለማግኘት በርካታ ጠቀሜታዎች አላቸው፡፡ ስለዚህ በእኔ በኩል የማስበው ምንድነው? ተፎካካሪ ፓርቲዎች የመንግሥት ኃላፊነት ሲቀበሉ ከፓርቲ ኃላፊነቶቻቸው ነፃ ሆነው፣ በመንግሥት በኩል የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ዕድል ሊፈጥሩላቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ አብንም ውስጥ ወደፊት እንዲህ ዓይነቱ ነገር ቢለመድ የተሻለ ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥም ተሳትፏችን እንዲያድግ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥራዎችም ሳይቀጭጩና ሳይዳከሙ ወደፊት ለመንቀሳቀስ ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡  

ሪፖርተር፡– የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተጀመረው ሒደት ውስጥ በአብን ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል፡፡ ለአብነት እንኳ እርስዎም ያሉበት የአማራን ክልል የሚወክል አደራዳሪ ቡድን የተመሠረተ ሲሆን፣ አብን በሚጠቀምበት ማኅበራዊ ድረ ገጽ ደግሞ የአማራ ክልል በፌዴራል መንግሥቱ ተደራዳሪነት እንጂ ራሱን የቻለ የክልል ተደራዳሪ ሐሳብ እንደማይቀበል በማስታወቅ ተከታዮቹንም ከዚህ ዕሳቤ ተቆጠቡ ብሏል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በእርስዎና በአብን መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ባለፉት ጊዜያት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በተመለከተ ሰላም ለማምጣትና ለማስቆም እንቅስቃሴ ጀመሩ ከተባሉ ጀምሮ በርካታ የአማራ ሕዝብ ተወካዮች ከሰቪክ ማኅበራት፣ የተለያዩ ድርጅቶች ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራንና የተለያዩ የአማራ ድርጅቶች በተለይ በውጭ የሚኖሩ ከሃያ በላይ የአማራ ድርጅቶችና ማኅበራት አሉ፡፡ ፓርላማ ውስጥ የምንሳተፍ የአብን አባላት አለን፡፡ ዋነኛው ጉዳይ በ1983 ዓ.ም. የሽግግር ሒደት ወቅት የአገራችንን መፃኢ ዕድል የወሰኑ የፖለቲካ ውይይቶችና ውሳኔዎች ውስጥ የአማራ ሕዝብ አልተወከለም ነበር፣ እንዲወከልም አልተፈለገም ነበር፡፡ በታቀደ መንገድ እንዲገለል ታስበው በተደረጉ የሽግግር ሒደቶችና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፍ ተደርጎ ስለነበር፣ ያ ሒደት ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት የአማራ ሕዝብን ለዘር ማጥፋትና ለጅምላ ግድያ እንዲጋለጥ አድርጎታል፡፡ ከፖለቲካ፣ ከማኅበራዊና ከኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንዲገለል ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ በጠበቃትና በገነባት አገር ውስጥ አገር አልባና  ባይተዋር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፖለቲካ ሲስተም አሁንም መደገም የለበትም ብለን እናስባለን፡፡ እናም አንደኛ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደው ጦርነት የአማራ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንደኛ ተሳታፊ ነው፡፡ ሁለተኛ የጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ያረፈበት ክልል ነው፡፡ ሦስተኛ በዚህ የሰላም ሒደት ውስጥ የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ወደ ድርድር ጠረጴዛው ይቀርባሉ ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግሥት ተደራድሮ የአማራ ሕዝብን ጥቅም የሚያስከብርበት ዕድል አይኖርም፡፡ ሌላው