በአማራ ተማሪዎች ማህበር (አተማ) እና በአማራ ወጣቶች ማህበር (አወማ) በጋራ ፋኖን አስመልክቶ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የአማራ ተማሪዎች ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በአደረጃጀት አማራዊ ሆኖ በራዕይ ኢትዮጵያን አንግቦ የበርካታ አማራ ልጆችን አቅፎ የያዘ በተማሪዎች የተመሠረተ ግብረ ሰናይ ማህበር ነው።በአደረጃጀቱም አማራ የሆነና በስነ ልቦና የሚመስሉትንና ለኢትዮጵያ ቀናዒ ራዕይ ያላቸውን ከሊህቅ እስከ ደቂቅ(ከዶክትሬት ዲግሪ እስከ አንደኛ ደረጃ) ድረስ ያሉ ተማሪዎችን ያቀፈ ግዙፉ ሀገር በቀል ተቋም ለመሆን እየሰራ ያለ ማህበር ነው። የማህበሩ በተማሪዎች መቋቋም ዋነኛ አላማ በትምህርቱ ዘርፍ መሻሻልና ለውጦችም ይመዘገቡ ዘንድ የበኩሉን ማበርከት ነው።
ሆኖም ይህ ማህበር ገና ከጅምሩ ችግሮችን አስተናግዷል፤ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ግፍና መከራ መፈናቀልና ከዚያም በላይ በወንበዴዎች ታግተው፣ በመንግስት አሸናፊነት ከእጃችን ገቡ ከተባሉ በኋላ የውሃ ሽታ ሆነው የቀሩት 17 አማራ ተማሪዎች ጉዳይ አማራ ነኝ ለሚል ሁሉ የእግር እሳት ነው። ሰብዓዊ ህልውና ያለውና የአማራ ቁስል የሚያሳዝነው ማንኛውም አለማቀፋዊ ለሆነ የሰው ልጅ ሁሉ ተራ አሉባልታ አይደለም።
ይህን ጉዳይ በወንጀል እንደሚጠየቁበት ማሰላሰል የብልሆች ተገቢ አተያይ በነበረ፤ ነገር ግን ዞረው ከጫንቃው ላይ ያስቀመጣቸው ምስኪን ህዝብ ላይ ያስታጠቃቸውን ዝናር ሲፈቱ ግን ከግርምትም በላይ ነው። በከሚሴ ንፁሃን ላይ ባሩድ ሲፈላ ወንጀሉን አድበስብሰው እራሱን ለመከላከል የሞከረን ገበሬ ታጥቆ ከሚያሸብር ወንበዴ እኩል ማወራረጃ ተደርጎ የሁለት ጎረምሶች ግጭት በሚመስል ተራ የንቀት ቃል በማጣጣል የንፁሃንን ደም ውሻ ልሶት ቀረ።
በቤንሻንጉል ጉምዝ በርካቶች የጦር ኢላማ መለማመጃ ሆነው ሲያልቁ። ዜና ለመዘገብ እንኳን የመንግስት ሚዲያዎች የአማራ የሆነው ሁሉ ይቅርብኝ ያሉ ይመስል አፋቸውን ለጎሙ። ምስኪኑ ህዝብ እራሱን ከአውሬ ለመከላከል ያደረገውን ጥረት አሁንም ከረፈደ ደርሠው ግጭት በሚል ፈሊጣቸው የማካካሻ ምላሽ ይሰጡናል። በኦሮሚያ፣ በጎንደር በርካቶች ተቀሉ፣ ታረዱ ተቃጠሉ የመንግስት ትኩረት ግን አሁንም ያጎነቆለው የአማራ ብሔርተኝነት ላይ ነው።
ፋኖ በክብር ጃኖ ለብሶ በዙፋን ላይ መቀመጥ የነበረበት ያኔ ሁለት ሺህ ስምንት-አስር ግዳጁን ፈፅሞ እነ ዶክተር አብይን ከዙፋን ላይ ሲያወጣ ነበር። ታሪካዊ ስህተት ተፈፅሞ በኢህአዴግ አመራር ውስጥ ክህደት የፈፀሙትን ለሌላ ንግስና በማጨት ዳግም አመድ አፋሽ ሆነ።
ታዲያ አሁን በሁሉም አቅጣጫዎች አማራው ቀጣይ የተማረ ተተኪ ሀይል እንዳይኖረው በእቅድ ታስቦ ከ35,000 በላይ የአማራ ተማሪዎች ተፈናቅለው፣ ከ400 በላይ የማህበሩ አመራሮች ለምን የአማራ ተማሪዎች ፍትህ ጠይቃችሁ ተብለው ከትምህርት ገበታቸው እየታገዱ እና በአለም ላይ ተፈጽሞ የማያውቅ ከ3 ወር በላይ ተማሪዎች ታግተው እና እንደ አማራ ህዝብ ደግሞ በደል ተፈጽሞብናል የሚሉና በጠላትነት ፈርጀው የሚንቀሳቀሱ ድውያኖች መጣሁልህ እያሉ የመትረየስ ጫፍ እያሳዩት ፋኖ ተበተን የሚሉት አማራን ለምን አጭተውት ነው? ብሎ መጠየቅማ ጤነኝነት ነው።
ለማንኛውም መቶ ፋኖ ሲገደል አንድ ሺህ እያፈራ መሄዱ አይቀሬ ነውና አማራን በሙሉ ወታደር እንዳታደርጉት እንሰጋለን።ምክንያቱም ፋኖነትት የአማራ ሥነልቦና ሥሪት ነውና!
