በጦርነት ጊዜ መሪ መቀየር ይቻላል! #ግርማካሳ
በዛሬው ምሽት (ነሐሴ 2/2013) በወልዲያ በተካሄደ ውጊያ ወያኔ #በመድፍ ወልዲያን ሲደበድብ አምሽቷል።
ዶር አብይ አህመድ መቀሌን በሻሻ አድርገናታል፤ ከባባድ መሳሪያዎችን ሁሉ ይዘን ነው የወጣነው ብሎ ነበር፡፡ ታዲያ ከርቀት ወልዲያን ሲደበድቡ የነበሩ ከባባድ መሳሪያዎች ከየት እንደመጡ ድፍረት ካለው ወጥቶ ለወልዲያ ነዋሪዎች ቢነግራቸው ጥሩ ነበር፡፡
እንግዲህ በዚሁ መልኩ የሚዋሽ ፣ የማይታመን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እያለ እንዴትስ በአስተማማኝ ሁኔታ የዜጎች ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ይቻላል ? ለዚህ ነው ለውጥ መኖር አለበት የምለው፡፡
በሁለተኛ አለም ጦርነት ፣ ጦርነቱን እንደ ግሪጎሪያን አቆጣጠር በ1939 ናዚዎች ሲጀምሩ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበሩት ኔቪል ቻምበርለን ነበሩ፡፡ ቻምበርላን በጣም ደካማ መሪ ስለነበሩ፣ በጦርነቱ መካከል በዊንስተን ቸርችል እንዲተኩ ተደረገ፡፡
አንዳንድ ሰዎች አሁን ዶር አብይን የመቀየሪያ ጊዜ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ እንደውም ጊዜው አሁን ነው ባይ ነኝ፡፡ ዶር አብይ እንደ ጠቅላይ ሚኒስተር ቻምበርሌን ነው፡፡ ዊንስተን ቸርችል ያስፈልገናል፡፡ አዲስ አመራር ያስፈልጋል፡፡
እስቲ እግዜር ያሳያችሁ፣ ትላንት ከትግራይ ለቃችሁ ውጡ፣ ከኮረም፣ ከአላማጣ ለቃችሁ ወጡ የሚል ትእዛዝ የሰጠ፣ አሁን በምን የሞራል ብቃቱ ነው እንደገና አላምጣን፣ ኮረምን፣ ትግራይን ነጻ አውጡ ብሎ ሕወሃት ላይ ዘመቻ ሊጠራ የሚችለው ???? ማንስ ያምነዋል ? የመከላከያ ስራዊት አባላቶቻችን ተዋግተን ድል ካገኘን በኋላ እንደገና ልቀቁ ቢለንስ የሚል አስተሳሰብ ሊይዙስ አይችሉም ወይ ? ህዳር ላይ ትልቅ ዋጋ ተከፍሎ የተገኘውን ድል ሜዳ ላይ የበተነ መሪ ፣ አሁንም ሌላ ዋጋ ተከፍሎ እንደገና ሜዳ ላይ እንደማይበትነው ምን ማስተማመኛ አለ ? ምንም የለም፡፡
ለዚህ ነው ቻምበርሌን እንደለቀቀው፣ ዶር አብይም መልቀቅ አለበት የምለው፡፡ በሕወሃት ላይ የሚደረገው ዘመቻ በአሸናፊነት ለመወጣት፡፡ እንደውም ዶር አብይ መቀጠሉ የበለጠ ጦርነቱ እንዲቀጥል የሚያደርግ ሊሆን ይችላል፡፡ የዶር አብይ መኖር በራሱ ለሕወሃቶች ጥንካሬም ነው፡፡
ቀላሉ መንገድ የብልጽግና ፓርቲ ራሱ ተሰብስቦ ዶር አብይን ከድርጅቱ መሪነት ማንሳት ይችላል፡፡ ያንን የማድረግ ሙሉ ሕጋዊ ስልጣን አለው፡፡ ዶር አብይ ብቻ አይደለም፣ ምክትሉም አቶ ደመቀ መኮንን መሰናበት አለበት፡፡
በተወሰነ መልኩ ምርጫ ተደረገ እያሉ ነው፤፡ በብዙ ቦታዎች ምርጫ አልተደረገም፡፡ ምርጫ ባልተደረገባችው ቦታዎች ጳጉሜን 1 ብለዋል። በዚህ ወቅት እንዴት ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል አላውቅም፡፡ ስለሆነም መስከረም ላይ መንግስት መስርቶ መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ጦርነት ስላለ እንጂ በምርጫው ዙሪያ የፍርድ ቤት ውዝግቦች ብዙ አሉ፡፡ ስለዚህ የብልጽግና ፓርቲ፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ፈቶ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን የአንድነት መንግስትም መመስረት አለበት ባይ ነኝ፡፡
አዲስ የሚመረጠው የብልጽግና መሪ በተቻለ መጠን ከኬሎች ጋር መስራት የሚችል ከሆነ፣ የአንድነት ካቢኔ ከተመሰረተ፣ ቢያንስ አፍጦ በፊታችን የመጣውን ቻሌን በጋራ እንድንወጣ ሁኔታዎች ሊያመቻች ይችላል፡፡ ህዝብን አስተባብሮ አንድ አድርጎ መቀጠል ይችላል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ እንደ ሕወሃት ግትር ከመሆን ተቆጥቦ በርግጥ የአገርን ጥቅም ካስቀደ ይሄን ማድረግ ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ይሄ አንዱ ነው፡፡
ሌላው የመከላከያ አመራር እንደገና ተጠንቶ ብቃት ባለው መልኩ መዋቀር አለበት፡፡ የአገርን ጥቅም የማያስቀድሞ፣ ዘረኛ የጦር መኮንኖች መሰናበት አለባቸው፡፡ “አገራችን አይደለም አንዋጋም” የሚሉ፣ ለአገር ሳይሆን ለጎጣቸው የቆሙ የሰራዊት አባላት እንዲለቁ መደረግ አለበት፡፡
የባህታዊ ፅሁፍ ነው! ርካብና ወንበርን በሴራ የጨመደደ 7ኛው ንጉስ በምን ተአምር ጠቅላይ ምኒስትርነቱን ለቆ በሌላ ይተካል!?