ተደራዳሪዎችም የተመረጡት በፓርቲ መዋቅር ስለሆነ፣ ገዥው ፓርቲ የሚወክላቸው ሰዎች የአማራን ሕዝብ ሀቀኛ ጥያቄ ወክለው በመደራደር ጥቅሙን ያስከብሩለታል የሚል እምነት ስለሌለ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ለዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች አማካይነት አማራ ራሱን ችሎ መወከል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ዝግጁ ነን፡፡ ልጆች አሉን መሳተፍ እንችላለን ብለን በርካታ ዶክመንቶች ተዘጋጅተውና ኮሚቴዎች ተቋቁመው ስንሠራ ከቆየን በኋላ፣ በመጨረሻ 40 ያህል በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ለዚህ ሒደት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ የሚባሉ የአማራ ልጆች ከተለያዩ ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከውስጥም ከአገር ውስጥም ተለይተዋል፡፡ ከተለዩ በኋላም በንዑስ ኮሚቴዎች እየተደራጁ አጠቃላይ ሒደቱን የሚመሩ ደግሞ አራት ሰዎች ያሉበት፣ የአማራ ሕዝብ የሰላም ድርድር ልዑክ ኮሚቴ እንዲዋቀር አድርገናል ማለት ነው፡፡ ይህ ይፋ ሲደረግ ሁለትና ሦስት የሚሆኑ የአብን አሠራሮች የድርጅቱን ገጽና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ይቆጣጠሩ ስለነበር፣ በግላቸውም በአንድም ሆነ በሌላ ሒደት አልተመቸንም ስላሉ ብቻ የተቃውሞ ድምፅ አሰሙ ማለት የአብን አባል መዋቅር ደጋፊ ከፍተኛ አመራር ይህን ዕሳቤ አይደግፈውም ማለት አይደለም፡፡ ከ40ዎቹ መካከል ለምሳሌ ስድስትና ሰባት ያህሉ የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ፣ አራት  ደግሞ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  አባላት ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎች የሚሳተፉበት ስለሆነ የፓርቲው ጥቂት አመራሮች ተቃወሙት ማለት፣ ፓርቲው እንደ አጠቃላይ ይህን ሒደት ተቃውሞታል ማለት አይደለም፡፡ ሰሞኑን ሃያዎቹ የአማራ ማኅበራት በውጭ አገር የሚኖሩት ማለቴ ነው የድጋፍ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ምናልባት በቀጣይ ቀናት ደግሞ የአብን የክልልና የፌዴራል ምክር ቤት ተወካዮችና ከፍተኛ የዞንና የወረዳ መዋቅሮች ሁሉ ለዚህ ሒደት ድጋፋቸውን ይገልጻሉ ብለን እንጠብቃለን፡፡ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ከሞላ ጎደል በሰፊው ማዕቀፍ ካየኸው አብን የሚደግፈው ሒደት መሆኑን፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አመራርም ሆነ አባል የሚደግፈው መሆኑን ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– የአማራ ክልል የራሱ አደራዳሪ እንዲኖረው የተፈለገው በፌዴራል መንግሥቱ እምነት ስለሌላችሁ ነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- የፌዴራል መንግሥቱ ወይም ብልፅግና የሚመራው መንግሥት የአማራን ሕዝብ ጥቅሞች በሙሉ ልብ ይዞ ይሳተፋል የሚል እምነት የለንም፡፡ በነገርህ ላይ እኛ ብቻ አይደለንም ሕዝባችንም ይህ ነው እምነቱ፡፡ ዛሬ ብልፅግና በሚባለው ፓርቲ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ሆነው የምታያቸው እኮ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራር ሆነው ብአዴን በሚባለው ድርጅት ውስጥ ነበሩ፡፡ ዛሬም የድርድር ቡደኑ አባል ሆነው የተካተቱት ሰዎች እኮ ትናንት ወልቃይት ወደ ትግራይ ሲከለል፣ ራያ ወደ ትግራይ ሲከለል፣ ወፍላ ወደ ትግራይ ሲከለል ይከለል ብለው የወሰኑ ሰዎች ናቸው፡፡ እኛ ዋነኛ ተዓማኒነታቸውና ተጠሪነታቸው ለፓርቲያቸው እንጂ ለሕዝባቸው