Breaking News
Home / Amharic / በአዲስ አበባ የኦሮምያን ባንዲራ መስቀልና የክልሉን መዝሙር የማዘመር አካሄድ ለሃገሪቱ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ስለሆነ እንዲቆም የፌዴራሉ መንግስት አዘዘ

በአዲስ አበባ የኦሮምያን ባንዲራ መስቀልና የክልሉን መዝሙር የማዘመር አካሄድ ለሃገሪቱ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት ስለሆነ እንዲቆም የፌዴራሉ መንግስት አዘዘ

መንግስት በአዲስ አበባ ያለ ነዋሪዎች ይሁንታ የኦሮምያን ባንዲራ ለማውለብለብና መዝሙር ለማዘመር የሚደረገው ግፊት እንዲቆም አዘዘ

የፌደራል መንግስት በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የኦሮምያ ክልል ባንዲራ እንዲሰቀልና መዝሙር እንዲዘመር እየተደረገ ያለው ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ እንዲቆም መመሪያ መሰጠቱን ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ከፍተኛ የፌዴራል መንግስ ባለስልጣናት ። ከሰሞኑ በዚሁ የባንዲራ እና መዝሙር ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ቀውስ መፈጠሩ ይታወሳል። ከግርግሩ ጋር በተያያዘ የተጎዱ ተማሪዎች እንዳሉና የታሰሩ ሰዎችም መኖራቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

ከኦሮምያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ላለፋት ሁለት ሳምንታት ግርግሮች ጠንክረው ይታዩ እንጂ ከአንድ አመት ወዲህ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ የከተማዋ የትምህርት ተቋማት ተመሳሳይ ችግሮች ሲከሰቱ ተስተውለዋል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ባለፈው አንድ አመት ብቻ በተመሳሳይ የኦሮምያን ባንዲራ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከመስቀልና መዝሙሩን ከማዘመር ጋር የተያያዙ ችግሮች 12 ጊዜያት ያህል ተፈጥረዋል።

የጉዳዩ በዚህ ደረጃ እየከረረ መምጣት ያሳሰበው የፌደራል መንግስት በትምህርት ቤቶቹ የኦሮምያ ባንዲራ እንዲሰቀልና መዝሙር እንዲዘመር እየተደረገ ያለው ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ እንዲቆም አቅጣጫ አስቀምጧል። ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው በአዲስ አበባ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮምያን ባንዲራ የመስቀልና የክልሉን መዝሙር የማዘመር አካሄድ “ በከተማ አስተዳደሩ ያሉ አመራሮች ከተለያዩ አካላት ጋር እልህ በመጋባት እየፈጸሙት ያለው ተግባር” እንደሆነ የፌደራል መንግስት እንደሚያምንና ይህም ለሀገሪቱ ተጨማሪ የደህንነት ስጋት የመፍጠር አቅም ስላለው በድርጊቱ የተሳተፉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በፍጥነት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መታዘዛቸውን ነው። የፌደራሉ መንግስት እልህ የተጋቡ ያላቸውን አካላት በዝርዝር አላብራራም።

በዚህ በሰንደቅ አላማ ማውለብለብና መዝሙር በማዘመር እርምጃ በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የከፋ ጥርጣሬና ክፍፍል ያስከተለ ሲሆን የፓርቲው ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ድርጊቱን እንዲያስቆሙና በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዲደረግ የጠየቁ አባላት መኖራቸውን ለድርጅቱ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ስምተናል። ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ “የአንድን ብሄር ማንነት ብቻ ለማንጸባረቅ” ሲል የገለጸውን እንቅስቃሴ በፍጥነት እንዲቆም ማዘዙንም ዋዜማ ሬድዮ አረጋግጣለች። ሆኖም የፌደራል መንግስት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሰሞኑ የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢ የጸጥታ ችግሮች ጋር ተደምረው ተጨማሪ የደህንነት ስጋት እንዳይሆኑ ከመስጋት የወሰደው ጊዜያዊ መፍትሄ ይሁን ዘላቂ እርምጃ ዋዜማ ሬድዮ ማረጋገጥ አልቻለችም።

በአዲሰ ከበባ ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮምያ ክልል ባንዲራ ለመስቀልና የክልሉን መዝሙር ለማዘመር የተደረገው እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ተቋም : ከሌሎች ተቋማት እና ከፖለቲካ ፖርቲዎች ብርቱ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ባለፋት ሁለት ሳምንታት ከክልል ባንዲራና መዝሙር ጋር በተያያዘ ጠንከር ብሎ የታየውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በብሄራዊ ቴሌቭዥን በታየው ንግግራቸው ; የኦሮምያ ክልል ባንዲራን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመስቀልና መዝሙሩን የማዘመር ውሳኔ አዲስ እንዳልሆነ እና ከዚህ ቀደም በከተማዋ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለማስተማር ጥረት በሚደረግበት ወቅት ከተማዋ የራስዋ የትምህርት ፖሊሲ የሌላት በመሆኑ ፖሊሲውን ከኦሮምያ ክልል በውሰት ተወስዶ መተግበሩን ሲገልጹ ተሰምተዋል። ይህም ፖሊሲ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች የክልሉ ባንዲራ እንዲሰቀል እና መዝሙሩም እንዲዘመር የሚያዝ በመሆኑ ተግባራዊ መደረጉን ከንቲባዋ አንስተዋል። ከንቲባዋ አክለውም በቀጣይ ጊዜ ሌሎች ቋንቋዎች በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መሰጠት ሲጀምሩ ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

የዜናው ምንጭ ዋዜማ ራዲዮ ነው። merejatv

News in Pictures

Time in Ethiopia

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.