Breaking News
Home / Amharic / መልእክት ከመንግስት ለዲያስፓራ!

መልእክት ከመንግስት ለዲያስፓራ!

– ማስታወቂያ –

– ማስታወቂያ –

 

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ።

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል

መንገደኞች ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቧቸው የግል መገልገያ የሆኑ ልብስና ጫማዎች ‹‹ለአንድ ቤተሰብ ከሚያስፈልገው›› እንዳይበልጡ የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ‹‹የሻንጣ ንግድ›› ለሚያካሄዱ ግለሰቦች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮ የነበረውንና በኅዳር 2014 ዓ.ም. ዕገዳ የተጣለበትን መመርያ ቁጥር 51/2010 የሚተካ ነው፡፡ የገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መነሻ፣ ሚኒስቴሩ ረቂቅ መመርያውን ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ልኮ እንዳስመዘገበ ገልጸው፣ በሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ ፊርማ እንደሚወጣ አስረድተዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ወጥቶ ከዘጠኝ ወራት በፊት ዕገዳ የተጣለበት የቀድሞው መመርያ፣ ለግል መገልገያ የሚውሉና ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የተዘጋጁ ልብስና ጫማዎች ብዛት ላይ ገደብ አላስቀመጠም ነበር፡፡ አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ በአንፃሩ ያለ ቀረጥ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የፅዳት ዕቃዎች ‹‹አንድ ቤተሰብ ከሚያስፈልገው›› መብለጥ እንደሌለባቸው ይደነግጋል፡፡ መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎች ደግሞ ‹‹አንድ ሰው በሚያስፈልገው›› መጠን እንደሚሆኑ መመርያው ላይ ሠፍሯል፡፡

በተጨማሪም ረቂቁ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የሚፈቀድላቸው የግል መገልገያ የቁሳቁስ ዓይነቶች 16 ብቻ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ በቀድሞው መመርያ ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ የግል መገልገያ ዕቃዎች 130 የነበሩ ሲሆን በአዲሱ ረቂቅ ይህንን በ87 በመቶ ቀንሶታል፡፡

ከዚህ ቀደም ለግል መገልገያ ተብሎ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ይፈቀዱ የነበሩት ቴሌቪዥን፣ የማዕድ ቤት ዕቃዎች፣ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ መጻሕፍት፣ የሕፃናትና መጫወቻና መገልገያዎች ዕቃዎች በረቂቅ መመርያው ውስጥ አልተካተቱም፡፡

መድኃኒቶች፣ የሕክምናና የፅዳት ዕቃዎች በረቂቁ ላይ የተቀመጡት ሳይዘረዘሩ በጥቅል ነው፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን በ2010 ዓ.ም. በወጣው የግል መገልገያ ዕቃዎች መመርያ መሠረት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ያገደው፣ መመርያው መንገደኞች ለግል መገልገያ ተብሎ ካለ ቀረጥ የሚገቡ ዕቃዎች በሕጋዊ ንግድ ላይ ኢፍትሐዊ ውድድር በመፍጠሩ መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ወጥቶ በነበረው መመርያ መሠረት ተመላላሽ ነጋዴዎች በተለይ እንደ ልብስና ጫማ ያሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ከዱባይ፣ ከታይላንድና ከሌሎች አገሮች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ይሸጡ ነበር፡፡

ይሁንና አልባሳትንና ጫማዎችን ለንግድ ዓላማ ለማዋል ቀረጥ ከፍለው ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ነጋዴዎች፣ በዚህ አሠራር ምክንያት ኢፍትሐዊ ላልሆነ ውድድር እንደተጋለጡ የጉምሩክ የኮሚሽኑ የቅሬታ ክፍል ኃላፊ አቶ ዘሪሁን አሰፋ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ተመላላሽ ነጋዴዎች በሳምንት ሦስት ጊዜ በተለይ አልባሳትን ከቀረጥ ነፃ ማስገባታቸው፣ በገበያው ውስጥ ልዩነት መፍጠሩን ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹ቀረጥ እየከፈሉ የሚያስገቡ በርካታ ነጋዴዎች እኛ ዘንድ እየመጡ መወዳደር አልቻልምን ብለው ቅሬታ አቅርበው ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከቀረጥ መሰብሰብ የነበረበት ገቢ በዚህ ምክንያት እንደታጣ አስረድተዋል፡፡