ነው ብለን አናምንም፡፡ ነገር ግን ሁሉም እዚያ ውስጥ ያለ አካል ተቆርቋሪ አይሆንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ግልጽ የሆኑ ሥጋቶች አሉን፡፡ እነዚህ ሥጋቶች ደግሞ ዝም ብለን አየር ላይ ያሉና በግምት የፈጠርናቸው ሳይሆኑ፣ በተጨባጭ ባለፉት ዓመታትና ባለፍንባቸው ታሪኮች የሚነሱ ጉዳዮች ስለሆኑ መነሳት አለባቸው፡፡ ሁለተኛ የፌዴራል መንግሥት አማራ ክልልን አይወክልም ከተባለ፣ የፌዴራል መንግሥት ትግራይንም ይወክላል እኮ፡፡ ትግራይ እስካሁንም የፌዴሬሽኑ አባል ነው፡፡ በእኛ በኩል የምናስበው የፌዴራል መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ ወደ ድርድር ይዟቸው የሚቀርቡ የድርድር ነጥቦች አሉ፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ ደግሞ በተለየ ሁኔታ ከሌሎች ክልሎች በተለየ የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች በጦርነቱ ውድመት የተፈጸመባቸው ናቸው፡፡ ያ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያዊ አልወደመም ማለት አይደለም በዚህ ጦርነት፡፡ ነገር ግን በተለየ ሁኔታ ከጦርነቱ መሠረታዊ መነሻ ጉዳዮች አንዱ የማንነትና የታሪክ በመሆኑ፣ እነዚህ ደግሞ በተለየ ሁኔታ በአማራና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ስለነበሩ፣ በዚህም እኛ ጠብቀነው የነበረው የአማራ ክልል መንግሥት ራሱን ችሎ ለድርድር ይቀርባል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ በፌዴራል መንግሥቱ የሥልጣን ገደብ ልክ፣ እንዲሁም በሕወሓት በኩልም የራሳቸውን ፍላጎት ይዘው ይቀርባሉ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል መንግሥት ያንን ጥያቄ አላቀረበም፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ያን ጥያቄ አላቀረበም ማለት የአማራ ሕዝብ ወኪሎች ወይም ድርጅቶች ዝም ብለው ይቀመጣሉ፣ ዝም ብለው ሒደቱን ይመለከታሉና ሌሎች በ1983 ዓ.ም. በአማራ ክልል ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ ወስነው የፌዴራል ሥርዓቱን እንደጫኑት ዝም ብለን እናያለን ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ አማራ በታሪክ ሌላ አካል ወስኖ እንዲቀበል የተደረገበት ሒደት አሁን ላይ አይሠራም፣ ልጆቹ ተደራጅተዋል፡፡ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጠንካራው የአማራ ሕዝብ ላይ ማንም ተወያይቶ ፍላጎቱን እንዲጭንበት አይፈቅዱም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ከሁሉም አደረጃጀቶች የተውጣጣን ልጆች ዛሬ የምናደርገው ትግል ለአማራ ሕዝብ ወሳኝ የታሪክ መታሰቢያ አድርገን ልናየው እንችላለን፡፡ ይህንም በዚህ ደረጃ አማራ በእኔ ጉዳይ፣ በእኔ ፍላጎት፣ በእኔ መብት እኔ እንጂ ሌላ ማንም ሊወስንብኝ አይገባም ብሎ ወደፊት መውጣቱ የሕዝባችን የትግል እመርታ የሚያሳይ አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– በሰላም ንግግሩ ለመሳተፍ ተደራዳሪዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጉዘው ንግግር ተጀምሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ከጅምሩም ያልነበረ የእናንተ ቡድን እንዴት ሊሳተፍ ይችላል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ምናልባት በቅርቡ ኮሚቴውንና የኮሚቴውን አባላት ማስተዋወቃችን እንጂ ይህን ጉዳይ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለአሜሪካ መንግሥትና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ከመልዕክተኞቻቸው