የአገር ባለውለታዎችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን በመደገፍ ወገናዊ አለኝታነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 27/2015 “የአገር ባለውለታዎችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን በመደገፍ ወገናዊ አለኝታነታችንን በተግባር ማሳየት አለብን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአገር ባለውለታዎች እና አቅመ ደካሞች 193 መኖሪያ ቤቶችን በስጦታ አበርክቷል፡፡
ቤቶቹ የተገነቡት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሲሆን የከተማ አስተዳዳሩ ከበጎ አድራጊዎች ጋር በመተባበር ያሥገነባቸው ቤቶች ናቸው፡፡
የቤት ስጦታውን አስመልክተው ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የአገር እና የትውልድ ባለውለታዎችን ማስታወስና ከጎናቸው መቆም ይገባል ብለዋል፡፡
የቤት ስጦታው የአገር ባለዉለታ ወገኞችን ያሥታወሰ፣ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው ለነበሩ ወገኖችም እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የዜጎችን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
“ለህዝባችን የሚጨበጥ፣ የሚታይ፣ ችግሩን ሊያቃልል የሚችል እና አገሩን እንዲወድ የሚያደርጉ በጎ ተግባራትን እናከናውናለን እንጂ ባዶ ተስፋ ይዘን ከፊቱ አንቆምም” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
የቤት ስጦታ ያገኙ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም የቤት ስጦታው ለረጅም ዘመናት ከነበሩበት ችግር የሚያላቅቃቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ እያከናወነ ላለው ዜጋ ተኮስ ስራም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዛሬው ዕለት የቤት ስጦታ ያገኙት የአገር ባለውለታ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ይልማ ገብረአብ ፣ ጌታቸው ካሣ ፣ አሸናፊ ከበደ ፣ ሻምበል በላይነህ እና በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የአርቲስት መስፍን ጌታቸው እናት ናቸው፡፡