ክልላችን ውሥጥ ዘራፊ እንጅ : ዘራፊ ፋኖ ፣ ወንበዴ እንጅ፡ ወንበዴ ፋኖ የለም፡፡ ጥንት ለሀገሩ ተዋድቆ ሀገር የገነባ፤ትናንት ህይወቱን ገብሮ ለውጥ ያመጣውን ፋኖ የማይሆን ስም ሰጥቶ ማጥፋት መንግሥት ለሌላ መብት ረገጣ የተዘጋጀ ይመስላል።
ይታሰብበት! አማራ ጥያቄዎቹን የሚመልስለት አደረጃጀት ያስፈልገዋል። አዴፓ/ብልፅግና ግን ተፈትኖ የወደቀ ይመስላል።ታሪካዊ ድል ማስመዝገብ ሲችል ታሪክዊ ስህተት በመፈፀም ሽንፈቱን ደራርቦ እየተከናነበ የሚገኝ ለአማራው ተስፋ የሌለው ድርጅት መሆኑን እያስመሰከረ ይመሥላል።
በአማራ ክልል ሌባና ዘራፊ ለመበራከቱ የክልሉ መንግስት እንጂ ፋኖ ተጠያቂ አይደለም። አማራ ክልል ማን እንደሚዘርፍና ህፃናትን እንደሚያግት አጣርቶ መረጃ ማቅረብ የማይችል አስተዳደር ያለበት ክልል ነው። በርካቶች ተወልደው ባደጉበት ቀያቸው ጭልጋና ማዕከላዊ ጎንደር በሽፍቶች በጥይት እየተቆሉ ሲገደሉና ቤታቸው በእሳት ሲቃጠል በማረጋጋትና ጥቃቱን በመቀልበስ የክልሉ የጸጣታ መዋቅር የፋኖን ያህል ሚና አልነበረውም።
በሽፍቶች ታግተው በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት ህፃናት ገዳያቸው ማን ነበር? አስራ ሰባቱ እህትና ወንድሞቻችንን ማን በላቸው? መንግስት የሰወራቸውን ተማሪዎች ጉዳይ ይዘው ፍትህ የጠየቁ ምስኪን የተማሪ ቤተሰቦችስ በእስር ቤት የመማቀቃቸው እንቆቅልሽ ምንድን ነው?
ፍትህ ማለት እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ነው፡፡
መፍትሔው ግን የፋኖ መጥፋት ሳይሆን የህዝቡን የህልውና ጥያቄ መመለስ ነው። ሕገ ወጦች መንግስት ህግ ሲያከብር ይጠፋሉ።
የአማራ ተማሪዎች ፣ የአማራ ወጣቶች ፣ የአገር ሽማግሌዎች እንዲሁም መላው የአማራ ህዝብ ሆይ! ከጀግኖች ልጆችህ (ከፋኖ) ጎን ትቆም ዘንድ እናሳስባለን።
ፋኖነት ለአማራው ስነልቦናውና ግብሩ ነው!!
አማራነት በከዋክብት ልጆቹ ይደምቃል!!
አተማ እና አወማ 20/07/2012 ዓ.ም