ጋር በነበሩን ስብሰባዎች ስናነሳው የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን አልተሳካም ማለት ወደፊት አይሳካም ማለት አይደለም፡፡ እንደምታውቀው እንዲህ ዓይነት ድርድሮች ረዥም ጊዜ የሚፈጁ ናቸው፡፡ ሒደቶቹ ምናልባት ወራትን አልፎም ዓመታትን ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ጥያቄ ያቀረብክላቸው ዓለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጥያቄውን በበጎ ተመልክተው በሒደቱ እንድንሳተፍ ያደርጉናል ብለን እናስባለን፡፡ በሒደቱ እንድንሳተፍ ይጋብዙናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ የአማራ ሕዝብ በአግባቡ ያልተወከለበት የሰላም ንግግር ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ሕዝባችን ይሁንታውን ያልሰጠበት ማንኛውም የሰላም ሒደት ትርጉም ያለው ቀጣናዊ መረጋጋት ያመጣል ብለን አናስብም፡፡ በቅርቡ አሁን መግለጽ ከማልፈልጋቸው አንዳንድ ተቋማት ጋር ባደረግነው ውይይት ጥያቄያችን ፍትሐዊ መሆኑን ተቀብለውናል፡፡ ተሳትፎዎችን በምን ዓይነት መንገድ ማረጋገጥ ትችላላችሁ የሚለውን ወደፊት መነጋገር አለባችሁ የሚል ጥሩ ሊባል የሚችል የመጀመርያ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ዞሮ ዞሮ የእኛ ጉዳይ የመሳተፍና ያለመሳተፍ ሳይሆን፣ ትልቁ ጉዳይ የአማራ ሕዝብ በራሴ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ማንም ሊወስንብኝ አይገባም ብሎ ወደፊት መምጣቱ ነው፡፡ ከተሳተፍን ለሒደቱ በጎ አስተዋጽኦ እናበረክታለን ብለን እናስባለን፡፡ ነገር ግን እኛ ካልተሳተፍንበት ወይም የአማራ ሕዝብ ሀቀኛ ልጆች ካልተሳተፉበት፣ በአንድ የብልፅግና ፓርቲ ብቻ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት መወከል አለበት የሚለው ዘላቂ ሰላምና መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ከፍተኛ እምነት አለን፡፡ ከሕዝባችንም ያገኘነው አስተያየት ይህንን የሚያመለክት በመሆኑ ከንቱ ድካም ይሆናል የሚል ሥጋት ስላለን ለመንግሥት አካላት፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ለሕዝብ የማስረዳትና የማሳመን፣ እንዲሁም የዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡

ሪፖርተር፡– በፌዴራል መንግሥት የሚመራው ጥምር ኃይል ወደ ትግራይ ክልል በመግባት በርካታ ቦታዎችን ከሕወሓት ነፃ እያወጣ ባለበት በዚህ ጊዜ፣ የሰላም ንግግሩ  ተጀምሯል፡፡ የሁለቱ አካላት የመነጋገሪያ ነጥቦች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- እንግዲህ በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሁላችንም ኩራት በሆነ መንገድ በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠር፣ የሕወሓት ታጣቂዎች በዕገታ ይዘዋቸው የነበሩ ቦታዎችን ነፃ በማውጣት ወደፊት እየገሰገሰ ነው፡፡ ይህ ሒደት ተጠናክሮ በመቀጠል ሁሉንም የትግራይ አካባቢዎች ከሕወሓት ተዋጊዎች ነፃ በማድረግ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች የዕለት ደራሽ ዕርዳታ፣ የመብራት፣ የውኃ፣ የቴሌና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲዳረሱ ማድረግ ማስቻል የፌዴራል መንግሥቱ የመደራደር አቅም ይጨምርለታል ብለን እናስባለን፡፡ በመሆኑም ይህ ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሎ በርካታ አካባቢዎችን ነፃ ቢያወጣ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በድርድሩ የተሻለ ውጤት የማግኘት ዕድል