ማንኛውም መንገደኛ ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ሲያስገባ ቀረጥና ታክስ እንዲከፍል፣ የሚገባው ዕቃ ለንግድ ይውላል ተብሎ ከታመነ በቅጣት እንዲስተናገድ በኅዳር ወር ተወስኖ ነበር፡፡ ለንግድ ይውላል ተብሎ የታመነን ዕቃ ከአንድ ጊዜ በላይ ሊያስገቡ ሲሉ የተያዙ መንገደኞች፣ ጉዳያቸው በወንጀል ምርመራ እንዲታይም ኮሚሽኑ ትዕዛዝ አስተልፏል፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽን ይህንን ዕገዳ ሲያስተላልፍ አገልግሎቶች የሚታገዱት ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከኮሚሽኑ የተወጣጣ ኮሚቴ ጥናት አድርጎ መመርያው እስከሚሻሻል እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡

አሁን በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ለግል አገልግሎት የሚውሉ ሞባይል፣ ላፕቶፕ፣ የፎቶግራፍ ካሜራ፣ ዊልቸር፣ የእጅ ሰዓት፣ ሲጋራ፣ የፀጉር መተኮሻና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው 14 ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡ እነዚህ ዕቃዎች ብዛታቸው ገደብ የተቀመጠለት ሲሆን፣ የአብዛኞቹ ብዛት አንድ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ ውጪ መንገደኞች ‹‹አንድ ቤተሰብ ከሚያስፈልገው›› ሳይበልጥ ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው ልብሶች፣ ጫማዎች፣ የፅዳት ዕቃዎች፣ እንዲሁም መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያዎችን ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ወጥተው ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ በውጭ አገር ሲኖሩ የነበሩና ጓዛቸውን ጠቅልለው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚመለሱ ኢትዮጵያዊ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ግለሰቦች፣ ሲገለገሉባቸው የነበሯቸውን ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ይህ ተሽከርካሪን የማያካትት ሲሆን፣ ተመላሾቹ ሌሎች ዕቃዎቻቸው ቢያንስ አንድ ዓመት ያገለገሉ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

ረቂቅ መመርያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በስጦታ የሚላክላቸውን የግል መገልገያ ዕቃ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ከፍለው መረከብ እንደሚችሉ ደንግጓል፡፡ ስጦታው የመጣለት ሰው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የሌለው ከሆነ ዕቃው የጉምሩክ ቀረጥ ማስከፈያ ዋጋ ላይ የሚሰላ 30 በመቶ የገቢ ግብር ይከፍላል፡፡

በስጦታ የሚላከው ዕቃ የተገዛበትና እስከ ማስጫኛ ወደብ ድረስ የሚኖረው ዋጋ ከአንድ ሺሕ ዶላር መብለጥ እንደሌለበት በመመርያው ሠፍሯል፡፡ አንድ ግለሰብ በአንድ ዓመት ውስጥ ከሁለት ጊዜ በላይ ስጦታ ሊቀበልም አይችልም፡፡

ከአንድ ወር በፊት የ2015 በጀት ዓመትን የጀመረው መንግሥት 786 ቢሊዮን ብር በጀት ሲያፀድቅ፣ የ309 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳለበት አስታውቋል፡፡ የፌደራል መንግሥት ይህንን ጉድለት ለመሙላት በተጀመረው በጀት ዓመት ገቢን ለመጨመር የሚያስችሉ የታክስ ሕግ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ፋኖን እርዱ

 

Multi threaded Redundant Dedicated Server in USA and in Europe.