ይኖረዋል፡፡ ወይም ደግሞ በሒደቱ የበላይነት ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ሕወሓት ሙሉ ከተሞችን ለቆ በጦርነቱ ቢሸነፍ ወይም የሕወሓት ተዋጊዎች ከተሞችን ለቀው ቢበተኑም እንኳ ጦርነቱ ተጠናቀቀ ወይም ተደመደመ ሊባል አይችልም፡፡ በየትም አገር በተካሄዱ ጦርነቶች በተፋላሚ ወገኖች የደረሰውን ውድመት ብንመለከት ጦርነቱ ዘላቂ መፍትሔ ስለማያመጣ፣ ከጦርነቱ ይልቅ በመወያየት ወደ መፍትሔ ይሄዳሉ፣ እኛም ይህን ይቀበሉታል ብለን እናስባለን፡፡ ለመደራደሪያነት ያነሱት አንደኛው ጥያቄ የሰብዓዊ ዕርዳታ ያለ ምንም ገደብ መከናወን አለበት የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግሥት ትግራይን በተቆጣጠረ ቁጥር ያዳርሳል፣ አያዳርስም የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ወራት የሚታይ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሰላም ንግግር ሒደት ገና ጅማሬ ነው፡፡ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ አሁን የሚደረገው ውይይት የሥነ ሥርዓትና በምን ዓይነት ሒደት የሰላም ንግግር ሒደቱ ይመራል በሚለው ላይ መነጋገር ነው፡፡ በሒደት ግን ምን ምን አጀንዳዎች ያቀርባሉ? በሚለው ጉዳይ ላይ እኛም በሒደቱ መሳተፍ አለብን የምንለው ጥያቄ በመኖሩ በሒደት የምናየው ነው የሚሆነው፡፡  

ሪፖርተር፡– አብን በወልቃይት ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ወልቃይት ግልጽ ነው፡፡ ከመጀመርያም ጀምሮ ወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት የሚባለው ግዛት የጎንደር በጌምድር አውራጃ አካል የነበረ ነው፡፡ የትግራይ፣ የኤርትራና ሌሎችም ወንድሞቻችን ሠርተው ይኖሩበት የነበረ አካባቢ ነው፡፡ በተመሳሳይ ወፍላ የአገር አካል የሆነና በወሎ አውራጃ ውስጥ የነበረ ነው፡፡ ራያም እንዲሁ የወሎ አካል የነበረ ነው፡፡ ሕወሓት በ1983 ዓ.ም. የደርግ መንግሥትን በጦርነት አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሁሉን አድራጊ፣ ሁሉን ፈላጭና ቆራጭ በመሆን ሥልጣን በመቆናጠጡ ምክንያት ታሪካዊ የአማራ ግዛቶችን የአያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን የሆኑ ርስቶችን በኃይል አዲስ ወደ ተፈጠረው የትግራይ ክልል እንዲጠቃለል አደረገ፡፡ ከዚያ በፊት ለሺሕ ዓመታት ወሰኑ ተከዜን ተሻግሮ እንደማያውቅ ግልጽ ነው፡፡ የታሪክ ማስረጃዎችና በርካታ ሰነዶችም ያሳያሉ፡፡ ሕወሓት ሥልጣን ሲይዝ ታሪካዊ የሆኑ የአማራ ርስቶችን ወይም ደግሞ የጎንደርና የወሎ ግዛቶችን፣ እንዲሁም የጎጃም ግዛት የሚባለውን መተከልን በኃይል ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በማካተት ደራ፣ የሚባለውን የአማራ ሸዋ ግዛት ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲካተት ማድረጉ ይታወሳል፡፡ እነዚህን ግዛቶች ሕዝባችን ሳይፈቅድ ወይም ደግሞ ሕዝባችን ሳይመክርበት ምንም ታሪካዊ መሠረት ሳይኖር ነው የጠቀለላቸው፡፡ በጊዜው የነበረው የቋንቋ ተናጋሪና የሚነገረው ቋንቋ ወደ እዚያ ክልል ይጠቃለላል የሚለውን ሕግ በመጣስ ወልቃይት ጠገዴን፣ ጠለምትን፣ ወፍላንና ራያን ወደ ትግራይ ክልል በማካተት ታላቋ ትግራይ ተብላ በሕወሓት ማኒፌስቶ ላይ የተገለጠችውን ግማሹን እንኳ ማሳካት ችሎ እንደነበር መናገር እንችላለን፡፡ ይህ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ትግራይ ክልል የተካለለ አካባቢ ወደ አማራ ክልል መመለስ አለበት፡፡ ሁለተኛ ሕወሓት ካለፉት ሦስት ዓመታት በላይ በወልቃይት አማራዎች ላይ ለፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ ከአካባቢው ለዘረፈው ሀብትም ካሳ መክፈል አለበት ብለን እናምናለን፡፡ እናም ይህም ለድርድር የማይቀርብና ለአማራ ክልል መንግሥትም ሆነ ለብልፅግና ፓርቲ የወልቃይት፣ የራያ፣ የጠለምትና የወፍላ ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መስመር መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በእኛ በኩል ያለውም ጉዳይ እነዚህ ታሪካዊ ርስቶቻችንና የማንነት ጉዳይ ለድርድር የማይቀርቡ ቀይ መስመሮቻችን ናቸው ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡– ከሰሞኑ የሕወሓት አመራሮች የአማራና የትግራይ ሕዝብ እንዲተባበርና በተለይም የአማራ ሕዝብ ጦርነት በቃኝ እንዲል፣ ሁለቱ ሕዝቦች ደም መፋሰስ እንደሌለባቸው ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምቷል፡፡ አብን ይህን መልዕክት እንዴት ይቀበለዋል? በቀጣይስ የአማራና የትግራይ ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ምን ሊመስል ይችላል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ የሕወሓት አመራሮችና አፈ ቀላጤዎች ሲያንቋሽሹትና ሲጠሉት የነበረውንና በጥላቻ ግፍ ሲፈጸምበት የነበረውን የአማራ ሕዝብ ወንድም እንደሆነ፣ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ተጣልቶ በጋራ መኖር አንችልም ወደ የሚል ትርክት ለማዞር ሞክረዋል፡፡ ሀቁ ግን የትግራይና የአማራ ሕዝብ ለረዥም ዘመናት በሥነ ልቦና የተሳሰረ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ የኖረ፣ በሃይማኖትና በበርካታ ነገሮች ሺሕ ዓመታት ትስስር አለው፡፡ ወንድማማች ሕዝብ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ግን በተለይ ከሕወሓት መምጣት በኋላ የአማራን ሕዝብ በማንቋሸሽ ‹‹የአማራ ሕዝብ ጠላታችን ነው፣ የአማራ ሕዝብ አከርካሪው ካልተሰበረ የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ነፃነት አያገኝም፤›› በማለት የጥላቻ ትርክት ጽፈው ያን የጥላቻ ትርክት የትግራይ ወገኖቻችንን በፕሮፓጋንዳ መልክ ሲግቱ ከርመዋል፡፡ አሁን እንዳየነው በዚህ ጦርነት ውስጥም አማራ ጠላት እንደሆነ፣ አማራን የሚያንቋሽሹ በርካታ ዘፈኖችና ስድቦች ሲያሠራጩ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ እነዚህ ነገሮች የሕወሓት ፅንፈኛ የሆነ ፋሽስታዊ ርዕዮተ ዓለም እንጂ፣ የትግራይ ሕዝብን ይወክላሉ ብለን አናስብም፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ነገ በወንድምነቱ በመቀጠል፣ በትግራይም ሆነ በአማራ ክልል ርስቶች ተንቀሳቅሶ፣ በሥርዓት ነግዶና አርሶ መኖር የሚችልበት መብት መከበር አለበት፡፡ ያላግባብ ወደ ትግራይ ተካለው የነበሩ አስተዳደራዊ ወሰኖች ወደ አማራ ክልል መካተት አለባቸው፡፡ ያ ማለት ግን በወልቃይት ወይም በራያ ትግሬ አይኑር ማለት አይደለም፡፡ በትግራይ ውስጥም አማራ ሄዶ ሊሠራ ይችላል፡፡ ሊኖርም ይችላል፡፡ እነ ደብረ ጽዮን ከአማራ ሱዳን ይሻላል ብለው ከሁለት ዓመት በፊት የተናገሩትን የረሱት ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ በእኛም ሆነ በአማራ ሕዝብ በኩል የትግራይ ሕዝብ ወንድማችን ነው፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ወንድማችን ነው፡፡ አማራ ከማንም ጋር ችግር የለበትም፡፡ ፅንፈኛ ብሔርተኛ ኃይሎች አማራን ለማስጠላት ሞከሩ እንጂ፣ የአማራ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በምንም ዓይነት ደረጃ የሚገለጽ ጥላቻ የለበትም፡፡ አማራ ከአፋሩ፣ አማራ ከሶማሌው፣ አማራ ከኦሮሞው፣ ከጉምዙ፣ ከሽናሻው፣ ከደቡብና ከጋሞ ጋር ወንድምና እህት ሆኖ ለረዥም ዘመናት ሰላማዊ መስተጋብር መሥርቶ፣ ተጋብቶና ተዋልዶ በሰላም ሲኖር የነበረበት ጊዜ የቅርብ ትዝታችን ነው፡፡ እሱ ይመለሳል፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብ ወንድማማችነት ይጎለብታል፡፡ የሕወሓት አስተሳሰብ ከትግራይ ሕዝብ ላይ ተቀርፎ ይጣላል፡፡ ያ የጥላቻ አስተሳሰብና ስብከት ተወግዶ በቅርብ ጊዜ የሕወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ ፈተው ትግራይ ሰላም የምታገኝበት፣ አገራችን በርካታ ውድመት ውስጥ የከተታት የደም መፋሰስ የሚቆምበትና ሕዝባችን የሰላም አየር ተንፍሶና ሠርቶ የሚኖርበት ዕድል ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡– ኤርትራ በሰላም ንግግሩ ትሳተፍ አትሳተፍ የሚሉ ሙግቶች ይሰማሉ፡፡ ይህን ጉዳይ አብን እንዴት ይመለከተዋል?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- እንግዲህ ስለድርድሩ ሒደት ስናስብ በድርድሩ ሒደት ውሰጥ መሳተፍ ያለባቸው፣ በጦርነቱ ተፋላሚና ተሳታፊ የነበሩ ኃይሎች ናቸው ብለን እናስባለን፡፡ ሕወሓት በሽብር ወረራው ወደ ኤርትራ ሮኬት በማስወንጨፍ ትንኮሳዎችን በተከታታይ በመፈጸሙ ምክንያት፣ ኤርትራውያን ወደው ሳይሆን ተገፍተው ሕዝባቸውንና አገራቸውን ለመጠበቅ እዚህ ጦርነት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል ብለን እናስባለን፡፡ የአፍሪካ ኅብረትም በግልጽ ኤርትራ በዚህ ሒደት መሳተፍ አለባት ብሎ መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ በእኛም በኩል ያለው ዕሳቤ ኤርትራውያን መሳተፋቸው ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ፣ ወይም ደግሞ ትርጉም ባለው ደረጃ ተፋላሚ ኃይሎች አንድ ላይ ተቀምጠው ይህንን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ሒደት ውስጥ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን የራሳቸው ድርሻ አላቸው፣ መጋበዝና መሳተፍ አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡– በኦሮሚያ ክልል ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ ተከስተዋል፡፡ አብን በዚህ ላይ ያለው አቋም ምንድነው?

ዶ/ር ደሳለኝ፡- እንግዲህ ትልቁና በጣም አስቸጋሪ የሆነው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ትኩረት በመያዙ፣ ኦሮሚያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በሕዝባችን ላይ የጅምላ ዕልቂትና የጅምላ መፈናቀል እየፈጸሙ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን የኦሮሚያ ክልል መሪዎችና ኃላፊዎች፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቅን ጥፋት ማስቆም አልቻሉም፡፡ በመንግሥታዊ ኃላፊነታቸው ሊጠብቁት የሚገባውን ሕዝብ ለጅምላ ፍጅት አጋልጠው በመስጠታቸው ተጠያቂ የሚያደርጋቸው በመሆኑ፣ በተደጋጋሚ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥትን ስንጠይቅ ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ አገራችንን ወደ አለመረጋጋት የሚወስድና ወደፊት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ሊያስጠይቅ ስለሚችል፣ መንግሥት የፖለቲካ ዋጋ በመስጠትና ከፍተኛ የደኅንነት ጉዳይ አድርጎ በመመልከት በአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል ብለን እናስባለን፡፡ ለዚህም በተከታታይ ስናደርግ የነበረውን ጥሪ ዛሬም ማድረግ እንፈልጋለን፡፡   

October 30. 2022

Ethiopian Reporter

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.